Monday, February 29, 2016

የጋይንት ህዝብ ስለወልቃይት ጉዳይ አትጠይቅም በመባሉ ስብሰባ ረግጦ ወጣ

የካቲት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ጎንደር ዞን በጋይንት ከተማ የክልሉ ባለስልጣናት ህዝቡን ለማወያየት ትናንት እሁድ የጠሩት ስብሰባ፣ በተቃውሞ ተበትኗል።

የተቃውሞው መነሻ ደግሞ ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ፣ ህዝቡ ጥያቄ ማቅረብ በመጀመሩና ስብሰባውን የሚመራው ጋዜጠኛ ” ስለወረዳችሁ እንጅ ስለሌሎች አካባቢዎች ጥያቄ መጠየቅ አትችሉም” ማለቱን ተከትሎ ነው።

ስብሰባው የተጠራው ከዚህ ቀደም የከተማዋ ነዋሪዎች የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠርተውት የነበረውን ስብሰባ ረግጠው መውጣታቻው ተከትሎ ነው። በአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ባልደረቦች በተመራው ስብሰባ የወረዳው ከንቲባ አቶ ሙላው ጤናው ያቀረቡትን አጭር ሪፖርት ህዝቡ ውድቅ አድርጎታል።
ተሰብሳቢዎቹ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ጠያቂ ” ኢህአዴግ ጋይንት ከገባ 27 አመት ሆኖታል። 27 አመታት ሙሉ የረሳችሁትን ህዝብ፣ ዛሬ እንዴት ልታነጋገሩት መጣችሁ?” በማለት የጠየቁ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ መንግስትና ተሳፋሪ ሊወርድ ሲል ጩኸት ያበዛል በማለት መንግስት አሁን መውረጃው በደረሰበት ሰአት እንዳስታወሳቸው ተናግረዋል።
በርካታ ተሰብሳቢዎች በወልቃይት ጉዳይ ላይ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ሰብሳቢው ጋዜጠኛ “ወረዳችሁን ብቻ የተመለከተ ጥያቄ አንሱ እንጅ የወልቃይትን ጥያቄ ማንሳት የለባችሁም ” ማለቱን ተከትሎ ህዝቡ በአንድነት አዳራሹን ለቆ ወጥቷል።
በዚህ መሃል አንድ አባት ኢህአዴግ ገንዘብ ለመሰብሰብ የመጣ ዘረኛ መንግስት ነው ሲሉ ተናግረዋል። በተለይ በ97 ቅንጅትን ወክሎ የተወዳደረ መምህር በርካታ ጥያቄዎችን አንስቶ ጠይቋል። መምህሩ፣”አንድ አርሶአደር ምርቱን በጎታው ከከተተ በሁዋላ በየጊዜው ይፈትሻቸዋል፤ እህሉን ነቅዞ ካገኘው፣ የነቀዘው ያልነቀዘውን እንዳያበላሸው፣ የነቀዘውን እህል አውጥቶ ይጥለዋል፤ የኢህአዴግም አመራር የነቀዘ እህል ማለት ነውና ሊጣል ይገባዋል” ብሎአል። ዘረኝነትንና ጎጠኝነት በማስመልከት ያቀረበው ግጥምም በህዝቡ ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል።
ሌላ ተናጋሪ በበኩላቸው ” ኢህአዴግ ንፋስ መውጫን እያስተዳደረ አይደለም፣ እያስተዳደሩ ያሉት የእድርና የእቁብ ኮሚቴዎች ናቸው ” ያሉ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ንፋስ መውጫን እናስተዳድራለን የሚሉ ሰዎች “ወገዳ” የሚል ያስተዳደር ስርዓት እንደሚከተሉ፣ ወገዳ ማለት ደግሞ ወገን፣ ገንዘብና ዳሌ ማለት መሆኑን ገልጸዋል። የከተማው አመራሮች “አሸጎዳ” እንደሚባሉ፣ አሸጎዳ ማለት ትግራይ ላይ የተገነባ የንፋስ የሃይል ማመንጫ ሲሆን፣ ባለስልጣኖቹን በ ተደጋጋሚ በመዋሸታቸው የተሰጣቸው ስያሜ መሆኑን ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment