Friday, February 5, 2016

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከእስር እንዲለቀቁ ተጠየቀ።

ጥር ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢህአዴግ መንግስት እንደማያስራቸው የሰጣቸውን ዋስትና አምነው ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የአክሰስ ሪል ስቴት መስራች አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ ጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ ይገኛሉ።
አቶ ኤርሚያስ ሰሞኑን ጥር 23 ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የህግ አማካሪያቸውና ጠበቃቸው አቶ ሞላ ዘገዬ የደንበኛቸው መታሰር አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ሞላ ገለፃ አቶ ኤርሚያስ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ሳይለይ መታሰራቸው ከሕግ አግባብ ውጪ ነው።
አቶ ኤርሚያስ የተጠረጠሩበት ድርጊት ወንጀል ወይም ፍትሐ ብሔር መሆኑ እንዳልተለየ የገለጹት ጠበቃው፤ <<ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ...በት ድርጊት ሳይለይ፣ እሳቸውን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተገቢና ሕግን የተከተለ አይደለም>> ብለዋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ በተጠረጠሩበት ድርጊት ማስረጃ ቀርቦባቸዋል ቢባል እንኳን ዋስትና የሚያስከለክላቸው ሊሆን እንደማይችል የተናገሩት አቶ ሞላ፤ ያላቸው ማንኛውም ዓይነት ሀብት ዕግድ ስለተጣለበት የሚያሸሹትም ሆነ የሚሸሽጉት ነገር ስለሌለ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ማእከል መርማሪ ቡድን ቀደም ብሎ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ የሠራውን በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ ካቀረበ በኋላ፣ ምርመራውን እንዳላጠናቀቀ በመጥቀስ ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲሰጠው ሲጠይቅ፤ ያቶ ኤርሚያስ ጠበቃ ተቃውመዋል፡፡
ፖሊስ መጀመሪያውኑ ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር ከማዋሉ በፊት የሚያስፈልገውን ማስረጃ የመሰብሰብ ኃላፊነት እንደነበረበት ያስረዱት አቶ ሞላ፣ ያ ሳይሆን ቀርቶ እስካሁን በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ማጠናቀቅ ሲችል ለሦስተኛ ጊዜ ቀጠሮ እንዲራዘምለት መጠየቁ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ኤርሚያስ በአክሰስ ሪል ስቴትና -በቤት ገዢዎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታት መንግሥት ዋስትና ሰጥቷቸው ወደ አገር ውስጥ መመለሳቸውን ያስረዱት ያወሱት አቶ ሞላ፤ የተሰጣቸው ዋስትና ሳይወርድ በፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው፣ የነበረውን ችግር ለመፍታት ጫፍ ላይ ያደረሱትን ጥረት ከማክሸፉም በተጨማሪ፣ የመንግሥትን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ተግባር ነው ማለታቸውን የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment