Thursday, February 11, 2016

በጉጂ ዞን በርካታ ሰዎች ቢታሰሩም ተቃውሞው ግን ቀጥሎአል

የካቲት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፍትሃዊ ስርዓት እንፈልጋለን፣ የታሰሩ የህሊና እስረኞች ይፈቱ፣ ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ከአካባቢያችን ይውጣ፣ የተሻለ አስተዳደር ይምጣ የሚሉና በርካታ ጥያቄዎችን በመያዝ የተጠናከረ ተቃውሞ ሲያካሂዱ የሰነበቱት የጉጂ ማህበረሰብ፣ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊሶች እየተደበደቡ ወደ እስር ቤት ቢጓዙም፣ ትግላቸውን ከከተማ ወደ ገጠር በማዞር መቀጠላቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ካለፉት ሁለት ቀናት ጀምሮ አዳዳስ ወታደሮች ወደ አካባቢው የተሰማሩ ሲሆን፣ ህዝባዊ ንቅናቄውን ይመራሉ ያሉዋቸውን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን እና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን ጨምሮ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ37 በላይ ሰዎች ታፍነው ተወስደዋል። ከተያዙት ...መካከል የአካባቢው የሰማያዊ ፓርቲ አደራጅ የሆነው ሙሃመድ ጥላሁን ግርጃ ይገኝበታል።
ትናንት በሃርቃሎ የተካሄደው ተቃውሞ ወደ ዋገራ፣ ሱክራ ቀበሌ የተሸጋገረ ሲሆን፣ በሻኪሶ ቀበሌዎችም ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች እየታዩ ነው።
"በከተማው ውስጥ ያለው ሁኔታ አደገኛ በመሆኑ፣ ትግላችንን ወደ ገጠር ለማዞር ተገደናል" በማለት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የተቃውሞው ተሳታፊ ተናግረዋል።
በኦሮምያ የተጀመረውን ህዝባዊ ተቃውሞ በመሳሪያ ሃይል ለማስቆም የተደረገው ሙከራ አልተሳካም። በክልሉ ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ግምገማዎች እየተካሄዱ መሆኑም ታውቋል።

No comments:

Post a Comment