Thursday, January 10, 2019

ወለጋ ላይ ጦርነት አዲስ አበባ ላይ ሰላማዊ ትግል የሚለው አካሄድ ተቀባይነት የለውም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 2/2011)ወለጋ ላይ ጦርነት አዲስ አበባ ላይ ሰላማዊ ትግል የሚለው አካሄድ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ሲል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዴፓ አስታወቀ።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ ለኢሳት እንደገለጹት በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ በወለጋ ውጊያ እያደረገ በአዲስ አበባ ስለ ሰላማዊ ትግል መናገር አይቻልም ብለዋል።
ሸኔ ኦነግ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ በሶስተኛ ወገን እንደራደር ማለቱን በተመለከተ የፓርቲያቸውን አቋም የገለጹት ዶክተር ዓለሙ ስሜ ከእንግዲህ ድርድር የሚባል ነገር የለም መሳሪያውን አስቀምጦ በምርጫ ቦርድ በሚደረግ የፓርቲዎች ንግግር ላይ መሳተፍ ይችላል ሲሉ ጥሪውን ውድቅ አድርገዋል።

በኦሮሚያ ክልል በወለጋና በጉጂ ሰላም መስፈኑን፣ ሁሉ ነገር ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ህይወት መመለሱን የገለጹት ዶክተር አለሙ ዛሬ በአቶ ገላሳ ዲልቦ ከሚመራው ኦነግ ጋር የተደረገውም ውይይት ውጤታማ እንደሆነ ገልጸዋል።

በብርጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና በግብረ አበሮቻቸው ላይ ክስ ተመሰረተ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 2/2011) በብርጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና በግብረአበርነት በተያዙት የሜቴክ የስራ ሃላፊዎች ላይ ዛሬ በይፋ ክስ መመስረቱ ተሰማ።

በተለያዩ ሰባት የሙስና ወንጀሎች በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 5ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው ብርጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁንዲ፣ረመዳን ሙሳ፣ኮለኔል ደሴ ዘለቀ፣ቸርነት ዳናን ጨምሮ 8 ሰዎች መሆናቸው ተመልክቷል።

Wednesday, January 9, 2019

በመከላከያ ሰራዊት የሚመራ ኮማንድ ፖስት ሊቋቋም ነው

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 30/2011) በኢትዮጵያ በአንዳንድ የሃገሪቱ ክልሎች ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በመከላከያ ሰራዊት የሚመራ ኮማንድ ፖስት በመቋቋም ላይ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሯ ገለጹ።

የሃገር መከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ለፓርላማው ዛሬ እንደገለጹት በክልሎች ጥያቄ ጸጥታ ወደ ደፈረሰባቸው አካባቢዎች የገባው የመከላከያ ሰራዊት የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
ባለፉት 6 ወራት ከ7ሺህ በላይ የሰራዊት አባላት መሰናበታቸውንም ገልጸዋል።
ቦታዎቹ ወይንም ክልሎቹ የትኞቹ እንደሆኑ የመከላከያ ሚኒስትሯ ባይገልጹም በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድንበር እንዲሁም በጉጂ ዞን የመከላከያ ሰራዊት መሰማራቱ ታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ ጋር የጀመረው ውዝግብ መፍትሄ ሳያገኝ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሰራዊት የጸጥታ ችግር ወዳለባቸው አካባቢዎች እንዲሰማራ መደረጉ መንግስት የኦነግን እንቅስቃሴ በሃይል ለማስቆም መወሰኑን ያሳያል ተብሏል።
የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ችግሩን በሰላም ለመቋጨት በርካታ ጥረቶች ማድረጋቸውም ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከመምህራን ጋር ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ውይይት የኦነግን እንቅስቃሴ ለወራት በትዕግስት ሲያዩት መቆየታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
20 እና 30 ዓመታት ምንም ፍሬ በማያፈራ ሁኔታ ውስጥ ካለበት በክብር ያመጣናቸው በኤርትራና በሶማሊያ ያደረጉት የነበረውን ጦርነት ወለጋ ውስጥ እንዲያመጡት አይደለም ማለታቸው አይዘነጋም።
በሌላም በኩል የሃገር መከላከያ ሚኒስትሯ ዛሬ በፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት ባለፉት 6 ወራት 7 ሺህ 17 የሰራዊቱ አባላት መሰናበታቸውን ገልጸዋል።
ተሰናባቾቹም በዕድሜ የማዕረግ ዕድገት ፈተናን ባለማለፍ እንዲሁም በትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛነት የተሰናበቱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በገንዳ ውሃ ከተማ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በትላንትናው ዕለት በከፈቱት ተኩስ ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸው እና 15 መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች ለDW ገለጹ።

 ድርጊቱን በመቃወም ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡት የከተማይቱ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው የሰፈረው የመከላከያ ሰራዊት ከስፍራው ለቅቆ እንዲወጣ ጠይቀዋል። DW Amharic

የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ አንድ የዓይን እማኝ እንደተናገሩት የመከላከያ ሰራዊት አባላት በነዋሪው ላይ ተኩስ የከፈቱት በነዋሪዎች ታግተው የነበሩ የሱር ኮንስትራክሽን ድርጅት ተሽከርካሪዎችን ለማስለቀቅ በሚል ነበር። “የመከላከያ ሰራዊት የእሩምታ ተኩስ ተኩሶ ጉዳት አድርሷል። ባለኝ መረጃ መሰረት ህጻናትን ጨምሮ ወደ 15 ገደማ የሚሆኑ የቆሰሉ ሲሆን የሟቾቹ ቁጥር ዘጠኝ ደርሷል” ሲሉ እኚሁ የከተማይቱ ነዋሪ ተናግረዋል።

የሞቱትም ሆነ የተጎዱ ሰዎች ወደ ገንዳ ውሃ መተማ ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሚናገሩት የዓይን እማኙ ከማቾቹ ውስጥ የስድስት ሰዎችን አስክሬን መመልከታቸውን ገልጸዋል። “እኔ ስድስት ሰዎች ተመልክቻለሁ። እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት እስከነበርኩበት ድረስ ከገንደ ውሃ ከተማ አንዲት ህጻንን ጨምሮ ሶስት ሰዎች፣ ከኮኪት ከተማ ደግሞ ሶስት ሰዎች ነበሩ” ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ከቆሰሉት ውስጥ በእርሻ ስራ ላይ ቆይተው ሲመለሱ የነበሩ የቀን ሰራተኞች አሉበት ብለዋል።

የገንደ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች የመከላከያ ሰራዊትን እርምጃ በመቃወም ዛሬ አደባባይ ወጥተዋል። ከጠዋት እስከ እኩለ ቀን ድረስ በዘለቀው ተቃውሞ ይሰሙ ከነበሩት መፈክሮች ውስጥ “የወህሓት መከላከያ እኛን አይወክልም፤ በፍጥነት ይውጣልን”፣ “በአማራነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ይቁም” የሚሉ እንደሚገኙበት ከሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች አንዱ ተናግረዋል።

ሰልፈኞቹ ትላንት ወደ ኮኪት ከተማ እንዲወሰዱ የተደረጉት የሱር ኮንስትራክሽን ተሽከርካሪዎች ወደ ገንደ ውሃ ከተማ እንዲመለሱ እንዲደረግ እና አስፈላጊውን ማጣራት እንዲደረግባቸው መጠየቃቸውን የከተማይቱ ነዋሪ ገልጸዋል። በተቃውሞ ምክንያት ከአዘዞ እስከ መተማ የሚዘልቀውን አውራ ጎዳና መዘጋቱንም ጨምረው አስረድተዋል። ለተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ምላሽ ለመስጠት የአካባቢው አስተዳደርም ሆነ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች በስፍራው አለመገኘታቸውንም አክለዋል።

Wednesday, January 2, 2019

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጠ

ተቋሙ በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ክልል  የተፈጸመውን ወንጀል አስመልክቶ ተከሰቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ መነሻ ጉዳያቸውን ሲያጣራ ቆይቶ የምርመራ ሥራ መጠናቀቅን አስመልክቶ፣ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ለህግ ታራሚዎች የተሰጠ ይቅርታ እንዲሁም የምህረት አዋጅ ሀገር አቀፍ አፈጻጸም ወቅታዊ መረጃ አሰመልክቶ ታህሳስ 24 ቀን 2011 ዓ.ም በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ፡፡

Tuesday, December 18, 2018

አምዶም ገብረስላሴ ታሰረ

ባለፈው ቅዳሜ በመቀሌ በተካሄደው ስብሳባ አቶ በረከት ስሞኦን እና የሕወሓት ባለስልጣናትን የተቸው አምዶም ገብረስላሴ ታሰረ።
     ለኢሳት በደረሰው መረጃ መሰረትየአረና የሕዝብ ግኑኝነት ሃላፊ አቶ  አምዶም ገብረስላሴ በቁጥጥር ስር የዋለው መቀሌ አክሱም ሆቴል በተባለው አካባቢ ሲሆን፣ሰው ደብድበሃል በሚል  መታሰሩንም  መረዳት ተችሏል።አምዶም  መቀሌ አዲሸንዲህ በተባለ  ቦታ እንደታሰረ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።አምዶም ገብረስላሴ ባለፈው ቅዳሜ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ በተካሄደው  ሰብሰባ የሕወሃትን ባለስልጣናት ሲተች ንግግሩ እንዲቋርጥ መደረጉም ይታወሳል።

Friday, December 14, 2018

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ በተከሰተ ግጭት እስካሁን የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነገረ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ በተከሰተ ግጭት እስካሁን የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነገረ፡፡ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ተብሏል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ አድማሡ ዳምጠው ዛሬ ለሸገር እንደተናገሩት ከትናንት በስትያ አንስቶ በቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ግጭት ተከስቷል፡፡ በግጭቱ እስከ አሁን የ13 ሰዎች ህይወት ማለፉ የተነገረ ሲሆን ከአንድ መቶ የሚበልጡ ደግሞ ቆሰለዋል ተብሏል፡፡ በንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን አቶ አድማሱ ተናግረዋል፡፡