Tuesday, February 16, 2016

በምዕራብ አርሲ በትንሹ አምስት ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች ተገደሉ

ኢሳት (የካቲት 8 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች በወሰዱት የተኩስ እርምጃ፣ በትንሹ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉንና ድርጊቱ ሻሸመኔ ከተማን ጨምሮ በአካባቢው በሚገኙ አነስተኛ ከተሞች ተቃውሞ መቀስቀሱ ተሰማ።
...
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው በፀጥታ ሃይሎችና በነዋሪዎች መካከል በተቀሰቀሰው በዚሁ ግጭት ሰባት የጸጥታ ሃይሎች መሞታቸውን ሜይል ኤንድ ጋርዲያን አፍሪካ የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ማንነታቸው ያልታወቁ አካላት በፀጥታ ሃይሎች ላይ በወሰዱት እርምጃ ግጭቱ ሊቀሰቀስ መቻሉን ተናግረዋል።
ይሁንና የአካባቢው ነዋሪዎች በአካባቢው የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች ሰርገኞችን አሳፍሮ ይጓዝ በነበረ አውቶቡስ ላይ የወሰዱትን የማዋከብና የተኩስ እርምጃ ተከትሎ በስፍራው ግጭት መነሳቱን አስረድተዋል።
በአካባቢው ነዋሪዎችና በፀጥታ ሃይሎች መካከል የተካሄደውን ግጭት ተከትሎም በርካታ ነዋሪዎች ግድያና ድብደባ እንደተፈጸመባቸውም ጋዜጣው አስነብቧል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው በአካባቢው የተቀሰቀሰውን ግጭት ምክንያት ለማወቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ በነዋሪዎች ላይ የደረሰን ጉዳት በዝርዝር ከመግለፅ ተቆጥበዋል።
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ከሁለት ወር በፊት የተቀሰቀሰው ተቃውሞ አሁንም ድረስ በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ማገርሸቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ይኸው ተቃውሞ ከሳምንቱ መገባደጃ ጀምሮ በምዕራብ ሃረርጌ አካባቢ ቀጥሎ የሚገኝ ሲሆን ነዋሪዎች የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱትን የሃይል ዕርምጃ ማውገዛቸውን ታውቋል።
ተመሳሳይ ተቃውሞ በምዕራብና በምስራቅ ሸዋ ከተሞች መቀስቀሱን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው። ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የክልሉና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በነዚሁ አካባቢዎች ሰፍረው የሚገኙ ሲሆን፣ ነዋሪዎችም በጸጥታ ሃይሎች ላይ ተቃውሞ ማቅረባቸው ተነሯል።
ሶስተኛ ወሩን በያዘው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ እስከአሁን ድረስ በትንሹ 150 ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment