Friday, February 5, 2016

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የምስክርነት ቃሉን ሰጠ

ጥር ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ጥፋተኛ ተብሎና 18 አመት እስር ተፈርዶበት በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የመከላከያ ምስክርነት ቃሉን ሰጥቷል፡
ጋዜጠኛ እስክንድር -በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ አንደኛ ተከሳሽ ለሆነው አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ መከላከያ ምስክር ሆኖ ዛሬ ጥር 27/2008 ዓ.ም ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በመቅረብ ምስክርነቱን አሰምቷል።
...
ያለጠበቃ በግሉ የሚከራከረው ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ጋዜጠኛ እስክንድር እንዲያስረዳለት የሚፈልገው ጭብጥ፤ "ጡመራ ምንድነው?፣ ከወንጀል ጋርስ ግንኙነት አለው ወይ? እና ሰብዓዊ መብት እና ዴሞክራሲ ላይ ስልጠና ስለሚሰጡ ድርጅቶችና የስልጠናው ይዘት ምን ይመስላል?" የሚሉትን ነጥቦች እንደሆነ ቢያስታውቅም፤ በጭብጡ ላይ እንዳይመሰክር አቃቤ ህግ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
አቃቤ ህግ ተቃውሞ ያሰማው-"ጡመራ ምንድነው? ወንጀልስ ነው ወይ?" የሚለው፤ በምስክር ሳይሆን በህግ ድንጋጌዎች የሚረጋገጥ ነው በማለት ነው፡፡
ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከሰማ በኋላ ጡመራ ወንጀል ስለመሆን አለመሆኑ የተያዘውን ጭብጥ ውድቅ በማድረግ -ስለ ስልጠናውና አሰልጣኝ ተቋማት የተመዘገበው ጭብጥ ላይ ምስክሩ እንዲመሰክሩ ብይን ሰጥቷል፡፡
ብይኑን ተከትሎ ምስክሩ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ችሎት ፊት የቀረበ ሲሆን በመጀመሪያ በፍርድ ቤቱ የቀረቡለትን ጥያቄዎች መልሷል፡፡
እስክንድር በፍርድ ቤቱ ‹‹ስራ›› ተብሎ ሲጠየቅ፣ ‹‹ጋዜጠኛ ነበርኩ›› ያለ ሲሆን፤ ‹‹አሁንስ?›› ለሚል ተጨማሪ የፍርድ ቤቱ ጥያቄ፦‹‹አሁን የህሊና እስረኛ ነኝ›› ሲል መልሷል፡፡
በማስከተልም ዘላለም ወርቃገኘሁ በዋና ጥያቄ ፦"ተከሳሹ ውጭ ሀገር ሊወስደው ነበር" ተብሎ በክሱ ላይ ስለተጠቀሰው ስልጠና ምስክሩ እንዲያብራሩለት ጠይቋል፡፡ ምስክሩ እስክንድርም ‹‹ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገራትንም የሚያሳትፍ ስልጠና በሰብዓዊ መብት፣ በሚዲያ ‹ኢቲክስ›፣ እና በዴሞክራሲ ላይ ይሰጣሉ፡፡ ድርጅቶቹ የተለያዩ ቢሆንም በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ መርሃቸው ተመሳሳይና ዓለም አቀፍ ነው›› በማለት መስክሯል፡፡
ድርጅቶቹን በስም መጥቀስና የሚገኙበትንም ሀገር ለፍርድ ቤቱ መግልጽ ይቻል እንደሆነ ምስክሩ ተጠይቆ ‹‹የተቋማቱ መገኛ ምዕራቡ ዓለም ነው፡፡ በዴሞክራሲ የዳበሩ ሀገራት ነው ዋና መቀመጫቸው፡፡ ሲ.ፒጄ፣ ፍሪደም ሀውስ፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል እና አርቲክል 19 የመሳሰሉትንም በስም መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኔም ከነዚህ ተቋምት ውስጥ በአንዱ የተሰጠ ስልጠና አዲስ አበባ ላይ ተካፍየ ነበር፡፡ ስልጠናው ስለ ሰብዓዊ መብት፣ ስለ ሚዲያ፣ ስለ ዴሞክራሲ የሚያስተምር ነው፡፡ ስልጠናው ከሽብር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ ይህ እንደማስረጃ መቅረቡ ኢትዮጵያን ትዝብት ውስጥ የሚከትና የሚያሳዝን ነው›› ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መቼ እንደታሰረ በመስቀለኛ ጥያቄ ተጠይቆ ‹‹መስከረም 2004 የሀሰት ክስ ቀርቦብኝ፣ በግፍ ተፈርዶብኝ ታስሬ እገኛለሁ›› ሲል መልሷል፡፡ እስክንድር ነጋ ጥቁር ሱፍ በደብዛዛ ሸሚዝ ለብሶ፣ ሙሉ ጥቁር መነጸር አድርጎና ነጠላ ጫማ ተጫምቶ ችሎት ፊት መቅረቡን የነገረ-ኢትዮጰያ ዘገባ ያመለክታል።
አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ምስክሩ ምስክርነቱን ማጠቃለሉን ተከትሎ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡለት የጠራቸው ሌላኛው ምስክር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በተደጋጋሚ ባለመቅረባቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ከመጠየቁም ባሻገር አቶ አንዳርጋቸው እስካሁን አለመቅረባቸው መንግስት እርሳቸውን ለማቅረብ ፍላጎት እንደሌለው ያሳያል ሲል ቅሬታውን አሰምቷል፡፡
አክሎም፦ ‹‹አሁን የተረዳሁት ነገር ከሳሼ የሆነው መንግስት አቶ አንዳርጋቸውን ከሚያቀርብ እኔን በነጻ መልቀቅ እንደሚቀለው ነው›› ብሏል ተከሳሽ ዘላለም ወርቃለማሁ።
ተከሳሹ ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እንደተገናኜ አቃቤ ህግ መጥቀሱን በማስታወስ ምስክሩ መቅረባቸው ያለውን ተገቢነት አስረድቷል፡፡ ‹‹ምስክሩ እንዲቀርቡልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ፍርድ ቤቱ ከምስክሩ ጋር በተገናኘ ያለውን የክሱ ፍሬ ነገር አውጥቶ በቀሪው ላይ ብይን ይስጥልኝ›› ብሏል ተከሳሹ አቶ ዘላለም፡፡
ፍርድ ቤቱም ምስክሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት ምስክርነታቸውን ለመስማት በሚል ለየካቲት 16/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
See More

No comments:

Post a Comment