Monday, February 1, 2016

በጋምቤላ የሚደረገው የጦርነት ዝግጅት አሳሳቢ ሆኗል

ከጋምቤላ ከተማ በ45 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ኢታንግ ወረዳ መሳሪያ የታጠቁ የአኝዋክና የኑዌር የልዩ ሃይል ኣባላት እርስ በርስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት ከሁለቱ ሃይሎች ጋር ለጦርነት እየተዛጉ መሆኑን ከክልሉ የደረሰን አስተማማኝ መረጃ አመልክቷል። የክልሉ ፕሬዚዳንትና ምክትሉ በወታደራዊ ቁጥጥር ስር እንዲዉሉ የተደረገ ሲሆን፣ የኢታንግ ወረዳ አስተዳዳሪዎችም በተመሳሳይ መንገድ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላት በዋና ከተማዋ የሚገኙ የአኝዋክና ንዌር ተወላጅ የልዩ ሃይል ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት በተለያዩ ቦታዎች አግተው ያስቀመጡዋቸው ሲሆን፣ በኢታንግም እንዲሁ አንድ ሻምበል ጦር የኑዌር የልዩ ሃይል አባላትን ትጥቅ አስፈትቶ በቁጥጥር ሲያውል፣ የአኝዋክ የልዩ ሚሊሺያ አባላት ...ግን ትጥቅ አንፈታም በማለት ባሮን ወንዝ ተሻግረው መስፈራቸውን፣ ከሁለቱም ወገን ታጣቂዎች የተወሰኑት ጨካ መግባታቸውን ምንጮች ገልጸዋል። እነዚህ ሃይሎች እርስ በርስ እየተታኮሱ ነው።
የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከእነዚህ ሃይሎች ጋር ለመዋጋት ትእዛዝ እየጠበቁ መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ ጦርነቱ በአኝዋክና በንዌር የልዩ ሃይል አባላት ፣ በአኝዋክና በመከላከያ እንዲሁም በኑዌርና በመከላከያ መካከል በማንኛውም ጊዜ ሊካሄድ ይችላል ብለዋል።
በተለያዩ የስደተኛ ካምፖች የሚገኙ የንዌር ተወላጆች እንዲሁም በከተማዋ የሚገኙ የአኝዋክና የንዌር ተወላጆች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመሄድ መሰባሰብ መጀመራቸው አካባቢውን አስፈሪ አድርጎታል በማለት ምንጮች ተናግረዋል።
በወረዳው 2 የኑዌር የልዩ ሃይል አባላት መገደላቸው ታውቋል።
በርካታ ቤቶችም ተቃጥለዋል። የአጋዚ ጦርና ሌሎች የመከላከያ ሰራዊት አባላት ክልሉን ተቆጣጥረው እያስተዳደሩ ሲሆን፣ ዜጎች ከቤት እንዲወጡ አልተፈቀደላቸውም። ባንኮች፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተዘግተዋል።
ምንጮች እንደገለጹት አሁን የተፈጠረው ችግር ከግል ጸብ ጋር በተያያዘ የተቀሰቀሰ ቢሆንም፣ አጠቃላይ የችግሩ መነሻ ግን ከስልጣን እና ከአስተዳደር መበላሸት ጋር የተያያዘ ነው። የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት ኑዌር ሲሆኑ፣ ምክትላቸው ኢንጂነር ኦሌሮ ኦፒዩ አኝዋክ ናቸው። ዋናው ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተወለዱና ከስደኛ ካምፕ ወጥተው የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸውን አኝዋኮች አይቀበሉትም። ስልጣን መያዝ ያለበት የኢትዮጵያ ተወላጅ መሆን ሲገባው፣ መንግስት ግን ለውጭ አገር ዜጋ ስልጣን ሰጥቷል በማለት አኝዋኮች የፕሬዚዳንቱን ሹመት ይቃወሙታል። በሌላ በኩል ደግሞ የሁለቱም ብሄረሰቦች በተለይም ከጋምቤላ ከተማ እየተገፉ መውጣታቸውና መሬታቸውን መቀማታቸው የፈጠረባቸው ድህነት ብሶታቸ እንዲጨምር አድርጓል ይላሉ።
ክልሉን የመከለከያ ሰራዊት አባላት እያስተዳደሩ መሆኑ፣ ከህግ አንጻር ጥያቄ እያስነሳ ነው። ክልሎች እውነተኛ ስልጣን እንደሌላቸው በጋምቤላ ያለው ሁኔታ ጥሩ ማሳያ ነው የሚሉት ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ወገኖች፣ በጋምቤላ ከተማና በኢታንግ ያሉ መሪዎች በሙሉ በቁጥጥር ስር በመዋላቸው ክልሉ እንደፈረሰ ይቆጠራል ይላሉ።

No comments:

Post a Comment