Saturday, October 31, 2015

አይኔ አያየ እዚህ ዉስጥ አልገባም – መሠረት ሙሌ (ኤፍሬም ማዴቦ ከአርበኞች መንደር)


ኤፍሬም ማዴቦ ከአርበኞች መንደር
መብራቱን አጥፍቼዉ አልጋዬ ላይ የወጣሁት በግዜ ነዉ። አለወትሮዬ እንቅልፍ የሚባል ነገር በአይኔ አልዞር ብሎኝ ከጨለማዉ ጋር ፊት ለፊት ተፋጥጠናል። የነፋስ ሸዉታ እንኳን የማይሰማበት ደረቅ ሌሊት ነዉ። ጨላማዉ አይን ይበሳል። እቤቱ ዉስጥ ያለዉ ሰዉ ሁሉ ተኝቷል። ቀኑን በሠላም ላዋለኝ አምላክ ምስጋና ሰጥቼ ሌሊቱንም አደራ ብዬዉ ፀሎቴን ጨረስኩ። ያ ምቀኛ እንቅልፍ ግን አሁንም እንደከዳኝ ነዉ። ትንሿ አልጋዬ ላይ ግራ ቀኝ እያልኩ ተገለባበጥኩ። እንቅልፍ ተጎትቶ የሚመጣ ይመስል አሁንም አሁንም ላይ ታች እያልኩ አልጋዉ ላይ እራሴን ጎተትኩት . . . እንኳን እንቅልፍ ሊወስደኝ ጭራሽ አይኖቼ መርገብገባቸዉን ያቆሙ ይመስል ቀጥ ብለዉ ቀሩ። ከተጋደምኩበት ብድግ ብዬ መብራቱን አበራሁና ለመንገድ ከያዝኳቸዉ ሁለት መጻህፍት አንዱን አዉጥቼ ማንበብ ጀመርኩ። እኔ ላንብበዉ ወይ መጽሀፉ ያንብበኝ አላዉቅም። ጧት ስነሳ ግን “The Architecture of Democracy” የሚል መጽሐፍ ደረቴ ላይ ተለጥፎ ነበር። ሰዐቴን ሳየዉ ከሌሊቱ ስምንት ሰዐት ተኩል ይላል። ከአልጋዬ ላይ ዘልዬ ወረድኩና ሰዉነቴን ታጥቤ ልብሴን ከለበስኩ በኋላ መኪናዉ ዉስጥ ገብቼ “I’m ready” አልኩ። የመኪናችን መብራት ጨለማዉን እየገላለጠዉ የአስመራ ከረንን መንገድ ተያያዝነዉ። መኪናዉ ዉስጥ ከገባሁ በኋላ እንደገና አፌን የከፈትኩት ባሬንቱ ደርሰን ቁርስ ሳዝ ነዉ። ባሬንቱ በግዜ መድረሳችን ደስ ቢለኝም የቀረን መንገድ ርዝመት ታየኝና ቁርስ መብላቴን ትቼ . . . በሰዐት ይህን ያክል ብንጓዝ እያልኩ ዋናዉ ጉዳያችን ቦታ የምንደርስበትን ሰዐት ማስላት ጀመርኩ። የስሌቱ ዉጤት ከሦስት ሰዐት ሲበልጥብኝ ተናደድኩ። ቀሪዉ መንገድ ገና ሳልጀምረዉ ሰለቸኝ። በተፈጥሮዬ መንገድና መኃላ ሲረዝም አልወድም።

የህወሓት አገዛዝ የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት የነበሩትን እየለቀመ ከመከላከያ ኃይሉ እያባረራቸው መሆኑ ታወቀ፡፡

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ)
የህወሓት አገዛዝ የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት የነበሩትን እየለቀመ ከመከላከያ ኃይሉ እያባረራቸው መሆኑ ታወቀ።
ህወሓት በ1983 ዓ.ም መላ አገሪቱን በነፍጥ እንደተቆጣጠረ በሁለት ያለፉ የኢትዮጵያ መንግስታት ከፍተኛ የህዝብ ሀብት፣ ዕውቀትና ጉልበት ፈሶበት ለዘመናት በስንት ልፋትና ጥረት
የተገነባውን የአገር መከላከያ ሰራዊት ባደረበት ጭፍን ጥላቻና ቂም ብቻ ተመስርቶ "የደርግ ነው" በሚል ሰበብ ባንድ ጀምበር ንዶ ማፈራረሱን አገር ያወቀው ፀሃይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ከበረሃ የመጡ ድኩማን ታጋዮቹን ለሙያው የሚመጥን ምንም አይነት ዘመናዊ ዕውቀት ሳይኖራቸው የጀነራልነት ማዕረግ በማሸከም በአየር ኃይሉና በምድር ኃይሉ ውስጥ በሚገኙ የአዛዥነት ቦታዎች ላይ እነሱን ብቻ አስቀምጦ ስልጣኑን ለመጠበቅ ብቻ እንዲተጉለት በማድረግ የአገራችንን ብሄራዊ
ደህንነት አደጋ ላይ ጥሎት ይገኛል፡፡

Friday, October 30, 2015

በሶማሊ ክልል ዜጎች በረሃብ መፈናቀላቸውን የአለም የምግብ ድርጅት አስታወቀ

ጥቅምት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአለም የምግብ ድርጅት በእንግሊዝኛው ( FAO) ተወካዮች በዚህ ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝን አንድ የመጠለያ ካምፕ ከጎበኙ በሁዋላ ባወጡት መግለጫ፣ በአንዳንድ ወረዳዎች 95 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በረሃቡ ምክንያት አካባቢውን ለቆ ተሰዷል።

እጅግ በርካታ የቤት እንስሳት መሞታቸውን ይፋ ያደረገው ድርጅቱ፣ አሁንም ከፍተኛ የምግብ እጥረት በማጋጠሙ በተለይ ህጻናት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዱ ነው። በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙት 1 ሺ 400 ቤተሰቦች ባለፈው ግንቦት እና ሰኔ ወር መምጣታቸውን የገለጸው የምግብ ድርጅቱ፣ አብዛኞቹ እንስሶሳቸው የሞቱባቸው ከመጋቢት ወር ጀምሮ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮንሶ በርካታ ወጣቶች ታሰሩ

ጥቅምት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከትናት ጀምሮ የአርበኞች ግንቦት7 አባሎች በሰገን ዞን ኮንሶ ወረዳ ውስጥ ገብተዋል በሚል የፖሊስ አባላት በከተማው የሚገኙ ወጣቶችን ሲያድኑ ከዋሉ በሁዋላ ፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወጣቶችን ይዘው አስረዋል።

በአካባቢው ሰሞኑን በፖሊስ አባላት ላይ የተፈጸመ የተባለ ጥቃትና ወጣቱን የሚያነሳሱ በራሪ ወረቀቶች መበተናቸው ለአሰሳው ተጨማሪ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክርቤት አባል መመረጧ ተወገዘ

ጥቅምት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሚፈጽሙት አገራት ውስጥ ጋዜጠኞችን በማሰር፣ ሰላማዊ የዴሞክራሲ ሽግግር እንዳይፈጠር ከሚያደርጉ በቀዳሚነት ተርታ የምትገኘው ኢትዮጵያን ጨምሮ ቡሩንዲ፣ቬንዚዌላ፣አረብ ኤምሬትስ፣ቶጎ፣ ታጃኪስታን ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባል ሆነው መመረጣቸው የስብዓዊ መብት ተሟጓቾችን ጨምሮ የእስራኤል መንግስት ማውገዛቸውን ዴሊ ኒውስ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶች በየአመቱ በሰብአዊ መብት ጥሰት ትወነጀላለች።

በደቡብ አፍሪካ ስደተኞች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ተፈጸመ

ጥቅምት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚኖሩ ስደተኞች ላይ ኢላማውን ያደረገው ባለፈው ዓመት ተፈፅሞ የነበረው ዘግናኝ ግድያና ዘረፋ በግርሃምስቶን ከተማ ውስጥ ማገርሸቱ ተገልጿል።

የራሳቸውን አነስተኛ ሱቆች ከፍተው የሚተዳደሩና በተቀጣሪነት የሚሰሩ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን፣ሶማሊያዊያን፣ ባንግላዴሻዊያን፣የፓኪስታናዊያን ከ500 በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦች ከዕለተ ሰኞ ጀምሮ ከስራ ቦታቸው ላይ ንብረታቸው እየተዘረፉ አካላዊ ጥቃቶች እንደተፈጸሙባቸውና በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል።
የስራአጦች ንቅናቄ በመሩት የዘረፋ መርሃግብር ላይ የከተማዋ የታክሲ ማኅበር አባላትም ተባባሪ በመሆን”የታክሲ አሽከርካሪዎች ለቃችሁ ካልወጣችሁ መኪኖቻችሁን እናቃጥላለን’ የሚል መፈክሮችን በመለጠፍ ከዘራፊዎቹ ጎን መቆማቸውን አሳይተዋል።
የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ያሉ ሲሆን የከተማዋ ከንቲባ በጠሩት ስብሰባ ላይ የፖሊስ አባላት አለመገኘታቸው ጉዳዩን ይበልጥ ውስብስብ እንዳደረገው ኦፒንየን ራዲዮ አክሎ ዘግቧል።

ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ቢሮ 16 የደህንነት አባላት እና አመራሮችን በስውር በቁጥጥር ስር ሊያውል ዝግጅት መጀመሩን ተጋለጠ።

ሚስጥራዊ መረጃው እንደሚያመለክተው ከሆነ በዛሬው እለት የተቋሙ ጀነራል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጌታቸው አሰፋ ዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጎን በሚገኘው ቢሮአቸው የተቋሙን ከፍተኛ አመራሮችን ትዕዛዝ ለመስጠት መሰብሰባቸውንና በስብሰባውም ዳይሬክተሩ ተቋሙ ከጥቂት ወራቶች በፊት ብዛት ያላቸው አዳዲስ አባላትን መቅጠሩን እና ወደ ስራ ማሰማራቱን አስታውሰው ነገር ግን በውስጣቸው ሴራ ይዘዉ በተቋማችን ለበርካታ አመታት ተሰግስገው ሲሰሩ የነበሩ 6 አመራሮች እነዚህን አዳዲስ አባላትን በተለያየ ጊዜ በሥውር በመሰብሰብና አቅጣጫዎችን በመስጠት መንግስት የደሞዝ ጭማሪ እንዲያደርግ እና የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን እንዲጨመርላቸው ጥያቄ እንዲያነሱና ጫና እንዲያደርጉ አነሳስተዋል ያሉ ሲሆን አባላቱም እሔን ጥያቄና አቅጣጫ በመያዝ በየተመደቡበት መምሪያ እና የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ጋ በመሔድ አቅርበው ነበር::

Thursday, October 29, 2015

10 የፌ. ፖሊስ አባላት ኮንሶና ቦረና መገንጠያ ድልድይ ላይ ከነመኪናቸው ተደመሰሱ ሲል አርበኞች ግንቦት 7 ድምጽ ዘገበ


እንደ ራድዮው ዘገባ በትናንትናው ዕለት አመሻሽ ላይ አስሩ የፌደራል ፖሊሶች መጀመሪያ አንድ አይሱዙ የጭነት መኪና በኃይል በማስገደድ አስቁመው የተሳፈሩ ሲሆን መኪናው መንቀሳቀስ ሲጀምር “የጫንካቸውን ፖሊሶች አራግፍ አለያ ከነንብረትህ አብረህ ትጋያለህ!” የሚል የስልክ ማስጠንቀቂያ መልዕክት ለአሽከርካሪው በመድረሱ አሽከርካሪው መኪናውን አቁሞ ፖሊሶቹን “አልሄድም” ይላቸዋል፡፡ ቀጥሎም ፌደራል ፖሊሶቹ ሾፌሩን ለማንገራገር ሞክረው ትዕዛዛቸውን በቀላሉ ሊቀበል ባለመቻሉ ስልክ ተደዋውለው ሌላ ላንድ ክሩዘር መኪና እንዲመጣላቸው በማድረግ ተሳፍረው ጉዟቸውን ቀጥለው ኮንሶ እና ቦረና መገንጠያ ድልድይ ላይ ሲደርሱ ቅፅበታዊ ጥቃት ተከፍቶባቸው ከነተሳፈሩበት መኪና ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል ብሏል የአርበኞች ግንቦት 7 ድምጽ:: ራድዮው ዘገባውን በመቀጠል የአርባ ምንጭ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ባለው የልዩ ኃይል እና የፌደራል ፖሊስ ጦር ተወራ ጓዳ ጎድጓዳዋ ሳይቀር እየታሰሰ ነው ብሏል:: ራድዮው እንደሚልው እየተፋፋመ ያለው የፀረ-ወያኔ ትግል እየተካሄደባቸው ከሚገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ከተሞች አንዷ አርባ ምንጭ መሆኗ እና በህወሓት የደህንነት ተቋም ጥርስ ውስጥ ገብታ አገዛዙ በአዓይነ ቁራኛ እየተከታተላት የምትገኝ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ከሰሞኑ ደግሞ አርበኞች ግንቦት 7 አንድ አይሱዙ ሙሉ የጦር መሳሪያ ወደ ከተማዋ አስገብቷል በሚል የህወሓት ልዩ ኃይሎች፣ ፌደራል ፖሊሶችና ደህንነቶች በየመንደሩ ተሰራጭተው ከፍተኛ አሰሳ እያደረጉ የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት የህይወት እንቅስቃሴና ሰላም በማወክ ላይ ናቸው፡፡ በተያያዘ ዜና ሙሉጌታ አባ፣ ፀጋዬ ገብረ ፃድቅ እና በኃይሉ ሲሳይ የተባሉ የህወሓት ጆሮ ጠቢዎችና የአካባቢው ቆራጭ ፈላጮች ፎቶግራፋቸው በማህበራዊ ሚዲያው መሰራጨቱን ተከትሎ ከትናንት ምሽት ጀምሮ አርባ ምንጭ ከተማ ከከዚህ ቀደሙ በባሰ ሁኔታ በፌደራል ፖሊስ ተጥለቅልቃ እየታመሰች ትገኛለች ሲል ራድዮው ዘግቧል:: ይህን ዜና የሚያስተባብል መረጃ ከመንግስት በኩል እስካሁን የተሰጠ ነገር የለም:: ዘ-ሐበሻ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገችው ሙከራም አልተሳካም::

እነ ሀብታሙ አያሌው ለጥቅምት 22 ተቀጠሩ

᎐ማረሚያ ቤት እነ ሀብታሙን አላቀረባቸውም
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ የተበየነላቸው የአንድነት፣ የሰማያዊ እና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች ላይ አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆ ጉዳያቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት አምስት ተከሳሾች ለጥቅምት 22/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡ 
ዛሬ ጥቅምት 17/2008 ዓ.ም የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ማረሚያ ቤት ሳያቀርባቸው በሌሉበት ቀጠሮ የተሰጣቸው የፓርቲዎች አመራሮቹ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና አብሯቸው ይግባኝ የተጠየቀበት አብርሃም ሰለሞን ናቸው፡፡ 
የቂሊንጦ እና የቃሊቲ ማረሚያ ቤቶች እነ ሀብታሙን ፍርድ ቤት ያላቀረቡበትን ምክንያት ፍርድ ቤቱ ሲጠይቅ፣ ‹‹ቃሊቲ በፕላዝማ ይታያል ስለተባለ አላመጣናቸውም፤ ከአይ.ሲ.ቲ ጋር ተነጋግረው ነው ያስቀሯቸው›› የሚል መልስ ተሰጥቷል፡፡ ማረሚያ ቤቱ እነ ሀብታሙን ብቻ ሳይሆን በሌላ መዝገብ በተለያዩ ወንጀሎች ስር የተጠቀሱ ተከሳሾችንም አለማቅረቡ ታውቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የቃሊቲ ማረሚያ ቤትን መልስ ካደመጠ በኋላ፣ ‹‹ይሄ ቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚባል ነገር የሚሆን አይደለም፤ አቅርቧቸው ብለን አዝዘን ነበር፤ እኛ ነን የምናዝዛችሁ ወይስ ማን ነው? አሁንም ቀጣይ ቀጠሮ ላይ አቅርቧቸው›› ሲል በእነ ሀብታሙ መዝገብም በሌሎች መዝገቦችም ላይ ዛሬ ላልቀረቡ ተከሳሾች ተመሳሳይ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም እነ ሀብታሙ አያሌው ሰኞ ጥቅምት 22/2008 ዓ.ም የተጠየቀባቸው ይግባኝ ያስቀርባል ወይስ አያስቀርብም የሚለውን ብይን ቀርበው ለመስማት ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡

16 died, 12 injured in Ethio-Sudanese border conflict

ESAT (October 29, 2015)
Sudan Tribune reported on Thursday October 29, 2015 that ongoing clashes at the Ethio-Sudanese border in El-Gadaref state claimed the lives of at least 16 Sudanese nationals.
12 more people were wounded and 7 others were kidnapped during the clash, the report obtained from Sudan Tribune indicated. In addition, more than 300 cattle were also looted from Sudanese farmers.
Former Chief of Staff of the Sudanese Army and Current Interior Minister Esmat Abdel-Rahman told Sudanese Parliamentarians that armed Ethiopians attacked Sudan

በጋምቤላ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ሁለት ሰራተኞችን ገደሉ

ጥቅምት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኑዌር ዞን ዋና ከተማ ከሆነቸው ንያንግ 30 ኪሜ ራቅ ብሎ በሚገኘው የህንዱ ካራቱሪ ኩባንያ አጠገብ በሚገኘው አንዱራ የአነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ዙሪያ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የደቡብ ዲዛይንና ግንባታ ሲፐርቪዥን ኢንተርፕራይዝ ሰራተኛ የሆኑት ኢንጂር ሙሉጌታ ደሳለኝ እና የጋምቤላ የእርሻ ቢሮ ሰራተኛ የነበሩት ወ/ሮ ሃይማኖት ተገድለዋል። የሁለቱም ሰዎች አስከሬን ማታ ወደ አዲስ አበባ ተልኮ በሚኒሊክ ሆስፒታል ምርምራ ከተደረገበት በሁዋላ፣ የኢንጂነር ሙሉጌታ አስከሬን ወደ ነቀምት፣ የወ/ሮ ሃመልማል ደግሞ ወደ ናዝሬት ተልኳል።የአካባቢው ሰዎች እንደሚናገሩት ግድያው የተፈጸመው ከመሬት መቀራመት ጋር ተያይዞ ያካባቢው ነዋሪዎች በየጊዜው ከሚያነሱት ተቃውሞ ጋር የተያያዘ ነው።

በዚሁ ፕሮጀክት አካባቢም ከወራት በፊት ማቲያስ ዘነበ የሚባል ሰራተኛ ተገድሏል።

16 ዜጎቼ በኢትዮጵያውያን ታጣቂዎች ተገደሉብኝ ስትል ሱዳን አስታወቀች

ጥቅምት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ገዳሪፍ አቅራቢያ በተቀሰቀሰ ውጊያ 16 ሱዳናዊያን መገደላቸውን፣ 12 መቁሰላቸውን እንዲሁም 7ቱ ታግተው መወሰዳቸውንና የደረሱበት እንደማይታወቅ ከ300 በላይ የቁም ከብቶችም መዘረፉን የቀድሞው የአገሪቱ ጦር አዛዥና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ለፓርላማ ሪፖርት አቅርበዋል።

ኢስማት አብዱረሕማን ” ሽፍቶች” ያሉዋቸው መሬታችንን አሳልፈን አንሰጥም ያሉ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ለፓርላማው ከተናገሩ በሁዋላ፣ የፓርላማ አባላቱ በመልሱ በአካባቢው የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት በብዛት እንዲሰፍርና በሱዳናውያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲያስቆም ጠይቀዋል።የገዳሪፍ አካባቢ የፓርላማ ተወካይ የሆኑት ኢስማኤል አህመድ ሙሳ በበኩላቸው ከ794 ኪሎ ሜትር በላይ የሆነ መሬት የኢትዮጵያ ገበሬዎች በኃይል ወስደውብናል በማለት ለፓርላማው ተናግረዋል።
የኢህአዴግ መንግስት ሰፊ የሆነ ለም መሬት ለሱዳን አሳልፎ ከሰጠ በሁዋላ፣ በኢትዮጵያ አርሶአደሮችና በሱዳን ታጣቂዎች መካከል በተለያዩ ጊዜዎች ግጭቶች ተከስተው ከሁለቱም ወገን ሰዎች አልቀዋል። ቀድም ብሎ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሱዳን ድረስ በመሄድ “ድንበሩ በቅርቡ እንደገና ይካለላል” በማለት ተናግረው የነበሩ ቢሆንም፣ የድንበር ከተማ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉትን ተቃውሞ በመፍራት እስካሁን ተግባራዊ አላደረጉትም። ሱዳኖችም በየጊዜው ” አለን የሚሉት መሬት እንዲሰጣቸው የኢህአዴግን መንግስት እየጠየቁ ነው። የአካባቢው አርሶደሮች በበኩላቸው ” ሱዳን እንኳንስ ተጨማሪ መሬት ሊገባት፣ ከኢህአዴግ በገጸ በረከት የተበረከተላትን መሬት ካልመለሰች ግጭቱ አይቆምም” ይላሉ።
በቅርቡ የሱዳን ታጣቂዎች ስምንት ኢትዮጵያዊያንን ስራ ትቀጠራላችሁ በሚል አታለው በመውሰድ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል።
ሱዳን ከኢህአዴግ መንግስት ጋር በቅርበት በመስራት ፣ የኢህአዴግን አገዛዝ የሚቃወሙትንና በአገሯ ስደት የጠየቁ በርካታ ኢትዮጰያውያንን አሳልፋ ሰጥታለች።

አርባምንጭ በፌደራል ፖሊስ አባላት ስትታመስ ዋለች

ጥቅምት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት የአርባምንጭ ምንጮች እንደተናገሩት በቅርቡ የአርበኞች ግንቦት 7 ደጋፊዎች ኢህአዴግን የሚያወግዙና ወጣቱ ለመብቱ እንዲነሳ የሚቀሰቅሱ በራሪ ወረቀቶችን ከበተኑ በሁዋላ፣ ድርጊቱን ፈጽመዋል ብለው የጠረጠሩዋቸውን ወጣቶች በጅምላ ለማሰር ከትናንት ጀምሮ አሰሳ አካሂደዋል።

አሰሳውን ተከትሎ የ70 አመት አዛውንት እናትን ጨምሮ ሴቶችና ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወጣቶች ተይዘዋል። ከተያዙት መካከል የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪ እንደሚገኙበት ምንጮች ገልጸዋል። አቶ ሉሉ መሰለ እስከ ባለቤታቸውና ልጃቸው ተይዘው፣ ልጃቸውና ባለቤታቸው ሲለቀቁ እርሳቸው ታስረዋል፡፤ ቀደም ብሎ ቂልንጦ ተወስዶ የታሰረው የአቶ ፈቃዱ አበበ እናት ወ/ሮ አልማዝ ካሳና እህቱ አየለች አበበም እንዲሁ ” ተፈላጊ ልጃቸውን ባንተወሰን አበበን አምጡ” ተብለው ታስረዋል።
ወጣት ባንተወሰን አበበ ፣ በአጋጣሚ ቤት ውስጥ ባለማደሩ አለመያዙንና እናትና እህቱን አስረው መውሰዳቸውን እንዲሁም ከቤታቸው ተገኝቷል የተባለ መረጃ ፈርሙ ተብላ እህቱ ስትጠየቅ አልፈርምም ማለቱዋን ለኢሳት ገልጿል።

በሰቆጣ ከፍተኛ የውሃ ችግር ተፈጥሯል

ጥቅምት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ነዋሪዎች እንደሚሉት ከድርቁ ጋር ተያይዞ የውሃ ችግሩ በመባባሱ ፣ ህዝቡ ውሃ ለማግኘት በእጅጉ ተቸግሯል።

የውሃ ችግሩ በመባባሱና በየአካባቢው የሚታየው የውሃ ጀሪካም ብዛት ” ሳምንቱን ” ቢጫው ሳምንት” አስብሎታል በማለት ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የውሃ ችግሩ ከሰቆጣ በተጨማሪ በተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች ይታያል።
በሌላ በኩል ደግሞ ክልሉን እመራዋለሁ የሚለው ብአዴን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በማውጣት በአሉን ለማክበር እንቅስቃሴ ላይ ነው። ከዚሁ በአል ጋር ተያይዞ ለብአዴን ገንዘብ አናዋጣም ያሉ ነጋዴዎች ክትትል እየተደረገባቸው ነው።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አብዴን አባላት እንደገለጹት፣ያለፍላጎታቸው መዋጮ እንዲያወጡ ተጠይቀው ፈቃደኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች፣ ፋይላቸው ወደ ገቢዎች ቢሮ እየተላለፈና ክትትል እየተደረገባቸው ነው። በነጋዴዎቹ ላይ የሃሰት ወንጀል በማዘጋጀት የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ተብሎ እየተሰራ መሆኑን ነጋዴዎች ይገልጻሉ። አባላቱ እንደሚሉት የአብዴን አባላት ወደ አንዳንድ ነጋዴዎች ቤት በመሄድ ገንዘብ ሲቀበሉ ደረሰኝ አይሰጡም።

Wednesday, October 28, 2015

ቴፒ በተኩስ ስትናወጥ አመሸች

ጥቅምት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ፣ “የአመጹ ወጣቶችን አጋልጡ” በሚል የመከላከያ ሰራዊት አባላት በግለሰቦች ቤት እየገቡ አዛውንቶችን፣ ወጣቶችንና ሴቶችን እየደበደቡ ሲያስሩ ከሰነበቱ በሁዋላ ትናንት ከምሽቱ ሶስት ሰአት ጀምሮ፣ ከጫካ በመጡ ወጣቶችና በመከላከያ ፖሊስ አባላት መካከል ለሰአታት የቆየ የተኩስ ልውውጥ ተካሂዷል።

ኢሳት ከተለያዩ ነዋሪዎች ባደረገው ማጣራት ከቴፒ 7 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቆርጫ ህብረት ፍሬ ቀበሌ ማምሻውን ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ተካሂዷል። አንድ የአይን እማኝ እንደተናገሩት ፣ ሰሞኑን እንደገና በብዛት የሰፈሩት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ህብረት ፍሬ በሚባል ቀበሌ የሚገኙ ሴቶችን ” ሽፍቶችን የምትቀልቡት እናንተ ናችሁ አውጡ” በማለት ሲደብድቧቸው ፣ መረጃ የደረሳቸው ወጣቶች ፈጥነው በመድረስ ባደረሱት ጥቃት 14 ወታደሮች መገደላቸውንና ከወጣቶች መካከልም 2ቱ መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ነዋሪዎች እንደሚሉት የወታደሮች አስከሬን ሌሊት ላይ በ4 መኪኖች ተጭነው ሲወሰዱ ፣ የወጣቶችን አስከሬን ግን ህዝቡ መቅበር እንዳልቻለ ገልጸዋል

እነ አቶ ደህናሁን ቤዛ ፍርድቤቱን በአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ አስጨንቀውታል

ጥቅምት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ በሽብረተኝነት ወንጀል የተከሰሱት አቶ ደህናሁን ቤዛና አቶ ምንዳዬ ጥላሁን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ቀርበው እንዲመሰክሩ ፍርድ ቤቱ ለተለያዩ አካላት ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው ለልደታ ፍርድ ቤት 19ኛው ወንጀል ችሎት በድጋሜ ደብዳቤ ጽፈዋል።

ቃሊቲ እስር ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፣ ቃሊቲ አለመታሰራቸውን ጥቅምት 12 ፣ 2008 ዓም ለፍርድ ቤቱ ጠቅሶ የነበረ ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ ግን የቃሊቲን እስር ቤት ምክንያት ባለመቀበል ፍርድ ቤቱ ለተለያዩ አካላት ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው ጠይቀዋል።
ነገረ ኢትዮጵያ በለቀቀው የጽሁፍ ማስረጃ፣ እስረኞቹ ” የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን መያዙን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንክ ኮርፖሬት መግለጫ መስጠቱን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ መስከረም ወር 2007 ዓ.ም የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን መያዝ፣ የእድሜ ልክና የሞት ፍርደኛ መሆናቸውን በመግለፅ የኢትዮጵያ መንግስት ፍርዱን ተፈፃሚ እንደማያደርግ መግለፃቸውን እንዲሁም በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ አቶ አንዳርጋቸው ዜግነታቸው እንግሊዛዊ በመሆኑ ክትትል እንደሚያደርግ ” በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቱ ለእነዚህ ሶስት አካላት ድብዳቤ እንዲጽፍላቸው ፍርድ ቤቱን አስጨንቀውታል።

ኢህአዴግ አክራሪ የኒዮሊበራል ሀይሎች የግብርና ኢንቨስትመንቴን እየጎዱብኝ ነው አለ

ጥቅምት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የሀገር ውስጥና የዉጪ ሀገር ባለሀብቶች በሰፋፊ እርሻዎች ላይ እንዲሰማሩ ባለፉት አምስት አመታት ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም የኒዮሊበራል ሀይሎች ባካሄዱት ፕሮፖጋንዳ ምክንያት ውጤት ማግኘት አልቻልኩም ሲል አማሯል።

ከግንባሩ የተገኘ አንድ የግምገማ ሰነድ ፣ የሀገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶች በቆላማ አካባቢዎች በኮሜርሻል እርሻዎች እንዲሳተፉ አስፈላጊው ድጋፍ ቢደረግም ፣ አንዳንዶቹ በእድሉ ተጠቅመው ጥሩ እያመረቱ ቢሆንም፣ ሌሎች ግን ከስረው ከስርአቱ ለመውጣት እየተዘጋጁ ነው ብሎአል።
ሰነዱ “አዳዲስ ባለሀብቶች ወደዘርፉ ለማስገባት የሚደረገውን ጥረት አክራሪ የኒዮሊበራል ሃይሎች “መሬት ተወረረ፣ ህዝብ ተፈናቀለ” እያሉ በሚነዙት የበሬ ወለደ ዘመቻ መደናገር ያለ በመሆኑ እንዳሰብነው አልተሳካም “ይላል። አንዳንድ ባለሀብቶች ይህንኑ ዘመቻ ወደጎን ብለው የመጡ ቢሆንም፣ በአካባቢዎቹ በቂ መሰረተልማት ባለመሙዋላቱ በተገቢው ሁኔታ ማሳተፍ እንዳልተቻለ ይገልጳል። በአሁኑ ሰአት ከእነ ጉድለቱም ቢሆን ግማሽ ሚሊየን ሄክታር መሬት በባለሀብቶች እየለማ ነው ሲል አክሏል።
ኢህአዴግ ስርአቱን የሚቃወሙትን ወይም የሚፈጽመውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጋልጡትን አለማቀፍ ድርጅቶችም ጭምር የኒዎ ሊበራል ወኪሎች ይላቸዋል።

በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የዲሽ ተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረ ነው

ጥቅምት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ወኪላችን በአዲስ አበባ የተለያዩ መንደሮች በመዘዋወር ባደረገው ቅኝት እጅግ ደሃ በሚባሉት መንደሮች ሳይቀር በዲሽ ከውጭ አገር የሚለቀቁ ስርጭቶችን የሚያየው ህዝብ ቁጥር ጨምሯል ብሎአል።

በፎቶ ግራፍ አስደግፎ በላከው መረጃ ፣ የዲሽ ቁጥር መጨመር ህዝቡ የኢሳትን የናይል ሳት ስርጭት በብዛት እየተከታተለ መሆኑን ማሳየት ብቻ ሳይሆን፣ የመንግስቱን የቴሌቪዥን ስርጭት ለመስማት ፍላጎት እንደሌለውም የሚያመለክት ነው ብሎአል።

ኢትዮጵያ የተሸከመችው 25 ቢሊዮን እዳ አሳሳቢ አይደለም ሲሉ አቶ ሃይለማሪያም ገለጹ

ኢሳት (ጥቅምት 17 ፣ 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት ተሸክሞ ያለው ከ25 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ ጫናን አልፈጠረም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
የአለም አቀፉ ሞኒተሪ ፈንድ (አይ ኤም ኤፍ) እና በርካታ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ሃገሪቱ ተሸክማ ያለው ከፍተኛ ብድር ኢኮኖሚውን እየጎዳው እንደሚገኝ በመግለጽ ላይ ናቸው።
በሃገሪቱ የተከማቸ ብድር መጠን ከኢትዮጵያ አጠቃላይ  አመታዊ ምርት 50 በመቶውን እንደሚሸፍንና ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን IMF በቅርቡ በቅቡ ባወጣው ሪፖርት መግለጹ ይታወሳል።

131 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ኬንያ አሳልፋ እንድትሰጥ ኢትዮጵያ ጠየቀች

ኢሳት (ጥቅምት 17 ፣ 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኛ ወንጀል ይፈለጋሉ በማለት ኬንያ 131 ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን አሳልፋ እንድትሰጠው ጥያቄ መቅረቡን የምስራቅ አፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ሊግ ገለጠ።
የኢትዮጵያ የደህንነት እና ኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ለኬንያ አቻው ያቀረበውን ይህንኑ ጥያቄ ተከትሎም በእስካሁኑ ሂደት አቶ ደበሳ ጉያ የተባለ ስደተኛ ኢትዮጵያ የገባበት ሊታወቅ አለመቻሉን የሊጉ ፕሬዚዳንት አቶ ጋሩማ በቀለ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በሽብርተኛ ወንጀል እፈልጋቸዋለሁ ብላ ስማቸው አስተላልፋ የሰጠቻቸው 131ዱ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በኬንያ ለ20 ዓመታት ያህል የኖሩና ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ገልጸዋል።
የኬንያ መንግስትም ኢትዮጵያኑን ስደተኞች አሳልፎ እንዳይሰጥ ጥያቄ መቅረቡን የሊጉ ሃላፊ በሰጡት ቃለምልልስ አስታውቀው የኢትዮጵያውኑ ደህንነትም አሳሳቢ ሆኖ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

Tuesday, October 27, 2015

“በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት አለ” የሚለው ተረት ተረት ነው ሲሉ ዶ/ር መረራ ጉዲና ገለጹ

ጥቅምት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦሮሞ ፌደራሊስት ሊቀመንበር እና የመድረክ የአመራር አባል የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ይህን ምላሽ የሰጡት ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀረበውን የውይይት ግብዣ ተቃዋሚዎች ውድቅ ማድረጋቸውን ለፓርላማ አባላት መናገራቸውን ተከትሎ ነው።

መንግስት በጠራው የአምስት ኣመታት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውይይት ላይ ያልተሳተፉ እንደመድረክ፣ ሰማያዊ እና መኢአድ ያሉ ፓርቲዎች ያቀረቡት ምክንያተ ውሃ ያማያነሳ ነው ያሉት አቶ ሃይለማርያም ፣ ፓርቲዎቹ ያልተሳተፉት በሕጋዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት አይደለም በማለት መሆኑን ጠቅሰው ወደፊት ከየትኛው መንግስት ጋር እንደሚወያዩ እናያለን ሲሉ ዝተዋል፡፡
ዶ/ር መረራ ሲናገሩ፣ “በቅድሚያ አንነጋገርም አላልንም፣ ቅድሚያ መሰረታዊ በሆኑት የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ለምሳሌ ነጻ ምርጫን ፣ ነጻ ሚዲያን፣ በነጻነት መንቀሳቀስንንና በመሳሰሉት መሰረታዊ መብቶች ጉዳይ እንነጋገር ” ነው ያለው ካሉ በሁዋላ፣ እነሱ በሚሉት ጉዳይ ላይ ለመነጋገርም ፣ በር ዘግቶ ሳይሆን፣ በነጻ ሜዳ፣ ለህዝብ በቀጥታ በሚተላለፍ መልኩ መሆን አለበት በማለት በጽሁፍ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

ብአዴን 35ኛ አመቱን ለማክበር ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ያወጣል

ጥቅምት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ብአዴን ወጪውን የሚሸፍነው በዋነኝነት ከነጋዴዎችና ከነዋሪዎች ነው። በርካታ የክልሉ ነጋዴዎች ገንዘብ እንዲለግሱ የጥሪ ወረቀት ደርሶአቸዋል። ድርጅቱ ከህወሃትና ከኦህዴድ ባላነሰ መልኩ በአሉን እንደሚያደርግ እየገለጸ ሲሆን፣ አገሪቱ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ አንዣቦባት ባለበት እንዲሁም የኑሮ ውድነቱ የህዝቡን ኑሮ ፈተና ውስጥ በጣለበት ሰአት ይህን ያክል ገንዘብ ህዝቡን አስገድዶ በማውጣት ለማክበር ማሰብ ኢ-ሞራላዊና ህዝብን መናቅ ነው ሲሉ መረጃውን የላኩ የብአዴን አባላት ተናግረዋል።

የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ሽመልስ ከማል ከኃላፊነታቸው ተነሱ

ጥቅምት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አቶ ሽመልስ ፣ አቶ በረከት ስምኦን ከኮምኒኬሽን ሚኒስትርነት ተነስተው በአቶ ሬድዋን ሁሴን ከተተኩበት ካለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ወዲህ ከአቶ ሬድዋን ጋር መስማማት ባለመቻላቸው በስራ ገበታቸው ላይ የሚገኙት አልፎ አልፎ ነበር፡፡ የሁለቱ ሚኒስትሮች አለመግባባት በኢሳት ከቀረበ በኃላ ችግር የለብንም ለማለት ለአንድ ቀን አብረው መግለጫ በመስጠት ጎን ለጎን ተቀምጠው ከታዩ ወዲህ ደግመው እንኳን አብረው መታየት አልቻሉም፡፡

የአቶ ሬድዋን እና የአቶ ሽመልስ አለመግባባት ትክክለኛ ምክንያት ባይታወቅም የቅርብ ባልደረቦቻቸው እንደሚናገሩት ከቡድንተኝነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
የአቶ ሽመልስ ውግንና ከእነአቶ በረከት ስምኦን ጋር መሆኑ በእነአቶ ሬድዋን ባለመወደዱ፣ ሰበብ አስባብ እየፈለጉ በመተቸት ግለሰቡን ከአጠገባቸው ዞር እንዲሉ ማድረጋቸው በባልደረቦቻቸው ይነገራል፡፡ በአቶ ሬድዋን በኩል አቶ ሽመልስን በተመለከተ ተደጋግሞ የሚነሳው ሥራውን በአግባቡ አይሰራም፣ ቢሮ አይገኝም የሚል ቢሆንም ዋንኛ ምክንያት ግን የፖለቲካ ቡድንተኝነት የፈጠረው መሆኑን ባልደረቦቻቸው ይናገራሉ።
በአሁኑ ሰዓት አቶ ሽመልስ የት እንደተመደቡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ያልታወቀ ሲሆን በቀጣይ ቀናት ግን አንድ ቦታ በአማካሪነትም ቢሆን መሾማቸው የማይቀር መሆኑን ምንጮቹ ገምተዋል፡፡
አቶ ሽመልስ ከማል የ1997ቱን ታሪካዊ ምርጫ ተከትሎ በተለይ የቅንጅት ተከሳሾችን ጉዳይ በአቃቤ ሕግነት በመያዝና በመምራት ከዚህ ቀደም በስራ ይተዋወቁዋቸው የነበሩ የቅርብ ጓደኞቻቸውን ጭምር የጥቅም ግጭት በሚያስከትል መልኩ ሐሰተኛ መረጃዎችንና ምስክሮችን በማዘጋጀት ከባድ ቅጣት እንዲጣልባቸው የራሳቸውን ሚና የተወጡ የኢህአዴግ ባለውለታ ናቸው፡፡
አቶ ሽመልስን የተኩት የብአዴን ታጋይና ማዕከላዊ ኮምቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ ፍሬሕይወት አያሌው ሲሆኑ ፣ ወደ ጠ/ሚኒስትር ቢሮ የተዛወሩትን የኦህዴዱ አቶ እውነቱ ደበላን የተኩት ደግሞ የኦህዴድ አባልዋ ወ/ሮ ብርቅነሽ ብሩ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች አሁንም ወደ የመን መፍለሳቸውን እንዳላቆሙ ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት አሳታወቀ

ጥቅምት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መነሻቸውን ከሶማሊያ የባሕር ዳርቻዎች በማድረግ በሕገወጥ መንገድ ሕይወታቸውን ለአደጋ አልጋልጠው በጦርነት ሰላሟ ወደራቃት የመን የሚሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ቁጥር መጨመሩን ዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት በምህጻረ ቃል /UNHCR/ አስታውቋል። ባለፈው ዓመት ብቻ ከ70 ሺ በላይ አዲስ ስደተኞች የመን መግባታቸውን የገለጸው ድርጅቱ፣ ጥቂት የሶማሊያ ዜጎች ሲገኙበት አብዛኞቹ ስደተኞች ኢትዮጵያዊያን ናቸው። 88 ስደተኞች በባሕር ውስጥ ሰጥመው መሞታቸውንም ድርጅቱ አስታውቋል።

የመንን ለመሸጋገሪያነት በመጠቀም ወደ ተለያዩ የአረብ አገራት ለስራ ፍለጋ የሚመጡት ስደተኞች የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙባቸውና በየመን ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የምግብ እና የጤና አቅርቦት የተሟላ ባለመሆኑ የረድኤት ድርጅቶች አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንዳሉም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ሁለት አሃዝ አድጋለች እየተባለ በየቀኑ ቢነገርም ፣ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በአራቱም ማእዘናት መፍለሳቸውን አለማቆማቸው ሲታይ የአገሪቱ ምጣኔ ሃብታዊ ለውጥ ትሩፋቶች ለሕዝቡ እንደልደረሰ ያመላክታል ሲሉ የሙያው ጠበብት ይገልጻሉ።

Monday, October 26, 2015

በጎንደር አንድ የአርበኞች ግንቦት 7 አባል በ6 ፖሊሶች ላይ ጥቃት ፈጽሞ ራሱን አጠፋ

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም አመሻሽ ላይ አምሳሉ ተሾመ የተባለው ታጋይ ሰዎችን በመመልመል ወደ በረሃ ተልካለህ ተብሎ በመጠርጠሩ፣ ፖሊሶች ሊይዙት ሲሞክሩ፣ እጄን አልሰጥም በማለት በያዘው ሽጉጥ አንድ የመቶ እልቅና ያለው መኮንንና ሌላ አንድ ተራ ፖሊስን በመግደል፣ እንዲሁም 4 ታጣቂዎች በማቁሰል በመጨረሻም በያዘው ሽጉጥ ራሱን አጥፍቷል።

ወጣቱ ከዚህ ቀደም የአርበኞች ግንቦት7 አባል ነህ በሚል ታስሮ የተፈታ ሲሆን፣ ባለፈው አርብ በድጋሜ ፖሊሶች ሊይዙት ሲመጡ ” አትቅረቡኝ ተመለሱ ” እያለ ማስጠንቀቁን ያልተቀበሉት ፖሊሶች ፣ እርምጃ ለመውሰድ ሲሞክሩ ታጋዩ ፈጥኖ እርምጃ በመውሰዱ በታጣቂዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ በራሱም ላይ እርምጃ መውሰዱን የአይን እማኞች ገልጸዋል።

በቴፒ የመንግስት ታጣቂዎች ህዝቡን ሲያዋክቡት ሰነበቱ

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በድቡብና ጋምቤላ የድንበር ከተማ በሆነቸው ቴፒ ራሳቸውን ያደራጁ ወጣቶች በመልካም አስተዳደርና ህዝቡን አፍኖ በመግዛት ለስቃይ ዳርገውታል ባሉዋቸው የመንግስት ታጣቂዎች እና ሹማምንት ላይ የሚያደርሱትን የሃይል ጥቃት መቆጣጠር እየተሳነው የመጣው መንግስት ካለፈው አርብ ጀምሮ፣ በተለያዩ የከተማው አካባቢዎች ጥቃቱን በማስፋት ነዋሪዎች ሲያሰቃይ ሰንብቷል።

በአዲስ አበባ እስረኞች አመለጡ አንዱ ተገደለ

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዛሬ ጥቅምት 15/2008 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት 3 ያህል እስረኞች ማምለጣቸውን የአይን እማኞች ገልፀዋል፡፡ እስረኞቹ በተለምዶ ሰባራ ባቡር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ፍርድ ቤት ፊት ለፊት አስፓልቱ ላይ ከመኪና ወርደው ወደ ፍርድ ቤቱ በሚገቡበት ወቅት መጥፋታቸውን የአይን እማኞች ገልፀዋል፡፡ በወቅቱ ሶስት ያህል እስረኞች እንዳመለጡ የተገለፀ ሲሆን አንድ ከሶማሊ ክልል የመጣ ነው የተባለ እስረኛ በጥይት ተተኩሶ እንደተገደለም የአካባቢው ነዋሪዎች አክለው ገልፀዋል፡፡ እስረኛው ፍርድ ቤቱ ፊት ለፊት ከሚገኘው አስፓልት ወጥቶ 200 ሜትር ያህል ወደ ሰፈር ከገባ በኋላ ከኋላው ተመትቶ እንደተገደለ እማኞቹ የተናገሩ ሲሆን፣ የሶማሊ አካባቢ ተወላጅ መሆኑን የተናገሩት ፊቱን እና ቁመቱን በማየት መሆኑን ገልጸዋል።

ኬንያ ውስጥ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ወደ ኢትዮጰያ ተላልፈው ሊሰጡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳደረበት ሂውማን ራይትስ ሊግ ገለጸ

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት ሊጉ ለኢሳት በላከው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት የጸረ ሽብር ግብረሃይል ለኬንያ መንግስት የ131 የኦሮሞ ተወላጆችን ስም በመዘርዘር በሽብረተኝነት የሚፈለጉ በመሆኑ ተላልፈው እንዲሰጡት ጠይቋል።

በቅርቡ ኬንያ ውስጥ የደረሱበት ያልታወቁት የ80 አመት አዛውንቱ አቶ ደባሳ ጉዮ፣ ከ35 አመታት በላይ ከኖሩበት ኬንያ ታፍነው መወሰዳቸውን ገልጿል።
ድርጅቱ የኬንያ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት ላቀረበለት ጥያቄ ምላሽ እንዳይሰጥ ጠይቋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች የኦሮሞ ስደተኞች ለገጠማቸው አደጋ ትኩረት እንዲሰጡም ድርጅቱ አሳስቧል።

የፖለቲካ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥምረት መሰረቱ

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻ አውጭ ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ህዝብ ነጻ አውጭ ንቅናቄ፣ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ንቅናቄ፣ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባርና የሲዳማ ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር ” የህዝቦች የነጻነትና የዲሞክራሲ ጥምረት” የተባለ የጋራ ጥምረት መመስረታቸውን ለኢሳት በላኩት መግለቻ አስታውቀዋል።

ጥምረቱ በመግለጫው ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን እድል በራሳቸው መወሰን የሚችሉበትን፣ በነጻ ምርጫ ስልጣን የሚይዙበትን መንገድ ለማፈላለግ እንደሚሰራ ጠቅሷል።

ከ30 አመታት ወዲህ አስከፊ ነው ለተባለው ድርቅ እርዳታ ቢቀርብም በቂ አይደለም ተባለ

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ክፍል ባወጣው ዘገባ፣ አገሪቱ ለገጠማት አስከፊ ረሃብ አንዳንድ የምእራብ አገራት እርዳታ እያደረጉ ቢሆንም፣ እርዳታው አሁንም በቂ አይደለም ብሎአል።

አንዳንድ መንግስታት ለልማት በሚል ለመንግስት ሊሰጡት ያሰቡትን እርዳታ፣ለተጎጂዎች ለማዋል እያሰቡ መሆኑንም መጽሄቱ ገልጿል። በሶማሊ ክልል በኤሚ ወረዳ የሸበሌ ወንዝ በከፍተኛ ሁኔታ በመሙላቱ 700 የሚጠጉ ሰዎች በምስራቅ ኤሚ ወረዳ መጠለላቸውንና እርዳታ እየተጠባበቁ መሆኑን መጽሄቱ ዘግቧል።
በተመሳሳይ ዜናም በዘንድሮው ድርቅ ያጋጠመውን የእንስሳት ሞት አስቀድሞ የመቀነስ ስራ አለመከናወኑን የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው አምነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬድዮ የተመሰረተበት 5ኛ ዓመት በአውስትራልያ ብሪዝቤን ከተማ በልዩ ሁኔታ ተከብሮ ዋለ።

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቅዳሜ ጥቅምት 13 2007 ዓም በተካሄደው በዚህ ዝግጅት ላይ ነዋሪነታቸው በኪዊንስላንድ ግዛት የሆኑ የሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የታደሙበት ሲሆን ለንደን ከሚገኘው የኢሳት ማሰራጫ ጣቢያ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ቀጸላ ተገኝታ ከነዋሪዎቹ ጋር ውይይት ተካሂዷል። ዝግጅቱን በቡራኬ የከፈቱት በብሪዝበን የደብረ ጸሃይ ቅዱስ ጊዎርጊስ ቤ/ክ አስተዳዳሪ ቀሲስ መንግስቱ ሃይሉ ሲሆን እሳቸውም ከቡራኬው አስከትለው ባደረጉት ንግግር ሃገራችንና ህዝቧ በአሁኑ ወቅት እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ መገኘታቸውን አውስተው ለተገፉት ድምጽ በመሆን እውነትን እያወጣ ያለውን ኢሳትን ሁላችንም መደገፍ እንደሚገባን አሳስበው፤ እውነትን ከያዘ ጎን መቆም በራሱ ሃይማኖታዊ ስራና ግዴታም ጭምር መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

Saturday, October 24, 2015

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአየር ላይ አደጋ ተረፈ

ኢሳት ዜና :- ሶስት መቶ መንገደኞችን ጭኖ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በደብሊን አድርጎ ወደ አሜሪካ ሲጓዝ የነበረው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ድሪምላይን 787-8 አውሮፕላን ዛሬ ማለዳ ላይ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር በድንገት አንድ ሞተሩ አየር ላይ ቢጠፋም በአየርላንድ ዋና ከተማ ደብሊን በሰላም ማረፍ ችሏል። መንገደኞቹ ከጀርመን ፍራንክፈርት በተላከ ተቀያሪ አውሮፕላን ወደ አሜሪካ ማቅናታቸውን ሜይል ኦንላይን ዘግቧል።

ባሳለፍነው ሳምንትም ጋምቤላ ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለማረፍ ሲሞክር አደጋ አጋጥሞት በሰላም ማረፉ ይታወሳል።

Friday, October 23, 2015

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ) ‪#‎የህወሓት‬ አገዛዝ ከመከላከያ ሰራዊቱ የሚከዱ አባላትን ጨርሶ መቆጣጠር ከማይችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተረጋገጠ፡፡

(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ)
‪#‎የህወሓት‬ አገዛዝ ከመከላከያ ሰራዊቱ የሚከዱ አባላትን ጨርሶ መቆጣጠር ከማይችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተረጋገጠ፡፡
‪#‎በጎንደር‬ ወገራ ወረዳ በአራት ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ድርቅ ደርሶ ነዋሪዎች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸው እና የቤት እንስሶቻቸውም በማለቅ ላይ መሆናቸውም ተሰማ፡፡
#የህወሓት አገዛዝ የላይ አርማጭሆ ሙሴ ባንብ ነዋሪ የሆኑ 50 ወጣቶችን በስብሰባ ስም በኃይል ጠርንፎ ይዞ ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አላችሁ እያለ በምርመራ እያስጨነቃቸው እንደሚገኝ የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ ዜና ምንጮች የላኩት መረጃ አጋለጠ፡፡
#በጎንደር ከተማ ወላጆች ልጆቻቸውን በአገዛዙ ቁጥጥር ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለማስመዝገብ ለደላሎች በአንድ ሰው ከ500-1000 ብር እንዲከፍሉ በመገደዳቸው ከፍተኛ ምሬት ውስጥ ናቸው፡፡

“ተመስገንን ማየት አትችሉም!” (ታሪኩ ደሳለኝ)

ታሪኩ ደሳለኝ – አዲስ አበባ
ወንድማችን ተመስገን ሀሳቡን በነጻነት ስለገለጸ እና ጽሁፎችን በጋዜጣ ስላተመ ብቻ ሶስት ዓመት ተፈርዶበት ወደ ዝዋይ እስር ቤት ከተላከ ዛሬ 374 ቀናት ሆነው፡፡ በተለያየ ጊዜ ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ቢደርስበትም ሁሉን ችሎ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ለሚያሰቃየው የወገብ እና የጆሮ ህመም ህክምና ሳያገኝ ዛሬም ህመሙን እየታገለ አለ፡፡ የታሰረበትን አንደኛ ዓመት በማስመልከት ይህንን ችግሩን እና የሚደርስበትን እንግልት አስመልከቶ እኛም፣ ወዳጆቹም ለመናገር ሞክረናል፡፡ አቤቱታችንን እና ጩኸታችንን ተከትሎ ችግሮቹ ይስተካከላሉ ብለን ብናስብም ይባስ ብሎ በገደብ የተፈቀደለት የቤተሰብ ጥየቃ እንዳያገኝ ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ ተከልክሏል፡፡

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንደሌሉ ገለፀ

• ‹‹የስርዓቱን ሽፍትነት ያመላክታል›› 3ኛ ተከሳሽ አቶ ደናሁን ቤዛ
• ‹‹የሚቀርብልን ምግብ ለእንሰሳትም መቅረብ የማይገባው ነው›› 2ኛ ተከሳሽ አቶ አሸናፊ አካሉ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከ2ኛ -5ኛ መዝገብ ለተከሰሱት አቶ አሸናፊ አካሉ (2ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ደናሁን ቤዛ (3ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን (4ኛ ተከሳሽ) እና አቶ አንሙት የኔዋስ (5ኛ ተከሳሽ) በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሌሉ ማረሚያ ቤቱ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛው ወንጀል ችሎት በላከው ደብዳቤ ገልፆአል፡፡ 19ኛ ወንጀል ችሎት ሀምሌ 29/2007 ዓ.ም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ለምን እንዳላቀረበ እንዲያብራራ፣ እንዲሁም ለምስክርነት እንዲያቀርብ ለዛሬ ለጥቅምት 12/2008 ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበር ቢሆንም ማረሚያ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው ቃሊቲ እንደሌሉ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡

Thursday, October 22, 2015

የሞያሌ ወጣቶች ለውትድርና ምዝገባ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ አደረጉት

ጥቅምት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ ሞያሌ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ወጣቶችን ለውትድርና ለመመዝገብ በድምጽ ማጉያ የታገዘ ቅስቀሳ ቢያካሂዱም፣ አንድም ለምዝገባው ፈቃደኛ ሆኖ የሄደ ወጣት አለመኖሩን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ።

ወጣቶቹ የተደረገላቸውን የስብሰባ ጥሪ ባለመቀበላቸውም፣ መንግስት በሞያሌና አካባቢዋ አዳዲስ ምልምል ወታደሮችን ለመመዝገብ ያቀደው እቅድ ሳይሳካ ቀርቷል። አምና 10ኛ ክፍል ያጠናቀቁ ወጣቶችን ለወትድርና ለመመዝገብ ማቀዱን የገለጸው መንግስት፣ ሂደቱ ውጤታማ ባለመሆኑ የትምህርት ደረጃ መስፈርቱን ወደ 8ኛ ክፍል ዝቅ አድርጎት ነበር። ይህም ሆኖ ተመዝጋቢ በመጥፋቱ የትምህርት ደረጃ መስፈርቱ ወደ 5ኛ ክፍል ዝቅ እንዲል ተደርጓል።
በደቡብ ክልል ሰሞኑን ሲካሄድ የቆየው የውትድርና ምዝገባ ባለመሳካቱ የአካባቢውን ሹማንምን አስድንግጧል። የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ ባለስልጣናት እንደሚለምሉ የተሰጣቸውን የሰራዊት ቁጥር ለሟሟላት ባለመቻላቸው፣ ለስልጠናና ትምህርት በሚል ወጣቱን ለመመዝገብ ቢያቅዱም ይህም እቅድ ሳይሳካ ቀርቷል። መንግስት በየጊዜው በገፍ እየጠፉ የሚገኙትን የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአዳዲስ ምልምል ወታደሮች ለመተካት በማሰብ ቅስቀሳውን መጀመሩን ምንጮች ይገልጻሉ።
በሁሉም አቅጣጫዎች የሚጠፉ ወታደሮች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ መጨመሩን የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ።

ብአዴን ለበአል ማክበሪያ በሚል ህዝቡን በመዋጮ እያስጨነቀው ነው

ጥቅምት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-35ኛ አመቱን ለማክበር በዝግጅት ላይ ያለው ብአዴን ፣ በአማራ ክልል የሚኖረው ህዝብ ለበአሉ ማድመቂያ ገንዘብ እንዲያዋጣ እያስገደደ ነው። ነጋዴዎች ከብአዴን ጽ/ቤት የተጣለባቸውን ክፍያ ያለፍላጎታቸው በግድ እንዲከፍሉ ታዘዋል።

ከፍተኛ የረሃብ አደጋ በክልሉ ባንዣበበት በዚህ ወቅት፣ ብአዴን እንደ ህወሃትና ኦህዴድ መቶ ሚሊዮኖችን አፍስሶ በአሉን ለማክበር መሞከሩ ፣ ከታሪክ አለመማሩን ያሳያል የሚሉት አንድ በክልሉ የሚኖሩ መምህር፣ ድርጅቱን በህወሃት ተለጣፊነቱም ይከሱታል።
የክልሉ ህዝብ በኑሮ ውድነት የተነሳ በነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ውስጥ ነው የሚሉት መምህሩ፣ ብአዴን ህዝቡን ሊደጉም ሲገባ፣ በተቃራኒው ህዝቡ ብአዴንን እንዲደጉም መገደዱ አሳዛኝም አሳፋሪም ነው ይላሉ።
ብአዴን ከህወሃት ጋር በሽርክና ከያዛቸው የንግድ ድርጅቶች ማለትም ዳሽን ቢራ ፋብሪካ፣አምባሰል የንግድ ሥራዎች፣ጥቁር አባይ ትራንሰፖርት ፣ ዘለቀ እርሻ ሜካናዜሽን ኩባንያዎች፣ ዳሽን ቢራ ቁጥር ፣ ጣና ፐልፕና ወረቀት ፋብሪካ ፣ ጎንደር ብቅል ፋብሪካ፣ ጣና ኮምዩኒኬሽን ፣ ሎያል ጥረት የጥጥ መዳማጫ ፋብሪካ ፣ በለሳ ሎጅስቲክሰ ፣ዋልያ ቆርኪ ፋብሪካ ፣ ተክራርዋ ፕላስቲክ ፋብሪካ ፣ ወልድያ አትክልትና ፍራፍ ፣ ትዛ የወተት ሃብት ፣ አዚላ የፍሪጅ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ፣ ጥቁር አባይ የመኪና መገጣጠሚ ፋብሪካ ፣ ቢዲሲ ኮንስትራክሽን ፣ ማዕድ የምግብ ኮምፕሌከሰ ፣ ቲቲ ኢንጅነሪንግ ፣ የጁ ማር እና ሌሎች 16 ድርጅቶች እንዲሁም ብአዴን ሼር የገባባቸው አባይ ባንክ፣ አፍሪካ ኢንሹራንስ፣ ሬዲዮ ፋና እና ወጋገን ባንኮች በእያመቱ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ ቢያገኝም፣ የድርጅቱ ገቢ ለአማራው ህዝብ ምንም የፈየደለት ነገር የለም።
ምንጮች እንደሚሉት የብአዴን ጥረት የሚባለውን ተቋም የአንድ አካባቢ ሰዎች በመንደር ተሰባስበዉ ሀብቱን እንዳሻቸዉ የሚመዘብሩት ተቋም ነው።
በአላስፈላጊ የዉጭ አገር ጉዞ፡ የጥረት እና የብአዴን ከፍተኛ ባለስልጣኖችን እስከ ቤተሰቦቻቸው ውጭ አገር ልኮ ለማሳከም፣ የፖለቲካ ታማኞችን ለመግዛት የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ፣ ባለስልጣኖች በግለሰቦች ስም አክሲዮን በመግባት የሚያጋብሱት ከፍተኛ ገንዘብ ከብአዴኑ ጥረት የሚመጣ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ።
ድርጅቱ ከ36 በላይ በሚሆኑት የንግድ ድርጀቶቹ በአሉን ማክበር እያቻለ ደሃውን ህዝብ ገንዘብ አዋጡ እያሉ ማስጨነቅ ነውር ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው በማለት መናገራቸውን ዘጋቢያችን ከባህርዳር የላከልን ዘገባ ያመለክታል።

አስራ አምስት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ኬንያ ውስጥ ተያዙ

ጥቅምት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኬንያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሳምብሩ ምስራቃዊ ኢዞሎ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ሎሲሳ ውስጥ በሕገወጥ መንገድ ገቡ ያላቸውን አስራ አምስት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ማሰሩን አስታውቋል።

ባለፈው እሁድ ሃያአራት፣ ሰኞ ደግሞ ስድስት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአካባቢው በታጣቂዎች በከበባ መያዛቸውን ገልጸዋል።ስደተኞቹ በሕገወጥ መንገድ ካለምንም ሕጋዊ ፍቃድ ድንበር አቋርጠው እንደሚገቡና አስራ አምስቱ ኢዞሎ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን የጸጥታው ሹም ኪፑቺምፓ ሮቶ መናገራቸውን ኦል አፍሪካ ዘግቧል።
ገዥው ኃይል በኢትዮጵያ ኤኮኖሚያዊ ለውጥ አምጥቻለው እያለ በመገናኛ ብዙሃን ቀን ከሌት ቢናገርም፣ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚወጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ሲጨምር እንጅ ሲቀንስ አይታይም።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሎሚ መፅሄት ማኔጂንግ ደይሬክተር ላይ የ 18 አመት እስር በየነበት !!


የሎሚ መፅሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ባለቤት የሆነው ጋዜጠኛ ግዛው ታዬ ላይ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ 18 አመት እስራትና የ 100 ሺህ ብር ቅጣት ሲበየንበት በመፅሄቱ አሳታሚ ድርጅት ላይ ደግሞ የ 200 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት በዛሬው ዕለት በሌሉበት ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላልፎል!
ከ 800 ሺህ ብር በላይ ታክስ በማጭበርበርና በሌሎች 14 ክሶች ጥፋተኛ የተባለው የሎሚ መጽሄት ዋና ስራ አስኪያጅ በ 18 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ተወሰነ.
በመጽሔታቸው በወጡ ጽሁፎች ድርጅቱና ሥራ አስኪያጆቹ ሐሰተኛ ወሬ አትሞ በማውጣትና ሕዝብን በማነሳሳት ወንጀል ‘በሚሉ ሁለት ክሶች ሰኔ 6 ቀን 2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር መከሰሳቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤት ቆመውም ነበር.

የህወሓት አገዛዝ ከመከላከያ ሰራዊቱ የሚከዱ አባላትን ጨርሶ መቆጣጠር ከማይችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተረጋገጠ፡፡


11144995_814272385352811_3462902730849957444_o
የህወሓት አባላት በሆኑ የይስሙላህ የጦር መኮንኖች ከታች እስከላይ ተጠርንፎ በጉልበት ተይዞ በአገር መከላከያ ስም እየተጠራ ነገር ግን በፀረ-ህዝብነት ሳይወድ በግድ እንዲሰለፍ እየተደረገ የሚገኘው ሰራዊት ስርዓቱን መክዳቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ፈፅሞ ከአገዛዙ ቁጥጥር ውጭ ሆኗል፡፡
በተለይም ደግሞ ማዕከላዊ ዕዝ እና ምዕራብ ዕዝ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት የከዳባቸው መሆናቸው ታውቋል፡፡

Wednesday, October 21, 2015

እንግሊዝ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጉዳይ ቅደሚያ እንድትሰጥ በድጋሜ ተጠየቀች

 ኢሳት ዜና :-በእስር ላይ የሚገኙትን የግንቦት 7 ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ህገወጥ እስር አስመልክቶ የእንግሊዝ ባለስልጣናት ነገ በሚጀመረው የኢትዮጵያና የእንግሊዝ የንግድና ኢንቨስትመንት መድረክ ላይ ሊያነሱት እንደሚገባ አቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ የሚከታተለው ሪፕሪቭ የተባለው ተቋም ጠይቋል።

የንግድ እና የኢንቨስትመንት ስብሰባው ከፍተኛ ቦታ የተሰጠው እንደመሆኑ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግራንት ሻፕስ ለኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጉዳይ ማንሳት ይኖርባቸዋል ብሎአል። ሪፐርቭ አቶ አንዳርጋቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እየጠየቀ ባለበት ሁኔታ፣ የእንግሊዝ ባለስልጣናት ግን ስለ አማካሪና ስለህግ ሂደት ያወራሉ በማለት ተችቷል። እንግሊዝ የነገውን አጋጣሚ በመጠቀም አቶ አንዳርጋቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ መጠየቅ አለባት ሲል ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።

የወልቃይት ነዋሪዎች ወደ ትግራይ መካለላቸውን እንደማይቀበሉት አስታወቁ

 ኢሳት ዜና :-ነዋሪዎች “መሰረታችን ሕገ መንግስቱ ነው ተብሎ የወልቃይት ነዋሪዎች ቋንቋን ብቻ መሰረት ያደረገና የሕዝቡን ስነ ልቦናዊ፣ ባሕላዊ ወግን ያላማከለና ያላጠቃለለ ክልላዊ አከላለል በማድረግ የወልቃይት ሕዝብ የማይፈልገውንና የማያምንበትን በመጫን በግድ ወደ ትግራይ እንድንካለል መደረጋችን በውስጣችን ያለውን ማንነታችንን በመጨፍለቅ እንድንቀበል እየተደረግን ነው ፣ዛሬ ስነ ልቦናችን የማይቀበለውን ሕወሃት በዘዴ ማንነታችንን ለማሸማቀቅ እየሞከሩ ነው” ብለዋል ።

አቶ አበበ ካሴ በማንነቱ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየተፈፀመበት እንደሆነ ገለፀ።

ኢሳት ዜና:-በሽብርተኝነት ተከሶ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኘው አቶ አበበ ካሴ እስር ቤት ውስጥ በማንነቱ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየደረሰብኝ ነው ሲል ለፍርድ ቤቱ አቤቱታውን አሰምቷል፡፡ በእነ አበበ ካሴ የክስ መዝገብ ሁለተኛ ተከሳሽ የሆነው አቶ ታጠቅ አስማረ የተከላካይ ጠበቃ ለማቅረብ ዛሬ ጥቅምት 9/2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ለልደታ ፍርድ ቤት 19ኛው ወንጀል ችሎት አቤቱታውን ያቀረበው አቶ አበበ ካሴ በማረሚያ ቤቱ በተደጋጋሚ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመበት እንደሚገኝና ፍርድ ቤቱ መፍትሄ መስጠት እንዳልቻለ ገልፆአል፡፡

‹‹የሥርዓቱ መሪዎች ፍርድ ቤት ነፃ ነው ይላሉ፡፡ እንደዛ ከሆነ እናንተም መብታችሁን መጠቀም አለባችሁ፡፡ እናንተ ናችሁ ማዘዢያ ቆርጣችሁ የምታሳስሩት፣ የምትፈርዱት፡፡ በመሆኑም ማረሚያ ቤቱን መቆጣጠር አለባችሁ›› ሲል ፍርድ ቤት ግዴታውን እንዲወጣ አሳስቧል፡፡

ለእንዳርጋቸው መታፈን ተጠያቂ የተባሉት ዶ/ር ቴዎድሮስን ሎንዶን ላይ መጋበዝ እደጋ አለው ተባለ


ካለፈው አመት የፈረንጆቹ ሰኔ ወር መባቻ ላይ ወደ ኤርትራ ሲጓዙ የመን(ሰነኣ ) አለም አቀፍ አወሮፕላን ጣቢያ ላይ ታፈነው ለ አዲስ አበባ መንግስት ተላለፈው የተሰጡት እና ቀደም ሲልም በሌሉበት ኢትዮጵያ ውስጥ በ 2009 አኤአ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው የግንቦት 7ቱ ዋና ጸሃፊ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እጣ ፈንታ ያሳሰበው አንድ ታዋቂ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የእንግሊዝ መንግስት “ለጥቅሙ ሲል “የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይን ችላ እንዳይል ዳግም እስጥነቀቀ።
በሰው ልጆች ላይ የሞት ብይን እንዳይተገበር የሚሟገተው እና መቀመጫውን ሎንዶን(እንግሊዝ) ያደረገው አለማቀፉ ሪትሪቪው ድርጅት በነገው እለት (ጥቅምት 21 2015 )ሎንዶን ላይ በእንግሊዝ መንግስት ከፍተኛ የውጪ ጉ/ሚ/ር ባለሰልጣናት እና በኢትዮጵያ አቻዎቻቸው መካከል የሚደረገውን ንግድ እና ኢንቨስትመንት ተኮር ፎርምን በማሰመልከት ዛሬ ባወጣው መግለጫው “ ፎረሙ የሚካሄደው እንግሊዝ እንደ ኢትዮጵያ እና እንደ ስውዲ አርቢያ ከመሳሰሉት በሰበዊ መብት ይዞታቸው ከመወገዙ አገሮች ጋር ያላት ቁርኝት አወዛጋቢ በሆነብት ወቅት ነው ።” ያለው የመብት ተማጋቹ ድርጅት “ ከዚህ በሁዋላ የሰበዊ መብት ጉዳይ የእኛ ቅድሚያ አይሆንም ያለው የእንግሊዝ መንግስት አንዳርጋቸውን አፍነው ከወሰዷቸው ባለሰልጣናት (እነ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድህኖም ይገኙበታል ተብሏል ) በንግድ ዙሪያ ፎረም መክፈቱ እና የእንግሊዝ ዜግነት ላላቸው ፣በሌሉበት የሞት ፍርድ ለተበየነባቸው እና የሶስት ልጆች አባት ለሆኑት ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መታፈን ዋንኛ ተጠያቂ የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስን በንግድ ሽፋን መቀበል ተጨማሪ ስጋት እና የተሳሳተ መልእክት ያሰተላልፋል።” በማለት የሪትሪቪው ዋና ሃላፊ የሆኑት ሚሲስ ማያ ፎአ ሰጋታቸውን ገልጸዋል።

Tuesday, October 20, 2015

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ ተሸላሚ ሆነ

በሽብርተኝነት ተከስሶ 18 አመት የተፈረደበትና በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ ደረጃ አንድ ሰብዓዊነት (PEN Canada’s One Humanity Award) ሽልማት ተሸላሚ መሆኑን ፔን ካናዳ ይፋ አድርጓል፡፡


ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በፈረንጆቹ ግንቦት 2012 የባርባር ጎልድ ስሚዝ ሽልማት እንዲሁም በሰኔ 2014 የጎልደን ፔን ሽልማትን ተሸላሚ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ በካናዳ ቶሮንቶ እየተደረገ በሚገኘው 36ኛው ዓለም አቀፍ የፀሃፊዎች ፌስቲባል የፔን ካናዳ ደረጃ አንድ ሰብዓዊነት ሽልማትን ተሸልሟል፡፡

አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ለሁለተኛ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት አስመረቀ

የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ


Professor Berhanu Nega with Patriotic Ginbot7 fighters
አርበኞች ግንቦት 7 በሁለት ድርጅቶች ማለትም በኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር እና በግንቦት 7 ንቅናቄ ውህደት ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም ከተመሰረተ በኋላ ከትናትና በፊት እሁድ ዕለት ጥቅምት 7 ቀን 2008 ዓም ለሁለተኛ ጊዜ ብዛት ያላቸውን አርበኛ ታጋዮች ለሦስት ወራት አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡

የማእከላዊ ምርመራ የማሰቃየት ምርመራ መዘዝ - በጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ላይ

የ2007 አገር አቀፍ ምርጫ መቃረብን ተከትሎ መስዋእት ከሆኑት  የዞን ዘጠኝ ጦማር አባላት ውስጥ የሽብር ክሱ ወደ ወንጀል ክስ ተቀይሮ ዛሬም በግፍ እስር በብቸኝነት የሚገኘው በፍቃዱ ዘ ኃይሉ አመጽ ለመቀስቀስ አስበህ ነው የጻፍከው የተባለውን ጽሁፍ እንዲከላከል ተወስኖበታል፡፡ ይህ የአመጽ መቀስቀስ የተባለው ጽሁፍ ራሱን ሳይሆን የበፍቃዱን የማእከላዊ ምርመራ ቃል ብቻ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ቃሉን ብቻ መሰረት በማድረግ ይከላከል በማለት የማእላዊ ምርመራን በማሰቃየት ውስጥ የተሰጠ ቃል ተቀብሎታል ማለት ነው ?

በአስገዳጅ ሁኔታ የተገኘ ማስረጃ እንደማስረጃ አይቆጠርም የሚለው የሕጎች ሁሉ የበላይ ነው የሚገባለው እና በፍቃዱ ከጓዶቹ ጋር ሆኖ ይከበር! ሲል የነበረው ሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 19.5 እንዲህ ይላል


‹‹የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ  በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችልየእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም፡፡ በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነትአይኖረውም፡፡››

Monday, October 19, 2015

የብአዴን የቀድሞ ታጋዮች መንገድ ላይ ወጥተው በመለመን ላይ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡

ጥቅምት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብአዴን የተመሰረተበትን 35ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ በማድረግ የተለያዩ ጋዜጠኞችንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ያካተተ ጉዞ ላይ ፣ የትግል ተሞክሮ እንዲያካፍሉ የተጋበዙት የቀድሞ ታጋዮች በርካታ ጓዶቻቸው መጠለያ በማጣት በየከተማው በላስቲክ ቤት መንገድ ላይ እንደሚኖሩ ለጎብኝዎች ተናግረዋል፡፡

‹‹ ህዝብ እንደኖረው ለመኖር ዕድሉን አልተሰጠንም፡፡ ›› የሚሉት ነባር ታጋዮች ገዥው መንግስት፣ድርጅታቸውም ሆነ በየአካባቢው የሚያገለግሉ ባለስልጣናት « ኢትዮጵያን በክፉ ቀን ከአረመኔው አገዛዝ ያወጡ ፤ ጊዜያቸውንና አካላቸውን መስዋዕት ያደረጉ ናቸው በማለት ግምትና ዋጋ አልተሰጠንም ›› በማለት በለቅሶ ለጎብኝዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

በአዋሽ መልካሳ አንድ የፌደራል ፖሊስ ተገደለ

ጥቅምት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፖሊሱ የተገደለው በከተማዋ ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ተጣልቶ ነው። ፖሊሶች አንድ የግሮሰሪ ሰራተኛን ሲደበድቡ ፣ ወጣቶች በብስጭት በፌደራል ፖሊሱ ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን ለማወቅ ተችሎአል።

በከተማዋ ከፍተኛ ግርግር መኖሩን የተናገሩት ነዋሪዎች፣ በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላት ገዳዮችን ለመያዝ ጥረት እያደረጉ ነው። የከተማው ወጣቶች የፌደራል ፖሊስ አባላት ከፍተኛ የሆነ ጫና እንደሚፈጥሩባቸው ለኢሳት ገልጸው፣ አሁኑ እርምጃም በወጣቶችና በፖሊሶች መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መሄዱን ያሳያል ብለዋል። “ህዝቡ ቢናገር፣ ቢደበደብ ችግሩን የሚያይለት የለም” የሚሉት ነዋሪዎች፣ በከተማው የተሰማራው የፌደራል ፖሊስ በወጣቱ ላይ የፈለገውን የማሰቃያ ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን ይገልጻሉ።

የአለም የመገናኛ ብዙሃን ስለኢትዮጵያ ድርቅ ሰፊ ሽፋን በመስጠት ላይ ናቸው

ጥቅምት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከታላላቆቹ የአለም የመገናኛ ብዙሃን መካከል ዘ ኒውዮርክ ታይምስና ቢቢሲን ጨምሮ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ስለተከሰተው ድርቅ የዜና ሽፋን በመስጠት ላይ ሲሆን፣ ዘ ኒዮርክ ታይምስ ባወጣው ዘገባ ድርቁ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል።

“ያሲን ሙሃመድ ከአነስተኛ የእርሻ ማሳው ላይ እየወሰደ ጫት ይቅማል፣ ለምን ተብሎ ሲጠየቅ ፣ ጫት ረሃብን ያስታግሳል “የሚል መልስ መስጠቱን የዘገበው ዘ ኒዮርክ ታይምስ፣ በመኢሶ አካባቢ ለወትሮው በክረምት ወር ይዘንብ የነበረውን ዝናብ ዘንድሮ አንድ ጊዜ ብቻ መዝነቡን ገልጿል።
ይህ ኢትዮጵያ በ10 አመታት ውስጥ የገጠማት ከባዱ ድርቅ ነው ያለው ጋዜጣው፣ ነዋሪዎች መሰደድ መጀመራቸውን ይገልጻል። የ50 አመቱ ጎልማሳ አቶ ያሲን፣ በሰአት ምግብ መመገቡን ማቆሙን ገልጾ፣ እስከ ሚቀጥለው የመኸር ወቅት ከብቶቹን ቢሸጥ እንኳን ቤተሰቡን ለማቆየት እንደማይችል ገልጿል።

የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አባላት ለሌላ ቀን ተቀጠሩ

ጥቅምት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ስብሰባ አውካችሁዋል በሚል ወንጀል የተከሰሱት የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ማህበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አለነ ማህፀንቱና የቀድሞ የፓርቲው አባል አቶ እስማኤል ዳውድ መከላከያ ምስክሮቻቸውን ሳያሰሙ እንደተቀጠሩ ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

አቶ እስማኤል ዳውድና አቶ አለነ ማህፀንቱ እስር ቤቱ” መኪና ላገኝ ስላልቻልኩ” ተከሳሾቹን ላቀርብ አልቻልኩም፤ በማለቱ የተነሳ መዝገባቸውን እየተመለከተ የሚገኘው የአራዳ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 5ኛ ወንጀል ችሎት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷቸዋል፡፡ እስማኤል ዳውድ ለጥቅምት 25 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠው ሲሆን፣ አቶ አለነ ማህፀንቱ ለጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም ተቀጥረዋል።

Sunday, October 18, 2015

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጀርባ – አርበኞች ግንቦት 7


ከሁለት አመት በፊት በቂ ህዝባዊ ምክርና ውይይት ያልተካሄደበት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተግባር ላይ ለማዋል የተደረገው ሙከራ በበርካታ የኦሮሞ ተማሪዎች ተቃውሞ እንደገጠመውና በየኮሌጁ በተነሱ ተቃውሞዎች ሳቢያ በርካታ ወጣቶች በወያኔ እንደተገደሉ ብዙዎች በእስር እየማቀቁ እንዳሉ ይታወቃል። ግጭቱ የፈጠረው ቀስል ገና ባላገመ ማግስት በአሁኑ ወቅት የህወሃቱ አባይ ጻሀይ በውድም በግድም ፕላኑ “ይተገበራል” ብሎበዛተው መሰረት ተግባር ላይ ለማዋል ሰሞኑን ሽር ጉድ ተይዟል።

ከዚህ ማስተር ፕላን በስተጀርባ የተደበቀው የህወሃትና ጀሌዎቹ አላማ በአግባቡ አለመተንተኑ የፕላኑ ተቃዋሚዎች ኦሮሞዎች ብቻ በመሆናቸው ጥያቄው የግዛት ስፋትና ጥበት ወይም ባለቤትነት ጉዳይ መስሎ ይታይ እንጂ ነገሩ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያስቆጪና ተቃውሞ ሊያስነሳ የሚገባው ደባ ነው። ከህወሃት/ ወያኔ ማስተር ፕላኑ ጀርባ የመሬት ዝርፊያ እቅድ እንዳለው አርበኞች ግንቦት 7 ከእስከ አሁኑ ተመክሮና ባህሪያቸው በግልጽ ማየት ይቻላል ብሎ ያምናል።

ውሸት ውሎ አድሮ መጋለጡ አይቀርም!!!


def-thumbሥልጣንን በጠመንጃ አፈሙዝ ተቆጣጥሮ ያለው የወያኔ አገዛዝ ካለመታከት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ተአምር ሊመስል በሚችል  መንገድ እያሳደኩ ነው እያለ ሲዋሽ አመታት ተቆጥረዋል። በተለይ ምዕራባዊያንን ሲያታልልበት የነበረው የዲሞክራሲ ጭንብል በምርጫ 97 ከተገፈፈበት ወዲህ ላለፉት አስር አመታት ባለ ሁለት አሃዝ እድገት አስመዝግቤያለሁ እያለ እጅ  እጅ እስኪለን ድረስ በባዶ ሜዳ ስለ ልማትና የዕድገት ሲነግረን ሰነበቷል።
ወያኔ በጉልበት በሚያስተዳድራት ኢትዮጵያ የልማትና የእድገት ፕሮፓጋንዳ ስለ ሰበአዊ መብትና ስለዲሞክራሲ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለማፈኛና አፍ ለማዘጊያነት በማገልገል ላይ ይገኛል ። አለማቀፍ የሰባአዊ መብት ተቋማት ስለሰበአዊ መብት ጥሰት ለሚያቀርቡት አቤቱታ ሁሉ የሚሰጠው መልስ “ኢኮኖሚውን እያሳደግን ነው” የሚል ነው። ኢኮኖሚ ማደግ አለማደጉን ትርጉም የሚኖረው ከህዝብ የእለተ ተእለት ኑሮ ጋር ሲያያዝ መሆኑ ሁሉ  ትርጉም አጥቷል። ራበኝ የሚለው ሰው ሁሉ ጠገብኩ ማለቱ ነው ተብሎም ይተረጎማል።

Friday, October 16, 2015

ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት የዲጂታል ሸግግር በሙስና ምክንያት በታቀደው መሰረት ሳይሳካ ቀረ

ጥቅምት ፭ (አምት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ለሚደረግ የቴክኖሎጂ ሽግግር ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ቢደረግም አልተሳካም። ፕሮጀክቱ በ2001 ዓም ተጀምሮ በ3 አመታት ውስጥ መጠናቀቅ ነበረበት።

ከብሮድካስት ባለስልጣን የወጣ መረጃ እንደሚጠቁመው ስራው ሊሳካ ያልቻለው በሙስናና በብልሹ አሰራር ምክንያት ነው። ሀገር አቀፍ የሬዲዮና የቴሌቭዥን የማስፋፊያ ማሻሻያ በ2001 ተጀምሮ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የመሳሪያ ግዥና የህንጸ ግንባታ ተጠናቆ የማሰራጫ መሳሪያዎቹን በመትከል ስርጭት ይጀምራል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም፣ በሙስና ምክንያት የተገዡት መሳሪያዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆኑ ሥራው እስካሁን ሊሳካ አልቻለም፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የዋጋ ንረቱን እያባባሰው ነው ተባለ

ጥቅምት ፭ (አምት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአገሪቱ የሚታየው የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት እጥረት ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ ለታየው አጠቃላይ የዋጋ ንረት መባባስ አንድ ምክንያት መሆኑን ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘ አንድ የጥናት ሰነድ ጠቆመ፡፡

በምግብ ነክ ምርቶች ላይ ማለትም በምግብ ዘይት፣ ዱቄት፣ ፓስታና ሞኮረኒ፣ በዳቦ ምርቶች ላይ የተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ አንዱስትሪዎች በኤሌክትሪክ እጥረት ምክንያት ከማማረት አቅማቸው በታች ለማምረት በመገደዳቸው በገበያ ላይ የምርት እጥረት አጋጥሞአል፡፡ በዚህም ምክንያት ሁሉም ዓይነት ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን ጥናቱ ጠቁሞአል፡፡
ከዚህም ችግር ጋር ተያይዞ እንደምግብ ቤቶች ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ሙሉ ጊዜያቸውን በስራ ላይ ማሳለፍ ባለመቻላቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ዋጋቸው ላይ ጭማሪ ለማድረግ ተገድደዋል፡፡ የነዳጅ ዋጋ መረጋጋት የትራንስፖርት ዋጋ እንዲረጋጋ ያደረገ ቢሆንም፣ ከክልሎች ተጓጉዘው ለአዲስአበባ ገበያ የሚቀርቡ እንደምስር፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጎመን፣ ቃሪያና የመሳሰሉ ምርቶችም ላይ የዋጋ ጭማሪው በከፍተኛ ደረጃ መንጸባረቁ ታውቆአል፡፡ የአሁኑ የዋጋ ንረት ሁለንም ዘርፎች የሚነካ መሆኑ ሲታይ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጫና ያስከተለ መሆኑን መረዳት ይቻላል ያለው ይህ ጥናት ፣ መንግስት ችግሩ መኖሩን ቢያውቅም ህዝቡን ግን ለመታደግ አቅም አጥሮት ታይቶአል ሲል ይተቻል፡፡

በሽብርተኝነት ሕግ ተከሰው አንድ ዓመት ከአምስት ወራት በእስር ሲንገላቱ የቆዩት የዞን ፱ ጦማሪያን በነጻ ተሰናበቱ

ጥቅምት ፭ (አምት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አንደኛ ተከሳሽ ሶሊያና ሽመልስ በሌለችበት፣ሶስተኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ ፣ አምስተኛ ተከሳሽ አጥናፍ ብርሃኔ፣ስድስተኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላ፣ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ የተሰናበቱ ሲሆን፣ ሁለተኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ ከሽብር ክስ ነፃ የተባለ ቢሆንም ማአከላዊ ምርመራ በኃይል እና በማሰቃየት የሰጠው ቃል ላይ አመፅ እንዳነሳሳ አምኗል በሚል በወንጀል ህጉ 257 መሰረት እንዲከላከል ይሁን እንጅ ዋስትና መጠየቅ እንደሚችል ፍርድቤቱ ወስኗል።

የጦማርያኑ ጠበቃ በፍቃዱ ይግባኝ እንዲሰጠው የጠየቁ ሲሆን አቃቤ ሕግ ተቃውሞ አሰምቶ ይግባኙ ላይ ለመወሰን ለጥቅምት 10 ለማየት ቀጠሮ ሰጥቷል። በነጻ እንዲለቀቁ የተወሰነላቸው ጸሃፊዎች የመፍቻ ወረቀት አልደረሰንም በሚል እስር ቤቱ ሳይፈታቸው በመቅረቱ ቅዳሜና እሁድን በእስር ቤት ሊያስልፉ ይችላሉ። ምንም እንኳ ጸሃፊዎቹ በነጻ የተለቀቁ ቢሆንም አሁንም እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ጋዜጠኞችም በእስር እየተንገላቱ ነው።

የኔዘርላንድስ ፖሊስ አንድ በቀይ ሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ ኢትዮጵያዊን አሰረ

ጥቅምት ፭ (አምት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ማንነታቸው ያልተገለጸው የ61 አመቱ ኢትዮጵያዊ አምሰተልፊን በምትባል ከተማ ውስጥ የተያዙ ሲሆን፣ ግለሰቡን ወደ ኢትዮጵያ ይመለሱ ወይም አይመለሱ የሚልውን ውሳኔ ለመስጠት ፍርድ ቤቱ የ90 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ግለሰቡ በደብረማርቆስና መተከል አውራጃዎች በርካታ ሰዎችን መግደላቸውንና ማሰራቸውን በውጭ አገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን መረጃ መሰብሰቡን ፖሊስ አስታውቋል። በግለሰቡ ላይ ቀድም ብሎ የሞት ፍርድ ተፈርዶ የነበረ ቢሆንም፣ ፍርዱ ወደ እድሜ ልክ እስር መለወጡን የጠቀሰው የፍትህ ሚኒስቴር ዘገባ፣ በፍተሻ ወቅት 2 ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እና ወታደራዊ ዶክመንቶች መገኘታቸውን ገልጿል። ግለሰቡ የሆላንድ ዜግነት ያለው ሲሆን፣ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ነው ብሎ ካመነ የዜግነት መብቱን በማንሳት ወደ ኢትዮጵያ ሊልከው ይችላል።

ዞን 9 ጦማሪያን በነጻ እንዲሰናበቱ ፍርድቤት ወሰነ

ኢሳት ዜና (ጥቅምት 5፡ 2008)

የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድቤት በሽብርተኛ ወንጀል ክስ፣ የክስ ሂደታቸው በመታየት ላይ የነበሩ አራት ጦማሪያን ከተከሰሱበት የሽብር ወንጀል መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ ዛሬ አርብ ወሰነ።
በጦማሪያኑ ላይ የመጀመሪያ ዙር ውሳኔውን ይሰጣል ተብሎ የተጠበቀው ፍርድ ቤቱ በጦማሪያኑ ክሳቸውን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በአንድ አመት በላይ የቆየው የእስር ጊዜያቸው አብቅቶ በነጻ እንዲሰናበቱ ትዕዛዝ መስጠቱ ታውቋል።
ይሁንና ተከሳሽ በፍቃዱ ሃይሉ ከተመሰረበተ የሽብርተኛ ወንጀል ነጻ ተብሎ አመጽ ቀስቃሽ ናቸው የተባሉ ጹሁፎቹ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ እንዲከላከል ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መስጠቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

Thursday, October 15, 2015

መንግስት ለመከላከያ ሰራዊት ምዝገባ አዲስ ቅስቀሳ ጀመረ

ጥቅምት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ካለፈው አመት ጀምሮ እንደ አዲስ በተጀመረው የሰራዊት ምልመላ የተፈለገውን የሰራዊት ቁጥር ማግኘት የተቸገረው መንግስት፣ ሰሞኑን ደግሞ በአንዳንድ ክልሎች የመከላከያ ሰራዊት አባላት በመኪና ላይ ሆነው ወጣቱ ለውትድርና እንደሚዘገብ በመቀስቀስ ላይ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ለእያንዳንዱ ቀበሌና ወረዳ የተሰጠው ኮታ ሊሟላ ባለመቻሉ፣ መንግስት በስራ ስልጠና ስም ወጣቶችን በመቀስቀስ ያለፍላጎታቸው እንዲዘምቱ ለማግባባት ሙከራ አድርጓል። ይሁን እንጅ መረጃው በሚዲያ መለቀቁን ተከትሎ፣ ወጣቶች በስራ ስልጠና ስም የሚደረገውን ቅስቀሳ ባለመቀበላቸው አብዛኞቹ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ሰው አልባ ሆነው ቆይተዋል።
ሰሞኑን በኦሮምያና በደቡብ የመከላከያ ሰራዊት አባል መንግስት የስራ እድል ፈጥሮላችሁዋል እና ተመዝገቡ በማለት በመቀስቀስ ላይ ሲሆኑ፣ ህዝቡ ” የስራ እድል ተፈጥሯል” በሚል ለሚቀርበው ቅስቀሳ የሚሰጠው መልስ ፌዝ ብቻ ሆኗል ሲል የደቡብ ተወካይ ጠቅሷል።

በሁመራ ከ500 በላይ የሞተር አሽከርካሪዎች ስራ እንዲያቆሙ ታዘዙ

ጥቅምት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሞተር ሳይክል ሰዎችን ከቦታ ቦታ በማዘዋወር ህይወታቸውን የሚመሩ 500 ያክል ወጣቶች ስራ እንዲያቆሙ በመታዘዛቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል።

ሰራተኞቹ በድንገት አቁሙ በመባላቸው፣ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር ተቸግረዋል። መንግስት አማራጭ ስራ ሳይፈጥር በድንገት ስራ አቁሙ ማለቱ ተገቢ አይደለም በሚል ወጣቶቹ ያስነሱትን ተቃውሞ ተከትሎ የወረዳው ባለስልጣናት ተጨማሪ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ሰጥተዋል።
አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ወጣት እንዳለው ሞተረኞች ለጸረ ሳላም ሃይሎች የተለያዩ መሳሪያዎችን ያቀብላሉ በሚል ምክንያት ለመቅጣት ታስቦ የተደረገ ነው ብሎአል።
ከተማው በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት ሳይኖረው፣ የህዝቡን የትራንሰፖርት አግልግሎት ችግር በመቅረፍ ላይ እያለን መበረታታት ሲገባን፣ ስራ አቁሙ መባላችን ተገቢ አይደለም በማለት ወጣቶች ተቃውሞአቸውን ለኢሳት ገልጸዋል።

በሰሜን ጎንደር የአርባ ፀጓር ፀባሪያ ነዋሪዎች ባለፉት ሃያ አራት ዓመታ ውስጥ ብአዴን ምንም እንዳልሰራላቸው ተናገሩ

ጥቅምት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በተከዜ ወንዝ ጫፍ ላይ የምትኘውና የዋግና የበለሳ ነዋሪዎች መተላለፊያ የሆነችው አርባ ፀጓር ወረዳ ደርግን ለመጣል በተደረገው የትግል ወቅት የኢህአፓና የኢሕዲን መተላለፊያ መስመር የነበረች ሲሆን በወቅቱ የድሮው ኢሕዲን የአሁኑ ብአዴን ታጋዮች የነበሩት ለሕዝቡ የኑሮ ለውጥና ዴሞክራሲያ ስርዓት እንደሚገነቡ ቃል በመግባታቸው ነዋሪው ሸማቂዎቹን በማገዝ ከለላ ይሰጣቸው የነበረ ሲሆን ድል አድርገው መንበረ ስልጣኑን ከያዙ በኋላ ግን ቃላቸውን በማጠፍ ምንም የልማት ስራዎች እንዳልተሰራላቸው ነዋሪዎቹ ምሬታቸውን ገልፀዋል።

በቀበሌው ነዋሪዎቹ የተነሱ አሳዛኝ ልብ ሰባሪ ጥያቄዎች፣ አብዛኛውን ታዳሚ ያስለቀሱ ሲሆን ለአስራ አንድ ዓመታት አርባ ፀጓር ፀባሪያ ቀበሌን በሊቀመንበርነት የመሩት የአካባቢው ነዋሪ እንዳሉት ”“በዚህ አካባቢ አንዳንድ ውርውር ከሚሉ ቆርቆሮዎች በስተቀር በልማት ተጠቃሚ ነን ብሎ መናገር አይቻልም። ለምን ከተባለ፣ እኛ የደም ዋጋችንን ስጡን እያልን ሳይሆን፣ ሌላው ሕብረተሰብ እንደሚያገኘው ከልማቱ ተጠቃሚ እንሁን ነው ጥያቄያችን። እንደሚታወቀው ደርግን ስንጥል ችግራችን ሁለት ዓብይ ነገሮች ነበሩ። አንዱ ራሱ ደርግ ነበር። ሁለተኛው ግን የተፈጥሮ ድርቅ ነበር። ሁለቱንም አጣምረን ደርግን መጣል ችለናል። ”

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ፥ ESFNA ቶሮንቶን በአዘጋጅነት መረጠ

ጥቅምት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ፥ ESFNA በካናዳ የቶሮንቶን ከተማ የ2016 የስፖርት ክብረ በዓል ዓስተናጋጅ እንድትሆን መርጧል።

ውሳኔው የተላለፈው፥ በኢትዮ-ስታር ቶሮንቶ የእግር ኳስ ክለብ ዓስተባባሪነት በቶሮንቶ ካናዳ በተዘጋጀው፥ የESFNA ዓመታዊ ጉባኤ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ የክለብ ተዎካዮችና የቦርዱ ዓመራር ዓባላት በተገናኙበት፥ ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ October 10 እና 11, 2015 የፌዴሬሽኑ ዓመታዊ የስራ ጉብኝት ላይ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች በፈጠሩት ችግሮች የኦሞና የቱርካና ሃይቅ የመድረቅ አደጋ ከፊታቸው ተጋርጧል ተባለ

ጥቅምት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙት የቱርካና ሃይቅና የኦሞ ወንዝ ኢትዮጵያ በምትከተለው የኢንዱስትሪ ዘመቻ ምክንያት የመድረቅ እና የአየር ንብረት መዛባት አደጋን ማስከተሉንና በዚህም ለውጥ ሳቢያ የአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ሂውማንራይትስ ወች በጥናት ሪፖርቱ አመልቷል።

በሰሜናዊ ምዕራብ ኬንያ በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ የሚገኘው የቱርካና ሃይቅ በዓለማችን በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ ሃይቆች አንዱ ሲሆን ዘጠና በመቶ የሚሆነውን ውሃ ከኦሞ ወንዝ ያገኛል። ኢትዮጵያ ግድቦችን በመስራት የውሃውን ፍሰቱን በማቆሟ ምክንያት በኦሞ ሸለቆ ውስጥ የሚኖሩ አርብቶ አደር ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያንን ጨምሮ በአካባቢው የአየር ንብረት ላይ መዛባት ስለሚያስከትል ነዋሪዎቹ ለችግር ተጋልጠዋል።
ወንዙን ለሸንኮራ አገዳ ምርት ለመጠቀም መታሰቡ የአርብቶ አደሩን የወደፊት ዕጣ ፈንታና ዝርያቸው አናሳ የሆኑትን ዜጎች በህልውና ስጋት ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል። የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የኢትዮጵያ መንግስት የአካባቢውን ነዋሪዎች ያማከለ የልማት ዕቅድ ተግባራዊ እንዲያደርግ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።