Wednesday, February 17, 2016

ሀሰቱም ያብቃ፤ ዳር-ድንበር መሸጡም ይቁም! (ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሜቴ የተሰጠ መግለጫ)

ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሜቴ የተሰጠ መግለጫ
የካቲት 8 ቀን 2008 ዓ/ም  (February 16, 2016)

ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ በአገራችን የተከሰተው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሰሞኑን የተጀመረ ለማስመሰል እንደሚሞክረው ሳይሆን፤ ሕወሓት ካለፉት በርካታ ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየፈፀመ ያለው ግፍና መከራ ድምር ውጤት ነው። ብሶቱም መጠነ ሰፊ፤ ጊዜውም ከ25 ዓመት በላይ ያስቆጠረ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው።
በተለያዩ ክፍለ አገራት ያሉ ወገኖቻችን ለዘመናት ይኖሩበት ከነበሩበት መንደሮች በልማት ስም በኃይል እየተፈናቀሉ የትም እንዲወድቁ ሲደረጉ፤ አንድም ቀን ይህን የሕወሓትን ግፍና መከራ በፀጋ የተቀበሉበት ጊዜ አልነበረም።
ከአፍንጫው ራቅ አድርጎ ማሰብ የማይችል አምባገነን አገዛዝ አንድ ሕዝብ በቁጣ በተነሳ ቁጥር ማስታገሻው ወይም እንደነሱ አባባል ማርከሻው ሕዝቡን በኃይል “ፀጥ” ማድረግ ነው። “ፀጥ” እናደርጋቸዋለን የሚሉ ወገኖች አንድ ቀን ራሳችው ፀጥ እንደሚሉ ስለማይገነዘቡ የማይቀረውን የቁልቁለት መንገድ ይያያዙታል። ያኔ ኃይል የነሱ ሳይሆን የሕዝብ መሆኑን ሳይወዱ በግድ ይረዱታል።

በሰሞኑ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ከሕዝብ በተነሱ ዐበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ ከሰሜን ኢትዮጵያ አንስቶ እስከ ጋምቤላ ድረስ ያለውን ለም የድንበር መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የተጀመረው ሴራ እንዳይተገበር ሕዝቡ አጥብቆ የመጠየቁ ጉዳይ ነው።
ይህን የአገርን ድንበር አሳልፎ የመስጠት ሤራን ሕዝባዊ ተቃውሞ ከመጀመሩ አንድ ወር በፊት የወያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለወያኔ ፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ በእሳቸው አባባል “… እነዚህ ኃይሎች (ተቃዋሚዎችንና የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴን ማለታቸው ነው) መንግሥት ለሱዳን መሬት ቆርሶ ሊሰጥ ነውና ሕዝብ ሆይ ተነስ ሲሉ ጥሪ ሲያቀርቡ እንሰማለን” ነበር ያሉት።
አዎን እርግጥ ነው፤ አቶ ኃይለማርያም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተላለፈውን መልዕክት በትክክል ሰምተዋል። ሕዝቡም ጥሪውን ሰምቶና ተቀብሎ ዕቅዱ ተግባራዊ እንዳይሆን በየአካባቢው እየተንቀሳቀሰ ነው ያለው። ጥሪውን ሰምቶ ጆሮ ዳባ ያለውና መልስ ያልሰጠው ቢሰጥም የክህደት መልስ የሰጠው የእርስዎ አገዛዝ ሕወሓት ብቻ ነው። አሊያማ ክ70 በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የሲቪክ፣ የሙያና የሚዲያ ድርጅቶች የጋራ አቋም ይዘውበት፣ ሕዝቡም እስከዛሬ የተሸረሸረው አልበቃ ብሎ ሌላ የአገሪቱ ክፍል (ድንበር) አይሸነሸንም እያለ ቁጣውን ከዳር እስክዳር እያሰማ ያለው በሕወሓት ሹሞች የሚሰጠውን ገደብ የለሽ ውሸት መቀበል ስላቃተው ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኰሚቴ ድንበር የማካለሉ ተግባር “ካላንዳች ችግር” እየተካሔደ የመሆኑን ዜና የሰማው ከኢትዮጵያ በኩል ሳይሆን ከሱዳን ጋዜጣ ሱዳን ትሪቡን (Sudan Tribune) እ.አ.አ. ጥር 17 ቀን 2016  ( January 17,  2016 ) ባወጣው እትሙ ነበር።
ጉዳዩ ለአገሪቱና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠቅማል ተብሎ ከታመነበት ድብብቆሹ ለምን አስፈለገ? ለምንስ የሱዳን መንግሥት ለራሱ ሕዝብ ይፋ እንዳደረገው ሁሉ የወያኔ መንግሥት ለምን ለሕዝቡ በይፋ ሊያሳውቀው አልፈለገም?
ከፍ ሲል በጠቀስነው ንግግራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም የሐሰት መግለጫቸውን ሲያብራሩ “በመሬት ዙሪያ የተደረገ ንግግርም የለም፣ ተቆርሶ የተሰጠ ነገርም የለም” ሲሉ ጭልጥ ያለ ከነጭም የነጣ ውሸት እንደተለመደው ተናግረዋል።
በጣም የሚያሳዝነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን በተናገሩበት አንደበት ወዲያውኑ አያይዘው “… ከኛ አካባቢ እየሔዱ በርካታ ሱዳናዊያንን እየገደሉ የሚመለሱ ሽፍቶች አሉ” ሲሉ ለዘመናት በአካባቢው ነዋሪ የሆኑትንና፣ ትዳር ይዘው፣ ወልደው ተዋልደው በሰላም አርሰው የሚኖሩትን ገበሬዎች “ሽፍቶች” ብለው ካለ አንዳች ሃፍረት ማዋረዳቸውና መወንጀላቸው ነው። በርሳቸው አመለካከት በአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ ‘’ነፍሰ ገዳይ ነው፣ ወንበዴ ነው፣ ሽፍታ ነው፣ አልፎ ተርፎም ወንጀለኛ ነው።”
ቀዳማዊው መለስ ሕይወታቸውን ሙሉ ለሱዳን ሕዝብና መንግሥት ጥብቅና እንደቆሙ፣ በአደባባይ እንደተከራከሩላቸው ለዝንተ ዓለም አንቀላፉ። አሁን ደግሞ ዳግማዊ መለስ በሌለባቸው ውለታና የዘሬን ብተው ዓይነት ሆኖባቸው የራሳቸውን ሕዝብ በአደባባይና  በይፋ መወንጀል ስራዬ ብለው ተያይዘውታል።
ጥማድ በሬ አሰማርቶ፣ ክረምትና በጋን ጠብቆ፣ የሚያርስና መሐር የሚሰበስብ ገበሬ በምንም መለኪያ ቢመዘን “ሽፍታ” መሆን ቀርቶ “ሽፍታ” ሊባል የሚገባው አይደለም። ይህ “ሽፍታ” ገበሬ ግብሩን የሚከፍለው እኰ ለሱዳን መንግሥት ሳይሆን ለሕወሓት ነው። “ሽፍታ” ደግሞ እንኳንስ ግብር ለመክፈል ቀርቶ ለዕለት ቀለቡም እየዘረፈ እንደሚበላ አቶ ኃ/ማርያም አጥተውት ነው ብለን አንገምትም። አባባላቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ከመናቅ የመነጨ እንደሆነ ግን የእስከዛሬው ታሪካቸው ጉልህ ማስረጃ ነው።
አዎን የአገራቸውን ሕልውና የሚደፍርና ማንነታቸውን የሚጋፋ ባላንጣ በተነሳባቸው ቁጥር የአካባቢው ነዋሪዎች ባላቸው አቅም ንብረቶቻቸውንና ዳር ድንበራቸውን ይጠብቃሉ፣ ያስከብራሉ። መሪር የሕይወት መስዋዕትነትም ይከፍላሉ። ከአባቶቻቸው የወረሱትን ንብረትና እነ አጼ ቴዎድሮስና እነ አጼ ዮሐንስ ያስረከቡንን ዳር-ድንበር ለማስከበር በመታገላቸው በዛሬ አገር ከሃዲዎች “ሽፍታ” መባላቸው አይደንቀንም። ሽፍታውስ በአገርና በሕዝብ ላይ ያመጸ፤ ጫካ ሳይሆን ቤተመንግሥት በጉልበት ኃይል የተቀመጠው ወያኔ እራሱ ነው።
“በርካታ ኪ/ሜትር ገብተው ሱዳን ውስጥ የሚያርሱ እኛም ሱዳኖችም የሚያውቋቸው የኛ ባለሃብቶችና ውስን አርሶ አደሮችም እንዳሉ” አቶ ኃ/ማርያም አልሸሸጉም። ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል? በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ሳይሆን አቶ ኃ/ማርያም አባባሉን በአንድ ራስ ወደ 3 ምላስ ከፍ አድርገውታል። በመጀመሪያ የሚሰጥም ለመስጠት የታቀደ መሬት የለም አሉ። አያይዘውም ነፍስ እየገደሉ የሚኖሩ ሽፍቶች እንዳሉ አስታወቁን። ትንሽ ዝቅ ብለው ደግሞ ሁለቱም ወገኖች የሚያውቋቸው ቱጃር ገበሬዎች እንዳሉም መሰከሩ። መሠረቱ ውሸት ነውና መደምደሚያው ግራ የሚያጋባ ሆነ። የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሚስተር ኢብራሒም ጋሐንዶር ስለዚሁ ጉዳይ ለአልጃዚራ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፤ በተለይ አል-ፋሽጋ የሚባለው ቦታ የሱዳን መሆኑን ከገለጹ በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል ባለው መልካም ትብብር የተነሳ የሱዳን መንግሥት እነዚህ ገበሬዎች እንዲያርሱ የፈቀደላቸው መሆኑን በዝርዝር ተናግርዋል።
በሱዳን በኩል ይህን ስራ እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የተሰጠው የቴክኒክ ኰሚቴ የድንበር ከለላው ስራ በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅ ይፋ ከማድረጉም ባሻገር እስከአሁን ድረስ ሥራው አንዳችም እንቅፋት እንዳልገጠመው አበክሮ አስታውቋል።
የዚሁ የቴክኒክ ኰሚቴው ሹም ሚስተር አብደላ አል-ሳዲቅ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስነን ድንበር ርዝመቱ ወደ 725 ኪ/ሜ እንደሆነ ገልፀው፣ ወደ 600 ሺህ ኤከርስ የሚሆነው ለም የእርሻ መሬትም ይዘትነቱ የኢትዮጵያ ሳይሆን የሱዳን እንደሆነ በሚገባ አስምረውበታል።
አካባቢው እንደነ አትበራ (ጓንግ)፣ ሴቲት (ተከዜ) እና በሰላም (ባህረ ሰላም) የሚባሉ ትላልቅ ወንዞች በስም እየተጠቀሱ የሚፈሱበት አካባቢ እንደሆነና ይዞታው የሱዳን መንግሥት ነው እያሉ የአገሪቱ ባለሥልጣኖች ለዓለም ሲያሳውቁ፣ በኢትዮጵያ በኩል የሚሰጠው ምላሽ ግን “ሱዳኖች የፈለጉትን ሊናገሩ ይችላሉ” የሚል ነበር። ይህ ደግሞ የአገርን ድንበር የሚያህል ትልቅ የአገር ጉዳይ አቅሎ ማየትና ወያኔም ዛሬም ቢሆን ከስህተቱ ታርሞ ለሕዝብ ዕውነትን ለመግለጽ ፈቃደኛ አለመሆኑን በተጨባጭ የሚያሳይ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕወሓት የ25 ዓመት አገዛዝ መሮት ከዳር እስከዳር ለፍትህና ለእኩልነት በተንቀሳቀሰበት በአሁኑ ጊዜ፤ የድንበር ከለላውን ስራ እያጣደፉ እንዲካሄድ ማድረግ “አጥፍቼ ልጥፋ” ከሚል የአምባገነኖች ባህሪይና ዓላማ ውጭ ነው ለማለት ከቶ አያስደፍርም።
ሕዝቡ እናስተዳድርሃልን በሚሉ ጎጥኞች ነጋ ጠባ መዘለፉ፣ መዋረድና የሚሰነዘርበት የሐሰት ውርጅብኝ ከአቅሙ በላይ እየሆነበት መጥቷል። ዛሬ የኢትዮጵያን ሕዝብ የናፈቀው ነገር ቢኖር “ፀጥ እናደርግሃለን” የሚል አዕምሮው በዘር የተበከለ “መሪ” ሳይሆን መብትህ ይጠበቅልሃል ብሎ ማንነቱን የሚያከብርለት መሪ ነው። በባዶ እግሩ የሚሄድ ባላገር ብሎ የሚዘልፈውን ሳይሆን “አርሶ አደሩ ወገኔ” ብሎ የሚቀርበውን መሪን ነው ዛሬ ለማምጣት እየታገለ ያለው።
በመጨረሻ መስገንዘብ የምንፈልገው፤ አገርን የማስጠበቅ ኃላፊነታቸሁን ክዳችሁ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በሰተጀርባ በተዋዋላችሁት ውል መሠረት አሳልፋችሁ የምትሰጡት የአገር ዳር-ድንበር በከፍተኛ መሰዋዕትነት ተከብሮ ለዘመናት የኖረ እንደመሆኑ ሁሉ፤ ዛሬም በሚከፈለው የጀግንነት መስዋዕትነት እንደሚጠበቅ ቅንጣት ያህል ሳንጠራጠር ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን። ይልቁንስ በምትፈጽሙት የአገር ክህደት ወንጀል በሕግም ሆነ በታሪክ የምትጠየቁ መሆናችሁን ከወዲሁ እናሳውቃለን።
አገራችን በታላቅ ጀግኖች ልጆቿ ተጠብቃ፣ ታፍራና ተከብራ እንደኖሮችሁ ሁሉ፤ ዛሬም ሆነ ነገ በቆራጥ ጀግና ልጆቿ መስዋዕትነት ተጠብቃና ተከበራ ትኖራለች።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በቆራጥ ልጆቿ ይከበራል!
ድል ለጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!

No comments:

Post a Comment