Friday, February 26, 2016

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት የእሰረኞች ሰንድ እንዳይወጣ አገደ

የካቲት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በፌደራል አቃቤ ህግ ይግባኝ ተጠይቆባቸው ጉዳያቸውን ከከቃሊቲ እስር ቤት በመመላለስ በጠቅላይ ፍርድ ቤት እየተከታተሉ የሚገኙት የቀድሞው አንድነት፣ የሰማያዊ እና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት ማዕከል፣ አቃቤ ህግ ባቀረበባቸው ማስረጃ ላይ የሰነድ አስተያየታቸውን ለማቅረብ ያዘጋጁትን ጽሁፍ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዳይወጣ እንደከለከላቸው ገለጹ፡፡

ከእስር ተፈቶ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እየተከታተለ የሚገኘው የቀድሞው አንድነት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው 8 ገጽ ያለው የሰነድ አስተያየቱን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡
የካቲት 18/2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት የቀረቡት ይግባኝ መልስ ሰጭዎች አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ እና መምህር አብርሃም ሰለሞን ሲሆኑ፣ መዝገባቸው ለዛሬ የተቀጠረው የሰነድ አስተያየታቸውን ለመቀበል ነበር፡፡ ሆኖም በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኙት አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አቶ የሺዋስ አሰፋና አቶ አብርሃ ደስታ ያዘጋጁትን የሰነድ አስተያየት በማረሚያ ቤት አስተዳደር ክልከላ ምክንያት አለማቅረባቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
‹‹የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ‹ደህንነት› የሚል ጽሁፍ አለበት፣ ስለዚህ አይወጣም አሉን፡፡ ለፍ/ቤት እንደሚቀርብ ብንነግራቸውም እነዚህን ቃላት አስወጡ ተብለን ተከልክለናል›› ሲል አቶ አብርሀ ደስታ ገልጹዋል፡፡ ይግባኝ መልስ ሰጭዎቹ፣ የሰነድ አስተያየታቸውን ሲያዘጋጁ ከቀረበባቸው ማስረጃ በመነሳት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ሺበሺ በበኩሉ ‹‹ኢህአዴግ የሚለውን ቃል አውጣ›› ተብያለሁ ብሏል፡፡ ‹‹ሠማያዊ ፓርቲ ማለት አትችልም›› የተባለው ደግሞ የሺዋስ አሰፋ ነው፡፡ ይግባኝ መልስ ሰጭዎቹ ‹‹ለማስረዳት ብንሞክርም አልሰሙንም›› በማለት አቤቱታቸውን አሰምተው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
ዳኛ ዳኜ መላኩም ለማረሚያ ቤቱ ተወካይ ‹‹እናንተ ጋር አይደለም ሳንሱር መደረግ ያለበት……ማረሚያ ቤት አይመለከተውም፡፡ ጉዳዩን ፍ/ቤት ነው የሚያየው››፣በማለት ያዘጋጁትን ጽሁፍ እንዳለ ይዘው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ እንዲፈቀድላቸው አዝዘዋል፡፡
በሌላ በኩል የሰነድ አስተያየቱን ያቀረበው አቶ ሀብታሙ አያሌው ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ከሰጠው ትዕዛዝ ውጭ በስር ፍርድ ቤት ያልቀረበ 72 ገጽ አዲስ ፍሬ ነገር አሁን በቀረበው ማስረጃ ላይ ተቀላቅሎ መቅረቡን በአስተያየቱ ላይ አመልክቷል፡፡ ፍ/ቤቱ ዛሬ የተቀበለው የአቶ ሀብታሙን አስተያየት ብቻ ሲሆን፣ ቃሊቲ በእስር ላይ የሚገኙት ይግባኝ መልስ ሰጭዎች ያላቸውን የሰነድ አስተያየት ማቅረባቸውን ለመጠባበቅ ለየካቲት 22/2008 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment