Wednesday, June 29, 2016

በአዲስ አበባ ቤታቸው ይፈርስባችሁዋል የተባሉ ነዋሪዎች ባስነሱት ተቃውሞ ፖሊሶች ተገደሉ

ሰኔ ፳፪ ( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በወረዳ አንድ በተለምዶ ቀርሳ፣ ኮንቶማ፣  ኤንቱ ሞጆ፣ ዱላ ማርያም፣ ሰፈራ፣ ማንጎ፣ ገብሬአል በሚባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ አባወራዎችና እማወራዎች የሚኖረባቸውን አካባቢወች በማፍረስ መሬቱን ለባለሀብቶች ለመስጠት የተጀመረውን እንቅስቃሴ የተቃወሙ ነዋሪዎች ከጸጥታ ሃይሎች  የተሰነዘረባቸውን ጥቃት ተከትሎ ድንጋዮችን በፖሊሶች ላይ ወረውረዋል።

የመብራት ሃይል ሰራተኞች ኮንቶማ እና ማንጎ ሰፈር በሚባለው አካባቢ የሚገኘውን የሃይል ማስተላለፊያ ትራንስፎርመር ለመንቀል ሲሞክሩ ህዝቡ ተቃውሞ አሰምቷል።  በተቃውሞው 3 ፖሊሶች እና አንድ የመስተዳድሩ ሰራተኛ ሲገደሉ፣ ከ20 ያላነሱ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

በምእራብ ጎጃም ደንበጫ ከተማ የተጀመረው የመምህራንና የተማሪዎች ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው

ሰኔ ፳፪ ( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ካለፉት ሶስት ቀናት ጀምሮ በደንበጫ የተጀመረው የተማሪዎች እና የመምህራን አድማ መቀጠሉን ተከትሎ ፣ፖሊሶች በሃይል በወሰዱት እርምጃ በርካታ ተማሪዎች ተጎድተዋል። ቁጥራቸው በውል ያልተወቀ የ11ኛ እና የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች ተይዘው መታሰራቸውን የገለጹት ነዋሪዎች፣ ግጭቱ ዛሬም ቀጥሎ ውሎአል ብለዋል::

መምህራን የጠየቅነው የደሞዝ ማስተካከያ ካልተደረገ የተማሪ ውጤት አንሰጥም ማለታቸውን ተከትሎ፣ ተማሪዎች ከመምህራን ጎን በመቆም ተቃውሞ ማሰማት ሲጀምሩ፣ ፖሊሶች ተማሪዎችን እየደበደቡ አስረዋል። ዛሬ ተማሪዎች እየተፈተሹ ወደ ትምህርት ቤት ከገቡ በሁዋላ እንደገና ተቃውሞአቸውን የቀጠሉ ሲሆን፣ መምህራንም መልቀቂያ ስጡን እንጅ አንሰራም በሚል አድማውን አጠናክረዋል። የወረዳው ባለስልጣናት ችግሩን በሃይል ለመፍታት ሙከራ ማድረጋቸው በአካባቢው ያለውን ውጥረት እንዳባባሰው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በሃመር ወረዳ የተጀመረው ግጭት መቀጠሉ ተሰማ

ሰኔ ፳፪ ( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሃመር እና ኤርቦሬ ጎሳዎች መካከል የተጀመረው ግጭት ተባብሶ በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ችግሩ ከግጦሽ መሬት ጋር በተያያዘ ይጀመር እንጅ፣ ከትናንት ጀምሮ መልኩን በመቀየር በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሎአል።
የአገር ሽማግሌዎች ችግሩን ለመፍታት ጥያቄ ሲያቀርቡ የዞኑ የፖለቲካ ምክትል ሃላፊና የሀመር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ወሌ ለአገር ሽማግሌዎች_ አርበኞች ግንቦት7 ቶች እዚህ አካባቢ ገብተዋልና ጥንቃቄ አድርጉ በማለት ጉዳዩን ወደ አልሆነ አቅጣጫ በመውሰዳቸው የሽምግልናው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። አስሌ በሚባለው ቀበሌ አካባቢ ግጭቱ መባሳሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከመከላከያ ሰራዊት ተሰናብተው በየከተማው የሚገኙ ዜጎች ችግር ላይ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡

ሰኔ ፳፪ ( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እሁድ ሰኔ 19/2008 በብቸና ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ቅሬታቸውን ያቀረቡት የተመላሽ ሰራዊት አባላት በደረቅ ቆሻሻ ተሰብስበው በመሰማራት ኑሯቸውን በመግፋት ላይ ቢሆኑም የመንግስት አመራሮች ግን ከእርዳታ ይልቅ ጥላቻ እያሳዩዋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወደ መከላከያ ሰራዊቱ እንዲገቡ በርካታ እንክብካቤና የማስመሰያ ቅስቀሳ ተደርጎላቸው እንደተሸኙ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች በተቀናሽነት ሲመለሱ ግን አግባብ ባልሆነ አቀባበል እንደተቀበሉዋቸው ይናገራሉ፡፡
በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ከፍተኛ መከራና ስቃይ ሲያዩ ቆይተው ለሃገራቸው ምድር ቢበቁም ከወረዳ አመራሮች የጠበቃቸው በጥላቻ የተሞላ መስተንግዶ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ገልጸው፤ ከሁሉም አቅጣጫ ድጋፍ በመነፈጋቸው በችግር ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

Tuesday, June 28, 2016

የህወሃት አባላት ያልሆኑ የደህንነት አባላት በጥርጣሬ እየታሰሩ ነው

ሰኔ ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት አባል የነበሩና በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ በተለይም በሶማሊያ በሚካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ላይ ቁልፍ ሚና ነበራቸው የተባሉ 3ቱ ነባር የደህንነት አባላትና አስተባባሪዎች ከተገደሉ በሁዋላ፣ ከግድያው ጀርባ እጃቸው ሊኖርበት ይችላል ተብለው የተጠረጠሩ የህወሃት አባላት ያልሆኑ የሌሎች ብሄረሰቦች የደህንነት አባላት እየተያዙ ነው። እስካሁን ከተያዙት መካከል አብዛኞቹ የኦሮሞ ተወላጅ የደህንነት አባላት ሲሆኑ፣ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጠበቂዎችም ይገኙበታል።

በአልሸባብ ተይዘው የነበሩትን የኢትዮጵያን ወታደሮች እና አንድ የፈረንሳይ የስለላ አባል ለማስለቀቅ ተልእኮ ተሰጥቷቸው የነበሩና ተልእኮዋቸውን በስኬት የተወጡ ኮማንዶችም ታስረዋል።  ኮማንዶዎቹ ታጋቾችን ሲያስለቅቁ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚከፈላቸው ቃል ተግብቶላቸው የነበረ ሲሆን፣ ተልእኮዋቸውን ከፈጸሙ በሁዋላ ግን አብዛኛውን ገንዘብ ወታደራዊ አዛዦች እንደነጠቁዋቸው፣ ይህንንም በመቃወማቸው ለእስር ተዳርገው እንደበሩ ታውቋል። ከአሁኑ ግድያ ጀርባ እጃቸው ሊኖርበት ይችላል በሚል የተወሰኑት ተይዘው በድጋሜ ታስረዋል።

ቤታቸው በህገወጥ መንገድ ይፈርስባችሁዋላ በመባላቸው ሰዎች ተቃውሞአቸውን ገለጹ

ሰኔ ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ ወረዳ 11 በአካባቢው መጠሪያ ቀርሳና ኮንቱማ በሚባሉ አካባቢዎች ቤቶችን በህገወጥ መንገድ ሰርታችሁዋል የተባሉ ነዋሪዎች፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ቤታቸውን እንዲያፈርሱ ካላፈረሱ ግን መንግስት እንደሚያፈርስባቸው ከተነገራቸው በሁዋላ ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል።

“አንድ የአራት እናት ልጆችና የአንድ ሳምንት አራስ የሆኑት እናት “ መሄጃ የለኝም፣ መሞቴ ነው ድረሱልኝ “ ብላለች። ልጆቼን የሚረከቡኝ አካል እፈልጋለሁ፣ መንግስት ሊቀብረኝ ነው ፣ በአረብ አገር ለፍቼ የሰራሁትን ቤት አፍርሺ ተብያለሁ፣ ባለቤቱ በአደጋ በቅርቡ ሞተብኝ፣ እርዱኝ “ ብላለች።

ፍርድ ቤት እነ አቶ አግባው ሰጠኝ እንዲከላከሉ ወሰነ

ሰኔ ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ በተከሰሱ 16 ተከሳሾች ላይ ብይን የሰጠ ሲሆን፣   አቶ አግባው ሰጠኝን ጨምሮ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮነን፣  በላይነህ ሲሳይ፣  አለባቸው ማሞ፣  አወቀ ሞኝሆዴ ፣ ተስፋየ ታሪኩ፣  ቢሆነኝ አለነ፣ ተፈሪ ፈንታሁን ፣ፈረጀ ሙሉ፣  አትርሳው አስቻለው ፣ እንግዳው ቃኘው፣ አንጋው ተገኘ እና አባይ ዘውዱ ተከላከሉ ተብለዋል።

አቶ ዘሪሁን በሬ፣ ወርቅየ ምስጋናውና አማረ መስፍን መከላከል አያስፈልጋችሁም በሚል በነጻ ተሰናብተዋል። ፍርድ ቤቱ በ13ቱ ተከሳሾች ላይ የመከላኪያ ምስክር ለመስማት ለነሐሴ 18፣ 19 እና 20 ት ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ይዟል። አቶ አግባው ሰጠኝ “ብሄሬ እየተጠቀሰ  ተሰድቤአለሁ፣ ከቤተሰብና ከጠበቃ ጋር እንዳልገናኝ ጨለማ ቤት ታስሬያለሁ” በሚል የረሃብ አድማ አድርጎ ነበር።

Monday, June 27, 2016

በርሃብ በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች “ከረሃብ ወትድርና ይሻላችሁዋል” እየተባሉ ወደ ውትድርና እንዲገቡ እየተቀሰቀሱ ነው

ሰኔ  ( ሃያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመላ አገሪቱ አዳዲስ ወጣቶችን ለመመልመል የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ እክል ያጋጠመው መሆኑን ተከትሎ፣ የኢህአዴግ ካድሬዎች አዲስ የምልመላ ስልት ይዘው ብቅ ያሉ ሲሆን፣ በተለይ በአማራ ክልል ድርቅ ባጠቃቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች ለውትድርና እንዲመዘገቡ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው።

የክልሉ ዘጋቢያችን እንደገለጸው የብአዴን አባላት በሙሉ ሰሞኑን በወጣው የመከላከያ ሰራዊት ምልመላ ዙሪያ ወጣቱን እንዲቀሰቅሱ ከበላይ በመጣ ትእዛዝ መሰረት መመሪያ ሲሰጣቸው ነበር። በተለይ ድርቁ በስፋት በሚታይባቸው  የምስራቅ አማራ ወረዳዎች ወጣቱን ከረሃብ ውትድርና ይሻላል በሚል መሪ መፈክር ፣ ለወታደሩ ከፍተኛ ደሞዝ፣ ልዩ ልዩ የሙያ ስልጠና እንደሚሰጥና ከተማው ውስጥ መኖር የሚያስችል እድል እንዳለ በመንገር እንዲያስመዘግቡ አባላቱ ጥብቅ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል።

በአዲስ አበባ አትክልት ተራ “ ደረሰኝ የላችሁም” የተባሉ ነጋዴዎች ንብረታቸውን ተወረሰ

ሰኔ  ( ሃያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የከተማው መዘጋጃ በተለምዶ አትክልት ተራ ወደ ሚባለው አካባቢ በመሄድ በአነስተኛ የንግድ ስራ የተሰማሩ አትክልት ነጋዴዎችን ንብረት በመቀማት ከጥቅም ውጭ አድርጓል።

አንዳንድ ነጋዴዎች እንደገለጹት የመዘጋጃ ሰራተኞች “ ደረሰኝ አልሰጣችሁም” በሚል ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ሌሎችንም አትክልት በመቀማት እየወሰዱ በመፍጨት ከጥቅም ውጭ አድርገዋቸዋል።

በረሃብ የተጎዱ ዜጎች የእርዳታ አሰጣጡን አሰራር ነቀፉ

ሰኔ  ( ሃያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ በርሃብ የተጎዱ ዜጎች የሚቀርብላቸው እርዳታ በቂ አለመሆኑና በአንዳንድ ቦታዎች እስከ 7 ሰአት ተጉዘው 14 ኪሎ እህል ለወር ይዘው እንደሚመለሱ ተናግረዋል።

በምስራቅ አማራ እርዳታ የሚያከፋፍሉት በአብዛኛው የህጻናት አድን ድርጅትና የአሜሪካ ልማት ተራድኦ ( ዩ ኤስ አይ ኤድ) ሲሆኑ፣ ድጋፋቸው ያነጣጠረው በሴፍትኔት ለታቀፉ ተጎጂዎች ነው።
እርዳታው በየወሩ የሚሰጥ ሲሆን  ለአንድ ሰው 14 ኪሎ ግራም ይሰፈርለታል፡፡ በዚህ አገልግሎት ላይ ቀለብ የሚሰፈርላቸው በሴፍቲኔት ምግብ ለስራ ላይ ለሚሳተፉ ብቻ ሲሆን፣ በርካታ እርዳታ ፈላጊ ወገኖች በተለይ ከብት ካላቸው አይስተናገዱም፡፡ “ከብቶቻችሁን ሸጣችሁ ተጠቀሙ እንደሚባሉ ተረጅዎች ይናገራሉ።

Saturday, June 25, 2016

TPLF abandoning bodies of its soldiers everywhere, causing psychological trauma on people in Somali region of Ethiopia

ESAT News (June 25, 2016)
Residents in the Somali region of Ethiopia said the TPLF regime is dumping the bodies of its soldiers who were killed in fighting in Somalia everywhere, inflicting a heavy psychological trauma on people in the region.
Some residents confided to ESAT that the bodies of soldiers killed in Baidoa, Mogadishu and other areas in Somalia were being loaded on trucks and dumped in many places on the border with Somalia. They said it was shocking to see wild animals making feast out of human bodies, which they said was a recurring scene in the border areas.

Friday, June 24, 2016

በሊቦ ከምከም ወረዳ የተፈጸመውን ጥቃት በአገር ውስጥ የተደራጁ ሃይሎች የፈጸሙት መሆኑን ምንጮች ገለጹ

ሰኔ  (አሥራ  ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ጎንደር ሊቦ ከምከም ወረዳ ትናንት የመንግስት ተቃዋሚ ሃይሎች ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት 6 ፖሊሶች ሲገደሉ አንድ ብሬን መትረጌስ፣ 4 ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎችና በርካታ ቦንቦች ተማርከዋል። ኢሳት ከአምስተርዳም ባስተላለፈው ዜና ጥቃቱን አቶ አረጋ የሚባሉ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የመንግስት ተቃዋሚ እንደፈጸሙት  ቢዘግብም፣ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ባገኘው አስተማማኝ መረጃ፣ ጥቃቱ የተፈጸመው የተጠቀሰውን ግለሰብ ባካተተው በአካባቢው በተደራጁ የመንግስት ተቃዋሚ ሃይሎች ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ሲገደሉ በክብር አለመቀበራቸው በሶማሊ ክልል ከፍተኛ የስነልቦና ቀውስ እየፈጠረ ነው ተባለ

ሰኔ  (አሥራ  ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት በባይዶዋ፣ ሞቃዲሹና ሌሎችም የሶማሊያ ግዛቶች በአልሸባብ ተዋጊዎች የሚገደሉ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ፣ በመኪኖች እየተጫኑ በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር አካባቢ መጣላቸው በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የስነ ልቦና ቀውስ ፈጥሯል።

የበርካታ ወታደሮች አስከሬን እንደ አልባሌ ሜዳ ላይ እየተጣለ በመሆኑ የአውሬ ራት እየሆኑ ነው የሚሉት ነዋሪዎች፣ የወዳደቀ እና በአውሬ የተበላ አስከሬን መመልከት የተመደ ነገር ሆኗል ይላሉ። ማንኛውም ሰው ቢሆን ከሞተ በሁዋላ በክብር ሊቀበር ይገባል፣ በእኛ አካባቢ የምናየው ነገር ግን እጅግ አሳዛኝ ነው የሚሉት ነዋሪዎች፣ ድርጊቱ በአካባቢው ነዋሪዎች ስነልቦና ላይ ትልቅ ተጽኖ እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

መምህራን በግዳጅ የመምህራንን ቀን ሊያከብሩ ነው

ሰኔ  (አሥራ  ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰኔ 22 ቀን 2008 ዓም በሚከበረው በአል ላይ መምህራን በግዳጅ በቦታው ተገኝተው እንዲያከብሩ ታዘዋል።

የመምራን ነጻነት ባልተከበረበት ሁኔታ፣ የመምህራንን ቀን ማክበሩ ትርጉም የለውም በሚል ተቃውሞ ያነሱ መምህራን “ ትታሰራላችሁ” የሚል ማስፈራሪያ ደርሷቸዋል። መንግስት ከመምህራን ሊደርስበት የሚችለውን ተቃውሞ በመፍራት ሰሞኑን የደሞዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ አስታውቋል። ጭማሪው መታወጁን ተከትሎ በቤት ኪራይና በእቃዎች ላይ ዋጋ ይጨምራል በሚል መምህራን ፍርሃታቸውን እየገለጹ ነው።
ለደህነታቸው በሚል ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ መምህራን እንደገለጹት፣ ገዢው ፓርቲ በማስፈራራት እና የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን ለመስጠት ቃል በመግባት መምህራንን ከጎኑ ለማሰልፍ ጥረት ቢያደርግም፣ በርካታ መምህራን ግን አሁንም “ ከሁሉም በላይ ነጻነታችንን እንፈልጋለን” በሚል የድርጅቱ አባል ለመሆን ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

Thursday, June 23, 2016

አንዳርጋቸው ጽጌ የታገተበትን ሁለተኛ አመት ስናስታውስ ለነጻነት ትግሉ ያለንን ቁርጠኝነት በማደስ ነው!! –

June 23, 2016

የአርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ

የወያኔ አገዛዝ በአቡደራቡህ መንሱር ሃዲ ይመራ ከነበረው የየመን መንግሥት ጸጥታ ሃይል ጋር በመመሳጠር አንጋፋውን መሪያችንንና የትግል ጓዳችንን አንዳርጋቸው ጽጌን ከሰነዓ አውሮፕላን ማረፊያ አግቶ በቁጥጥሩ ስር ካስገባ እነሆ ዛሬ ሁለት አመት ሞላው።

Wednesday, June 22, 2016

የመከላከያ መሃንዲሶችና መምህሮቻቸው ወደ ጦር ግንባር እንዲዘምቱ መደረጉን ተቃወሙ

ሰኔ  (አሥራ  አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሜ/ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ቴክኒክ ኮሌጅና በደብረዘይት ወታደራዊ ምህንድስ ክፍል ውስጥ  ሲሰሩ የነበሩ በርካታ ወታደራዊ መሃንዲሶች፣ የጥገና ሰራተኞች እና መምህራን የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ከመነሳቱ ከ2 ሳምንት በፊት ወደ ኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መላካቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ሰራተኞቹ “ከዚህ ቀደም ተደርጎ የማያውቅ ነው” በማለት ወደ ግንባር መላካቸውን ቢቃወሙም፣ የሚሰማቸው አለማግኘታቸውን ገልጸዋል። ከሁለቱ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ብቻ ከ30 በላይ የምህንድስና አስተማሪዎች ወደ ግንባር የተላኩ ሲሆን፣ ሁሉም በብሄራችን የተነሳ ተመርጠን ወደ ግንባር እንድንላክ ተደርጓል በማለት ቅሬታ ያሰማሉ። ኢሳት የተላኩት መምህራን ስም ዝርዝር ያለው ሲሆን ለደህንነታቸው በመስጋት ይፋ አያደርግም።

የፌደራል ፖሊስ አባላት ኮንሶ ከተማን እንደገና መቆጣጠራቸው ተሰማ

ሰኔ  (አሥራ  አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሰኔ 13 ቀን 2008 ዓም ጀምሮ በኮንሶ የሚታየው ውጥረት መጨመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የፌደራል ፖሊስ አባላት ከተማዋን ከተቆጣጠሩ በሁዋላ 4 ነዋሪዎችን አፍነው መውሰዳቸው ታውቋል። ይህንን ተከትሎ ህዝቡ ተቃውሞ ያስነሳ ሲሆን፣ ወታደሮቹ በወሰዱት እርምጃ በርካታ ነዋሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የተቀናሽ ሰራዊት አባላት በረንዳ ላይ እያደሩ መሆኑን ተናገሩ

ሰኔ  (አሥራ  አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሌሎች አገር ዜጎች ለተቀናሽ የሰራዊት አባላት ተገቢውን እንክብካቤ ሲያደርጉ፣ በኢትዮጵያ ግን ማረፊያ ጎጆ እንኳን በማጣታቸው በረንዳ ላይ እየተጣሉ መሆኑን የተቀናሽ ሰራዊት አባላት ተናግረዋል።

በባህርዳር በርካታ የተቀናሽ ሰራዊት አባላት ያሉ ሲሆን ብዙዎቹ በረንዳ ላይ ያድራሉ። “ሰራዊቱ አካሉን አጥቶና ተጎድቶ እያለ” መኖሪያ ቤት እንኳን ማግኘት አልቻለም የሚሉት የተቀናሽ ሰራዊት አባላት፣ አቤቱታቸውን የሚሰማላቸው ሰው በማጣታቸው እንደሚበሳጩ ይገልጻሉ።
መስተዳድሩ የመንግስት ቤቶችን በአግባቡ ለህዝብ በሚጠቅም መልኩ አለማስተዳደሩ በርካታ ዜጎች በርንዳ ላይ እንዲያወድቁ አድርጎአቸዋል።

በአውስትራሊያ የአቶ አባይ ወልዱን ጠባቂ የመታው ግለሰብ ክስ ተመሰረተበት

ሰኔ  (አሥራ  አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በታስማኒያ ሆባርት ከተማ የገቢ ማሰባሰብ ስራ ለመስራት በሄዱት በትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አባይ ወልዱ ጠባቂ ላይ ድብደባ አድርሰሃል በሚል አንድ ወጣት መከሰሱን ሄራልድ ሰን የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ መዘገቡን ተከትሎ ኢሳት ባደረገው ማጣራት ፣ ወጣቱ ላይ ክስ የመሰረተው የሶማሊያ ዜግነት ያለው አብዱ ባራክ አብዲ   የተባለ የአቶ አባይ ወልዱ ጠባቂ ሲሆን፣ ፍርድ ቤት በሚቀጥለው ወር መግቢያ ላይ ክሱን እንደሚመለከተው ታውቋል።

በደቡብ ሱዳን የተሰማራው የሰላም አስከባሪ ጦር ትችት ቀረበበት

ሰኔ  (አሥራ  አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሥር የደቡብ ሱዳን  የሰላም አስከባሪ ጦር ሰላማዊ ዜጎችን ከለላ መስጠት አልቻለም ተባለ።

በእርስበርስ ጦርነት የምትታመሰው አዲሲቷ አገር ደቡብ ሱዳን በማላካል ከተማ ውስጥ እልቂት ሲፈፀም በስፍራው የነበሩት የሰላም አስከባሪ ጦር አባላት የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ እንዳልቻሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምርመራ ቡድን ጥናት ሪፓርት አስታውቋል።

Tuesday, June 21, 2016

በጨለንቆ አንዲት ወጣት መገደሏን ተከትሎ ተቃውሞ በመቀስቀሱ መንገድ ተዘጋ

ኢሳት (ሰኔ 14 ፥ 2008)

በምስራቅ ሃረርጌ ጨለንቆ ውስጥ የአንዲት ወጣት መገደልን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ በዛሬው ዕለት መንገድ መዘጋቱን የአይን ምስክሮች ከስፍራው ገለጹ። የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሳብሪና አብደላ የተባለች ወጣት ከመስጊድ ወጥታ ስትሄድ በፖሊሶች መገደሏን በመቃወም በተነሳው ተቃውሞ ፖሊሶች ቀብሩን ለመከፋፈል የሞከሩ ቢሆንም፣ በመጨረሻ የቀብሩ ስርዓት መፈጸሙን መረዳት ተችሏል።

አየር ሃይል የበረራ ስልጠናውን ሙሉ በሙሉ ወደ ድሬዳዋ አዛወረ

ሰኔ  (አሥራ  ራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት አየር ሃይል በዚህ ሳምንት አዳዲስ በገዛቸው የጦር አውሮፕላኖቹ ድሬዳዋ ላይ ወታደራዊ ልምምድ የሚጀምር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፓይለት ስልጠና ( pilot Training base) መቀመጫውን እስከሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ከድሬዳዋ ወደ መቀሌ እንዲያዛውር ትእዛዝ ተላልፎለታል።  አየር ሃይል “ለአገራዊ ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት አለባችሁ” በሚል ትእዛዝ አየር መንገዱ የድሬዳዋ የበረራ ማሰልጠኛውን እንዲለቅ ያስገደደ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ  አየር መንገድም በድሬዳዋ የቀሩትን 5 የመለማመጃ አውሮፕላኖች በሳምንቱ መጨረሻ ወደ መቀሌ ያዛውራል።

አየር ሃይል፣  የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያደርገው የበረራ ስልጠና የአየር ትራፊክ አፈና ( air traffic jam) ይፈጥራል የሚል ስጋት አድሮበታል። አየር ሀይል በመቀሌ አካባቢ የሚያደርገውን ስልጠና ለምን ወደ ድሬዳዋ ማዛወር እንደፈለገ የታወቀ ነገር የለም።

በጨለንቆ በተነሳው ተቃውሞ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ ዋለ

ሰኔ  (አሥራ  ራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምስራቅ ሃረርጌ ከትናንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ባለው ተቃውሞ ምክንያት ከአዲስ አበባ ወደ ሃረር ከሃረር ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በድንጋይ በመዘጋቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ አርፍዷል። አድማ በታኝ ፖሊሶች ከሃረር ወደ ጨለቆ በማምራት እና በህዝቡ ላይ በመተኮስ መንገዱን ቢያስከፍቱትም፣ ተቃውሞው ግን ይህን ዜና እስካጠናከርንበት በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር እስከ 9 ሰአት ቀጥሎአል።

አንድ የፖሊስ አባልስ በተኮሰው ጥይት ሳብሪና አብደላ የምትባል መንገድ ላይ ሻሂ በመሸጥ የምትተዳደር እና በቅርቡ የ10ኛ ክፍል ማትሪክ ፈተና የወሰደች ወጣት ሴት ልጅ መገደሏ ተቃውሞውን አባብሶታል። የወጣቷን መገደል ተከትሎ የአካባቢው ህዝብ ተቃውሞውን በመንግስት ላይ ማሰማት የጀመረ ሲሆን፣ ተቃውሞው እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ከሃረር የተነሳው ፖሊስ አካባቢውን ተቆጣጠሮታል።

በአርባምንጭ የ76 አመቱ አዛውንት ተፈረደባቸው

ሰኔ  (አሥራ  ራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሽብር ወንጀል ተከሶ 7 አመት የተፈረደበት የሰማያዊ ፓርቲ የአርባምንጭ ተጠሪ የአቶ በፈቃዱ አበበ አባት የሆኑት አቶ አበበ አስፋው ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው 1 አመት ከስድስት ወር የተፈረደባቸው ሲሆን፣ ውሳኔው እንደተላለፈ አዛውንቱ ወደ አርባምንጭ እስር ቤት ተልከዋል።

በፈቃዱ የአርባ ምንጭ ወጣቶችን እየመለመልክ ለአርበኖች ግንቦት7 ትልካለህ በሚል መታሰሩን ኢሳት በወቅቱ ዘግቦ ነበር። በፈቃዱ በታሰረ ማግስት የፌደራል ፖሊሶች ወደ አቶ አስፋው ቤት በመሄድ እርሳቸውንና ሴት ልጃቸውን ወ/ት አየለች አበበን አስረው በመውሰድ አቶ አስፋው በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ሲደረግ፣ ወ/ት አየለች ግን ወደ ማእከላዊ እስር ቤት ተወስዳ ፣ በአሁኑ ሰአት ቀሊንጦ እስር ቤት ትገኛለች።

Monday, June 20, 2016

ኤርትራ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ለተሰነዘረባት ጥቃት የአሜሪካ እጅ እንዳለበት ገለጸች

ሰኔ ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር እንደገለጸው ኢትዮጵያ በቅርቡ በኤርትራ ላይ ለሰነዘረችው ጥቃትም ሆነ በአካባቢው  ላሰማራችው ሳራዊት የአሜሪካ እጅ አለበት። የአሜሪካ መንግስት ሁለቱም ሃይሎች ጦርነት ውስጥ እንዳይገቡ ያስጠነቀቀ ቢሆንም፣ የኤርትራ መንግስት የአሜሪካ መግለጫ ጎጂውንና ተጎጂውን እኩል የሚፈርጅ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብሎአል።

የኤርትራ መንግስት በሰሞኑ ግጭት የአሜሪካ እጅ አለበት ቢልም ዝርዝር መግለጫ ወደ ፊት እንደሚሰጥ ከመግለጽ ውጭ ተጨማሪ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም። በኤርትራ እና በአውሮፓ መካከል ያለው ግንኙነት መሻሻል ቢታይበትም፣ በኤርትራ እና በአሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ግን እስካሁን መሻሻል አላሳዬም። የኤርትራ መንግስት፣ የአሜሪካ መንግስት ለኢህአዴግ መንግስት ጭፍን ድጋፍ ይሰጣል በሚል በተደጋጋሚ ክስ ሲያቀርብ ይሰማል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ባለፈው አመት አሜሪካ መንግስት ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚጠጋ ወታደራዊ ድጋፍ ለኢህአዴግ መንግስት አድርጓል። የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ ከአልሸባብ ጋር የሚያደርገውን ጦርነት አሜሪካ በገንዘብ እና በማቴራል እንደምትደግፍ ዘገባዎች ያሳያሉ።
በኢትዮ ኤርትራ ድንበር አሁንም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች የሚታዩ ሲሆን፣ ሁለቱም አገራት ወደ ሙሉ ጦርነት ሊገኑ ይችላሉ በማለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎችም ዲፕሎማቶች እያስጠነቀቁ ነው። ሰሞኑን በተደረገው ግጭት ኤርትራ 200 የኢትዮጵያ ወታደሮችን መግዷልን ማስታወቋ ይታወሳል። ኢትዮጵያ በኤርትራ በኩል ስላደረሰቸው ጉዳት እስካሁን የገለጸቸው ነገር የለም።

ሱዳን መከላከያዋን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ማስጠጋቷ ተሰማ

ሰኔ ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ ታጣቂ አርሶደአሮች የሱዳንን አርሶደአሮች በማባረር መሬታቸውን እየቀሙ ነው በሚል የአገሪቱ መከላከያ ሃይል የተወሰነ ጦሩን ወደ ድንበር አካባቢ አንቀሳቅሷል። ምንም እንኳ ሱዳን  ወታደሮቿን  ብታንቀሳቅስም፣ እስካሁን ደረስ ወታደሮቿ በኢትዮጵያ አርሶአደሮች ላይ እርምጃ ለመውሰድ አልደፈሩም።

የሱዳን መንግስት ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ታጣቂ አርሶአደሮች ከ800 ሺ ሄክታር በላይ መሬት ወስደውብናል በማለት ውንጀላ ያቀርባሉ። ፣ የሁለቱ አገራት ድንበር በፍጥነት እንዲካለልላቸውም እየጠየቁ ነው። የኢትዮጵያ አርሶአደሮች በበኩላቸው መሬቱን ለዘመናት ሲጠሙበት መቆየታቸውንና ሱዳኖች በማን አለብኝነት ወስደው እየተጠቀሙበት መሆኑን ይገልጻሉ።  በኢትዮጵያ በኩል መብታቸውን የሚያስከብርልቻው መንግስት እንዳላገኙ በመግለጽም ወቀሳ ያቀርባሉ።  አርሶ አደሮቹ በራሳቸው ተደራጅተው የሱዳን ወታደሮችን ጥቃት ለመመከት እንደሚችሉ በመናገር ላይ ሲሆኑ፣ የሱዳን ወታደሮች ድፍረው ተኩስ የሚከፍቱ ከሆነ ጉዳቱ ይከፋ ይሆናል በማለት ያስጠነቅቃሉ።
በሁለቱ አገር አርሶአደሮች መካከል በየጊዜው ደም አፋሳሽ የሆነ ግጭት ሲካሄድ የቆዬ  ሲሆን፣ አሁን ግን ውጥረቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሯል። ሱዳኖች በቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ በየጊዜው ኢትዮጵያውያን አርሶአደሮችን እያፈኑ ይወስዳሉ። ባለፉት 2 ወራት ብቻ ከ33 ያላነሱ አርሶአደሮች በሱዳኖች ታፍነው ተወስደዋል። ኢንሳ የተባለው የመንግስት የመረጃ እና ደህንነት ኤጀንሲ የሁለቱን አገራትን ድንበር ለማካለል የአየር ላይ ፎቶ ግራፍ ሲያነሳ መክረሙን ኢሳት መዘገቡ ይታወቃል። ስራው እንደተጠናቀቀም የድንበር ማካለሉ ስራ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

በአማራ ክልል የተሰራጨው የቡና ዘር ምንነት አለመታዎቅ ስጋት አስከትሏል፡፡

ሰኔ ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ደጋማ ክፍል በእርዳታ ስም የተሰራጨው የቡና ዘር ምንነት ሳይመረመር በመሰራጨቱ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ጉዳት ሊያስከትል

እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ማንነቱ ያልታወቀ የውጭ ዜጋ መስመሩን ባልተከተለ ሁኔታ ባለሙዎችን ሳያሳትፍ እና በቂ ገለጻ ሳያደርግ የዞኑን አመራሮች በመያዝ ወደ አርሶ አደሮች በመድረስ ዘሩን ማሰራጨቱ አግባብ እንዳልሆነ የአትክልትና
ፍራፍሬ ባለሙያው ተናግረው አንድ ዘር ወደ አርሶአደሩ ዘንድ ከመሰራጨቱ በፊት በምርምር ሊሞከር እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡
ብዙውን ጊዜ ዘር ሲቀርብ በመጀመሪያ ደረጃ በዘርፉ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ተገቢው ገለጻ ተደርጎና በሙከራ ተረጋግጦ ተስማሚነቱ መረጋገጡ የተለመደ ቢሆንም ሰሞኑን የቀረበው የቡና ዘር ግን ዘሩን ያመጣው
ግለሰብ ከበላይ አመራሩ ጋር ብቻ በመነጋገር እንዲከፋፈል ማድረጉ ተገቢ ያልሆነ በወንጀል የሚያስጠይቅ ድርጊት መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ ወደ አርሶ አደሩ የተከፋፈለው ዘር የአምራቹ ድርጅት ስም፣
የተዘጋጀበት ቀንና ሃገር እንዲሁም የዘሩን መለያ ስም አካቶ የሚይዘው መለያ [label] ያልተለጠፈበት መሆኑን ከስርጭቱ በኋላ በተደረገው ፍተሻ ለማረጋገጥ መቻሉን ባለሙያው ገልጸው፤የመለያው አለመኖር
ዝርያው ለየትኛው አካባቢ የተሰራ መሆኑንና የዝርያውን ባህሪ ለማወቅ አስቸጋሪ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
ወደ አርሶአደሩ መሰራጨቱ ጥቆማ ከደረሳቸው በኋላ ጉዳዩን ተከታትለው ለመመርመር ያደረጉትን እንቅስቃሴ በአመራሮች ተጽእኖ እንዲያቆሙ ግፊት እንደተደረገባቸው ተናግረው   ፣ ይህ ያልተመረመረ ዘር
መሰራጨቱ በአካባቢው ያለውን የቡና ዘር ሊበክል እና የመሬት ኪሳራ ሊያደርስ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ባለሙያው ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
አመራሮች ዘሩን ያቀረበው ግለሰብ ይህን በማድረጉ የሚያገኘው ጥቅም እንዳይቀርበት ብቻ በማሰብ በአቅራቢው ላይ የሚነሳ ጥያቄ እንዳይኖር ሲከላከሉ መታየታቸውን የሚገልጹት የአትክልትና ፍራፍሬ
ባለሙያ አቅራቢው ስለአቀረበው ዘር የሰጠው መግለጫ አለመኖሩ ሌላው ክፍተት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻ ያለ እውቅና የተሰራጨው ዘር እንደ ሃገር በቡና ላይ ያለውን የቴክኖሎጂ ስርጸት እና በቡናችን ላይ ያለው ተቀባይነት ዙሪያ የሚያመጣውን ክፍተት ቢያስረዱም ሰሚ በማጣት ክፍተቱ እንዳለ
መቀጠሉን ባለሙያው ለሪፖርተራችን ገልጸዋል፡፡

Friday, June 17, 2016

19 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መንገድ ላይ ማለቃቸው ተዘገበ

ሰኔ ፲(አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሰሌዳ ቁጥሩ AFB 496 በሆነ የዛንቢያ የአሳና ባቄላ መጫኛ ኮንቴነር ውስጥ ተደብቀው ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ላይ የነበሩ 19 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች እረቡ  ሚውንዳ ድንበር አቅራቢያ ሞተው ተገኙ።

በኮንቴነሩ ውስጥ በተጨናነቀ ሁኔታ የተጫኑ 73 ስደተኞች ሲሆኑ ከሟቾቹ በተጨማሪ በሕይወት የተረፉት ላይም ጉዳት ደርሶባቸዋል። ዘግናኝ እልቂት መድረሱን ተከትሎ የዛንቢያ የስደተኞች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት የሕገወጥ ስደተኞችን ዝው ውር ለመግታት አፋጣኝ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ለስደተኞቹ ሞት መንስዔ የሆነው በተጫኑበት ወቅት የአየር እጥረት በመከሰቱ ምክንያት ሕይወታቸውን እንዳጡና የሟቾቹ 19 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች አስከሬን ወደ ኒዶላ ማእከላዊ ሆስፒታል መወሰዱን ፓሊስ ገልጿል። የ29 ዓመቱ የመኪናው አሽከርካሪ የነበረው ዛንቢያዊያን ኤዲዋርድ ሲምዋባ የ37 ዓመቱ ረዳት አሸከርካሪውን  ኬስታ ካኒያንታን  ጨምሮ 54 ከአደጋው የተረፉ ኢትዮጵያዊያን በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ኒዶላ ተወስደዋል።

እነ አቶ አባይ ወልዱ ከአውስትራሊያዋ ታስማኒያ ግዛት ለቀው እንዲወጡ ተደረገ

ሰኔ ፲(አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለገንዘብ ማሰባሰብና ለቅስቀሳ ስራ በአውስትራሊያ የተገኙት የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አባይ ወልዱና የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት ሙክታር ከድር እና ሶማሊ ክልል

ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሃመድ በአካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያን ያጋጣመቻውን ተቃውሞ ተከትሎ የአገሪቱ ፖሊስ ዋና ከተማዋን ሆባርትን ለቀው እንዲወጡ በማዘዝ፣  በመጡበት አውሮፕላን ተመልሰዋል።
ሶስቱ ባለስልጣኖች ቀደም ብሎ በካምቤራና በሜልበርን የደረሰባቸውን ተቃውሞ ተከትሎ ደጋፊዎቻቸውን ኢትዮጵያውያን በብዛት አይገኙበትም ተብሎ በሚታሰበው የታስማኒያ ግዛት ለመሰብሰብ አስቀድመው ቢገኝም፣ በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሰባስበው ተቃውሞ በማሰማታቸው ፖሊስ ለጸጥታ አስቸገሪ ነው ከተማዋውን ለቀው እንዲወጡ አድርጓል።

በባህርዳር በቀበሌ ቤቶች ዙሪያ አመራሮች ተወዛገቡ

ሰኔ ፲(አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዋጅ ቁጥር 47/67 ትርፍ ቤትን ለመንግስት ባደረገው አዋጅ የተወረሱ የቀበሌ ቤቶችን አመራሩ ለራሱ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት በመኖሪያነትና በንግድ ቤትነት የሚገለገልበት አካሄድ አግባብ አለመሆኑን ሰሞኑን የባህርዳር ከተማ አስተዳደር አገልግሎት አቅርቦትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፋሲል ሙሉ ተናግረዋል።

“ድሃ ይቅደም!” የሚሉት የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራር ፣ ህብረተሰቡ በዚህ አሰራር መማረሩን ገልጸው፤ የከተማ አስተዳደሩ በፍትህ ተከራክሮ ነጻ ያደረጋቸውን ቤቶች አመራሩ “መመሪያነው!” በሚል ቀድሞ ለመያዝ መሞከሩ መሰረታዊ ስህተት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Thursday, June 16, 2016

ኤርትራ ከ200 በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ገድላ ከ300 በላይ ማቁሰሏን አስታወቀች

ሰኔ ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የህወሃት መንግስት ሰኔ 5 ቀን 2008ዓም  በጾረና ግንባር ጥቃት መጀመሩንና  ሰኞ ሰኔ 6 ጠዋት ላይ ለማጥቃት የተንቀሳቀሰው ጦር ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሁዋላ ማፈግፈጉን ገልጿል።

በዚህ አላማው ግልጽ ባልሆነ የግድየለሽ ጥቃት 200 የኢትዮጵያ ወታደሮች ሲገደሉ 300 የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል ብሎአል። የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊልቅ ይቻላል ሲል በመግለጫው ጠቅሷል።  ይህን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማካሄድ ለምን ተፈለገ? ምንስ ለማግኘት ነው ሲል የሚጠይቀው መግለጫው፣ ይህን ሃላፊነት የጎደለው ጥቃት እንዲጀመር ያነሳሱ ሃይሎች ከጥቃቱ በፊትና በሁዋላ ለህወሃት የፖለቲካ፣ የሚዲያና የዲፕሎማሲ  ሽፋን ለመስጠት ሞክረዋል ብሎአል። ጥቃቱን በጀመረውና ጥቃቱ በተፈጸመበት ላይ እኩል ወቀሳ መቅረቡንም መግለጫው አውግዟል። የኤርትራ መንግስት የጥቃቱን ስፋት በተመለከተ ተከታታይ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

የተለያዩ የጸጥታ ሃይሎችን ሙሉ መረጃዎች የሚያሳዩ ሰነዶች ኢሳት ውስጥ ገቡ

ሰኔ ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የጸጥታና የደህነት ሃይሎች ሙሉ ስም ዝርዝር፣ የመታወቂ ቁጥር፣ የመኖሪያና የስራ አድራሻ እንዲሁም ሌሎች መረጃዎች ኢሳት እጅ ገብተዋል። የጸጥታ ሃይሎች ያደረጉዋቸውን ስብሰባዎች የሚያሳዩ ቃለ ጉባኤዎች እንዲሁም በሚስጢር እንዲያዙ የተደረጉ የምርምራ ዘገባዎችም ኢሳት እጅ ገብተዋል። ኢሳት የደህንነት ምንጮቹን አደጋ ውስጥ በማይጥል መልኩ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ዋና ዋና መረጃዎችን እየመረጠ ለወደፊቱ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ለመግለጽ ይወዳል

የመንግስት ወታደሮች 400 የኦሮሞ ተወላጆችን መግደላቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች አስታወቀ

ሰኔ ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ተካሂዶ በነበረው ሰላማዊ ሕዝባዊ ተቃውሞ ወቅት በገዥው መንግስት ታጣቂዎች ከ400 በላይ የሚሆኑ ሰላሚዊ ዜጎች በግፍ መገደላቸውንና ከአስር ሺ በላይ መታሰራቸውን ሂውማን ራይትስ ወች ባወጣው ሪፓርት ገልጿል።

ሂውማን ራይትስ ወች ለተወሰደው ኢሰብዓዊ ጨፍጨፋ የኢትዮጵያ መንግስት በአፋጣኝ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት ብሏል። ገለልተኛ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ በዜጎች ላይ ግድያ፣ እስራትና ከሕግ አግባብ ውጪ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ግለሰቦች ተይዘው ለፍርድ መቅረብ ይገባቸዋል ሲል ጥሪውን አቅርቧል። በ61 ገጽ የምርመራ ሪፓርት ጥናት መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት ከአቅም በላይ የታጠቁ ገዳይ ኃይሎችን በማሰማራት በሰላማዊ ዜጎች ላይ አስፈላጊ ያልሆነ የጅምላ ግድያና እስራት አድርሷል። በተጨማሪም በወህኒ ቤት ውስጥ ያሉ እስረኞችን ሰብዓዊ መብታቸውን በመጣስ አላስፈላጊ የሆነ ግፍ መፈጸሙንና በሕዝባዊው ማእበል እንቅስቃሴ ወቅት መረጃዎች እንዳይሰራጩ እገዳ መጣሉን ገልጿል። ሂውማን ራይትስ ወች በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ ቁጥራቸው 125 ዜጎችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ በኢትዮጵያ የመሰብሰብ፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሕጋዊ መብቶች ሕዝባዊ ተቃውሞው ከጀመረበት ከጥቅምት ወር ጀምሮ በፀጥታ ኃይሎች ተከልክለዋል።

በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ ለመቀልበስ መንግስት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መውሰዱን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅት አስታወቀ

ኢሳት ዜና (ሰኔ 9 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰውና ከመንፈቅ በላይ በዘለቀው ተቃውሞ የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 400 ያህል መሆኑን እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ መቁሰላቸውን ፣በአስር ሺዎች መታሰራቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch) ሃሙስ ይፋ አደረገ። የ314ቱን ሰለባዎች ስም ዝርዝር በቀን እና በአድራሻ በ 86 ገጽ ሪፖርቱ አስፍሯል።
የHuman Rights Watch ሪፖርት ከ125 በላይ የሚሆኑ ምስክሮች፣ የጥቃቱ ሰለባዎች፣ እና የመንግስት ባለስልጣናትን ቃለመጠይቅ ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል። ሰነዱም በኦሮሚያ በተካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ ማለትም ከህዳር እስከ ግንቦት 2008 ጊዜ ድረስ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል።

Tuesday, June 14, 2016

ሜቴክ በህገወጥ መንገድ የሚገነባው ፋብሪካ በዩኒስኮ የተመዘገበውን የያዩ የቡና ጫካ ሊያጠፋው መቃረቡ ታወቀ

ሰኔ ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የያዩ የቡና ጫካ በእንግሊዝኛ ስያሜው Yayu Coffee Forest Biosphere Reserve በዩኒስኮ ከተመዘገቡት ሁለት የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጫካዎች አንዱ ቢሆንም፣ የመከላከያ ብረታብረት ኮርፖሬሽን ምህንድስና ( ሜቴክ) በሚገነባው የያዩ ድንጋይ ከሰል ልማትና ማዳበሪያ ፋብሪካ ኮፕሌክስ የተነሳ ጨካው የመጥፋት አደጋ እንደተደቀነበት ከማእድን ሚኒስቴር ለኢሳት የተላኩት ሰነዶች አመልክተዋል። ሜቴክ ግንባታውን የጀመረው ከማእድን ሚኒስቴር ፣ ከአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲሁም ከኦሮምያ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ፈቃድ ውጭ ሲሆን፣ በሌሎች አገሮች የማይገኙ የ አረቢካ የቡና ዘርና እና ሌሎችም እጽዋቶች ህልውና አደጋ ላይ በመውደቁ ጉዳዩ ያሳሰባቸው በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ህገ ወጥ ድርጊቱ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ ከቀያቸው ተፈናቅለው ኮረብታ ላይ የሰፈሩት ዜጎች እንደገና ተነሱ

ሰኔ ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ወኪላችን እንደገለጸው ከአዲስ አበባ የዘፈቀደ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የእርሻ ቦታቸውን የተነጡቁት  አርሶአደሮች ፣ በለቡ አደባባይ አብርሃሙ ስላሴ ቤተክርስቲያን ያለበት ኮረብታማ ቦታ ላይ መኖሪያ ቤታቸውን ሰርተው ቢኖሩም፣ አሁንም እንደገና ቤታቸው እንዲፈርስ በመደረጉ ያለምንም ካሳ መውደቂያ አጥተው ይገኛሉ።

ነዋሪዎቹ ቤቶቻቸው ሲፈርሱባቸው እቃዎቻቸውን እንኳን እንዲያወጡ ጊዜ አልተሰጣቸውም።

የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ወታደሮችን ለመቅጠር ማስታወቂያ ቢያወጣም የሚመዘገብ ወጣት ሊያገኝ አለመቻሉ ተገለጸ።

ሰኔ ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በወታደርነት መቀጠር የሚፈልጉ ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ  ወጣቶች   ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 10 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ድረስ እንዲመዘገቡ የሚጠይቁ ማስታወቂያዎች በየቦታው ቢለጠፉም ፣ የሚመዘገቡ ወጣቶች ቁጥር አነስተኛ መሆን ገዢው ፓርቲን አሳስቦታል።

Monday, June 13, 2016

ወያኔ ከገባበት ውጥረት ለመውጣት በከፈተው ጦርነት ትኩረታችን አይቀለበስም !!!

መግለጫ June 13, 2016
በጥጋብና እብሪት የተወጠረው የህወሃት አገዛዝ በትናንትናው ዕለት ዕሁድ ሰኔ 5 ቀን 2008 በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በኩል ከኤርትራ ጋር በሚያዋስኑ የድንበር ቦታዎች ላይ ጦርነት ጀምራል፤ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ይህን ዜና አረጋግጠው ዘግበዋል። ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በወያኔ በኩል ስለጦርነቱ ምንም የተሰጠ መግለጫ ባይኖርም የኤርትራ መንግሥት በጾረና ግንባር በኩል ጥቃት እንደተፈጸመበት ትናንት ማምሻውን ይፋ ባደረገ መግለጫ አረጋግጦአል።
የህወሃት ዘረኝነት በፈጠረው ኢፍትሃዊነትና አፈና የተማረረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሁሉም የአገራችን ክፍሎች በአገዛዙ ላይ ተቃውሞውን እያጠናከረ ባለበት በዚህን ሰዓት በሙስና የተጨማለቁ የህወሃት የጦር ጀነራሎችና በሲቪል ማዕረግ አስተዳደሩን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠሩ ሃይሎች ለምን ይህንን ጦርነት መጫር እንደፈለጉ ግልጽ ነው። በኦሮሚያ የተነሳውን የመብት ጥያቄ ለማፈን ከ400 በላይ ሕዝብ መጨፍጨፉና በሺዎች የሚቆጠሩ እስር ቤት መታጎራቸው የህወሃትን ዕድሜ ለማራዘም እንደ አንድ መሣሪያ ሆኖ ላለፉት 25 አመታት ሲያገለግል በኖረው ኦህዲድ ውስጥ እንኳን ከከፍተኛ አመራር እስከ ተራ ካድሬ ያሉትን አስኮርፎአል። የወልቃይት ህዝብ ያነሳው የማንነት ጥያቄ ሌላኛው የህወሃት አጋር በሆነው ብአዴን ውስጥ የማያባራ ክፍፍል ፈጥሮአል።

ኤርትራ በጾረና ግንባር ጥቃት እንደተሰነዘረባት አስታወቀች

ሰኔ ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ በጾረና ግንባር የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ትናንት እሁድ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ስለ ጥቃቱ ዝርዝር መግለጫ እንደሚያወጣ ገልጿል። በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም። በሁለቱም ድንበሮች ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየታዬ ሲሆን፣ ጥቃቱ ወደ ሙሉ ጦርነት ይሸጋገር አይሸጋገር ገና  የታወቀ ነገር የለም። አርበኞች ግንቦት7 ባወጣው መግለጫ ጦርነቱ ህወሃት ከገባበት የውስጥ አጣብቂኝ ለመውጣት የጀመረው ነው ብሎአል።

በአልሸባብ የተገደሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ቁጥር አሻቀበ

ሰኔ ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመከላከያ ምንጮች እንደገለጹት አልሸባብ የተባለው ታጣቂ ቡድን በማእከላዊ ሱማሊያ በኢትዮጵያ የጦር ካምፕ ላይ ባደረሰው ድንገተኛ ጥቃት 89 ወታደሮች ሲሞቱ 103 የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል። በከባድ ሁኔታ የቆሰሉ ወታደሮች በተከታታይ ቀናት ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ በጽኑ ከቆሰሉት መካከል ደግሞ 60 ወታደሮች ቅዳሜ ወደ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል ተልከዋል። ቁስለኞቹ በህክምና ላይ መሆናቸውን ኢሳት ከሆስፒታሉ ምንጮች ለማረጋገጥ ችሎአል።

የበየዳ ወረዳ ነዋሪዎች “መንግስት የለንም” እያሉ ተቃውሞ ሲያደርጉ ዋሉ

ሰኔ ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ቁጥራቸው ከ2500 በላይ የሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲሁም ትምህርታቸውን አቋርጠው ሰልፉን የተቀላቀሉ ተማሪዎች በርካታ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

“ መንግስት የለንም፣ አገራችንን የሚመራ ሰው ይሰጠን፣ የህወሃት ድርጅት የሆነው ሳትኮን ኮንስትራክሽን ድርጅት በወረዳችን እየሰራ ያለው መንገድ ጥራቱን ያልጠበቀ በመሆኑ ገንዘባችን  እየተበላ ነው፣ ስራ አጥ ወጣቶች ለስደት መደረጋቸው ይብቃ፣ ወረዳችን የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ እያለ ትኩረት ሰጥቶ ባለመሰራቱ ድሆች ሆነናል፤ ብአዴን እኛን አይወክለንም፣  የኤሌክትሪክ፣ የባንክና የሆስፒታል አገልግሎቶች በወረዳችን ላይ እስካሁን ባለመሟላታቸው ትዕግስታችንን እንድንጨርስ እያደረገን ነው” የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ተስተናግደዋል።

በጀርመን አርበኞች ግንቦት7 የተሳካ የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ ሲሰራ፣ በአውስትራሊያ ህወሃት የጠራው ስብሰባ በተቃውሞ ተቋረጠ።

ሰኔ ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አርበኞች ግንቦት ሰባት ከትናንት በስቲያ በጀርመን ፍራንክፈርት የተሳካ ህዝባዊ ስብሰባና የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ሊቀመንበሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በተገኙበት አካሂዷል። ስብሰባውን ለመቃወም የገዢው ስርዓት በኤምባሲው አማካይነት በመላ አውሮፓ የሚገኙ ደጋፊዎቹን ሰልፍ እንዲወጡ የጠራ ቢሆንም በሰልፉ ላይ ሊገኙ የቻሉት ግን አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎቹ ሲሆኑ ስብሰባውን ለመታደም የተገኙ ወገኖች በጣም በርካታ ከመሆናቸው የተነሳ አዳራሹ ሞልቶ ብዙዎች መግባት ሳይችሉ ለመመለስ ተገድደዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በአውስትራሊያ በካንቤራና በሜልቦርን ህወሃት የጠራው የድጋፍ ስብሰባ በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባሰሙት ጠንካራ ተቃውሞ ስብሰባው በአውስትራሊያ ፖሊስ እንዲሰረዝ ተደርጓል። የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አባይ ወልዱ ፤ የሶማሌው ክልል ፕሬዘዳንት አብዲ መሃመድ ኡመር  እንዲሁም የኦሮምያ ክልል ፕሬዘዳንት ሙክታር ከድር እና የፌደሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ አቶ ያለው አባተ በሜልቦርን ከተማ ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።