Tuesday, February 2, 2016

በጋምቤላ የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ

ጥር ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከአካባቢው የተገኘው አስተማማኝ መረጃ እንደሚያመለክተው በጋምቤላ ከተማ፣ በአቦል፣ በለሬ፣ በኢታንግ፣ በተሪፋም፣ በስደተኞች ካምፖች፣ በኚንኛንግ፣ አቦቦ፣ አሌሮና በሌሎችም አካባቢዎች እየተካሄደ ባለው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በእየቀኑ በአማካኝ ከ10 በላይ ሰዎች እየተገደሉ መሆኑንም የደረሰን መረጃ ይጠቁማል። በዛሬው ቀን ብቻ 2 ኑዌሮች በአጋዚ ወታደሮች ሲገደሉ፣ 5 የንዌር የልዩ ሃይል አባላት በአኝዋኮች ተገድለዋል። በአኝዋኮች በኩልም የሞቱ ሰዎች መኖራቸውንና የአስከሬን ፍለጋ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ጋምቤላ ከሁለት የተከፈለች ሲሆን፣ ከባሮ ወንዝ ድልድይ በላይ ኒውላንድ ተብሎ በሚጠራው አካ...ባቢ ኑዌሮች ሰፍረው ሲገኙ፣ በተቀራኒው ደግሞ አኝዋኮች ይገኛሉ። የአንደኛው ብሄረሰብ አባል ድልድዩን ከተሻገረ በሌላው ብሄረሰብ አባል የሚገደል መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ በሌሎች ወረዳዎችም በተመሳሳይ መንገድ ክፍፍል ተፈጥሮ ዜጎች እያለቁ ነው።
በኢታንግ ወረዳ ደግሞ የአጋዚ ልዩ ኮማንዶ ጦር እንዲገባ ተደርጓል። ወታደሮቹ ከባድ መሳሪያዎችን ጠምደው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ሲሆኑ፣ ዛሬ 2 የንዌር የልዩ ሃይል አባላትን ገድለዋል። መሳሪያ ታጥቀው አንፈታም ባሉት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የክልል አስተዳዳሪዎች እንዲፈርሙ ተገደው መፈረማቸውም ታውቋል።
የክልሉ ዋና እና ምክትል ፕሬዚዳንቶች በቁጥጥር ስር ውለው አጠቃላይ ክልሉ በአጋዚ የመከላከያ አመራሮች እየተመራ ነው፡፡ የግልና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል።
ኒውላንድ በሚባለው የኑዌሮች አካባቢ የደቡብ ሱዳን ባንዲራ ተሰቅሎ እንደሚውለበለብ የአይን እማኞች ገልጸዋል።
መንግስት በአኝዋኮች ላይ የወሰደው ተደጋጋሚ እርምጃ፣ የአኝዋኮች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉን የሚናገሩት ምንጮች፣ አኝዋኮች የመንግስትን ፖሊሲ አይቀበሉም በሚል ስሜት በክልሉ ያላቸውን ስልጣን እንዲያጡ እንዲሁም ከደቡብ ሱዳን የመጡ ኑዌሮች በቋሚነት እንዲኖሩ ከተፈቀደላቸው በሁዋላ የአካባቢውን ህዝብ ቊጥር ሚዛን በማዛባትና ስልጣኑን ተቆጣጥረው እንዲይዙ በማድረግ መንግስት አካባቢውን ለመቆጣጠር ባለፉት 10 ዓመታት ተከታታይ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ። ይሁን እንጅ የኑዌሮች ቁጥር ማዬል ከደቡብ ሱዳን ጋር በተያያዘ ሌላ ችግር እየተፈጠረበት መምጣቱን የሚገልጹት እነዚህ ወገኖች፣ በተለይም በኒውላንድ አካባቢ የደቡብ ሱዳን ባንዲራ እንዳይሰቀል ያወጣው መመሪያ በየጊዜው እየተጣሰ መቸገሩን ይናገራሉ።
መንግስት ሁለቱን ህዝቦች በማጋጨት አካባቢውን ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እንደከተተው የሚገልጹት እነዚህ ወገኖች፣ ወታደራዊ መፍትሄ ለመፈለግ የሚያደርገው ሙከራ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ እንደማያመጣለት በማናገር ላይ ናቸው።

No comments:

Post a Comment