Tuesday, February 16, 2016

ከ200 በሚበልጡ ወረዳዎች ውስጥ ከፍተኛ የውሃ እጥረት መፈጠሩን አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ገለጹ

ኢሳት (የካቲት 8 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የድርቅ አደጋ ተከትሎም ከ200 በሚበልጡ ወረዳዎች ውስጥ ከፍተኛ የውሃ እጥረት መፈጠሩን አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ገለጡ።
...
በነዚሁ ወረዳዎች ውስጥ ተከስቶ ያለውን የውሃ እጥረት መቅረፍ ካልተቻለ ችግሩ በነዋሪዎች ላይ ጉዳትን ሊያስከትል እንደሚችልም የብሪታኒያው ኦክስፋም እና ወርልድ ቪዥን የተባሉ ድርጅቶች አስታውቀዋል።
በወረዳዎቹ ውስጥ እየታየ ያለው የውሃ እጥረት የድርቁ አደጋ የሚያደርሰውን ጉዳት የከፋ ሊያደርገው እንደሚችል ያሳሰቡት የግብረ-ሰናይ ድርጅቶቹ፣ በአጠቃላይ 209 ወረዳዎች በዚሁ ችግር መጠቃታቸውን ገልጸዋል።
በሃገሪቱ ለአስቸኳይ የምግብ እጥረት በተጋለጡ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መካከልም ወደስድስት ሚሊዮን የሚጠጉት አስቸኳይ የውሃ አቅርቦት የሚፈልጉ መሆናቸውም ታውቋል።
ለአስቸኳይ የምግብ እጥረት በተጋለጡ ሰዎች ከሚያስፈልገው የምግብ እርዳታ በተጨማሪ የውሃ አቅርቦቱ ጊዜ የማይሰጠው መሆኑንም የእርዳታ ድርጅቶች አስታውቀዋል።
የተባበሩት መንግስታትና ሌሎች የእርዳታ ጅርጅቶች በበኩላቸው ለተረጂዎች የሚሆን የምግብ አቅርቦትን በማለቅ ላይ መሆኑ ስጋትን ፈጥሮ እንደሚገኝ በድጋሚ ገልጿል።
በሀገሪቱ ያለው የእህል ክምችት ለሁለት ወር ጊዜ እንኳን እንደማይበቃ ያስታወቁት ድርጅቶቹ፣ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ እርዳታን የማያቀርብ ከሆነ ድርቁ መልኩን ሊቀይር እንደሚችል አሳስበዋል።
የእርዳታ እህልን ከውጭ ሃገር ገዝቶ ወደኢትዮጵያ ለማጓጓዝም በትንሹ ሶስት ወር የሚፈጅ በመሆኑ ጉዳዩ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድጋሚ ገልጿል።
በስድስት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ በርካታ ዞኖች ውስጥ ጉዳትን እያደረሰ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል ከ 1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ በእስካሁኑ ሂደትም ግማሽ ያህሉ ብቻ ሊገኝ መቻሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክቷል።

No comments:

Post a Comment