Tuesday, February 9, 2016

በጉጂ ዞን ተቃውሞው ቀጥሎአል

የካቲት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለወራት ሲንከባለል የቆየው የጉጂ ዞን ህዝብ የመብት እና የኢኮኖሚ ጥያቄ ከፌደራል እና ከክልሉ መንግስት ምላሽ መነፈጉን ተከትሎ ወደ አደባባይ የወጣው ህዝብ፣ ተቃውሞውን አጠናክሮ ቀጥሎአል።
ትግሉ በጎበዝ አለቃ እየተመራ በመካሄድ ላይ መሆኑን የተቃውሞው ተሳታፊዎች ይገልጻሉ።...
ተቃውሞውን ለመቆጣጠር የፖሊስ ሃይል በብዛት ቢሰማራም፣ ሊያስቆመው አልቻለም። የሼክ ሙሃመድ አላሙዲን የወርቅ ማምረቻ ኩባንያም ከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ እየተደረገለት ነው። የድርጀቱ መኪኖች ከቦታ ቦታ መዘዋወር አቁመዋል።

ነዋሪዎቹ ሚድሮክ ወርቅ ከአካባቢያቸው ለቆ እንዲወጣ፣ የታሰሩት እንዲፈቱ እና ለወራት ያቀረቡዋቸው የመልካም አስተዳደር፣ የአስተዳደርና የአገልግሎት ጥያቄያቸው እንዲመለሱላቸው ይጠይቃሉ።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮችን ከመሬት ይዞታ ባለቤትነት የሚያፈናቅለውን ማስተር ፕላን በመቃወም ሰላማዊ ጥያቄያ ያነገቡ ከ140 በላይ ተማሪዎችና አርሶአደሮች መገደላቸው፣ ኢትዮጵያ ገና ያልተሻገረቻቸው የፖለቲካ ጥያቄዎች መኖራቸውን ፋይናንሺያል ታይምስ ዘግቧል።
መላውን የኦሮሚያ ክልል ባናወጠው ሕዝባዊ ማዕበል ፣ አብዛሃኛው የክልሉ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ምሁራንን ጨምሮ የተቃውሞው አጋር መሆናቸውን አሳይተዋል። በጫንጮ፣ሱሉልታ አካባቢ ያሉ አርሶአደሮች በበኩላቸው በቂ የሆነ ካሳ ሳይከፈላቸው የእርሻ ማሳቸውን ለፋብሪካና ለቤት መስሪያ እንዲውል በሚል ሙሰኛ ባለስልጣናት ከነባር ይዞታቸው እንዳፈናቀሉዋቸው ገልጸዋል።
በአናሳዎቹ የሕወሃት መሪዎች የበላይነት በሚመራው የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ውስጥ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች ወደ ጎን ተገፍተው የውሳኔ እና የኤኮኖሚ የበላይነቱን በሙስና ሰንሰለት ሕወሃቶችና ከእነሱ ጋር የተሳሰሩት ተቆጣጥረውታል ሲል ጋዜጣው ዘግቧል።
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ያልበቃቸው ባለስልጣናትና ባለሃብቶች በጥምረት ወደ የኦሮሚያ አዋሳኝ ቀጠናዎች በማስፋት ገበሬውን መሬት አልባ የሚያደርገውን አሰራር የስራ እድል እንደሚፈጥር ሲናገሩ ይደመጣል። ይህ ከድሃው ላይ የእርሻ መሬቱን ነጥቆ ለባለሃብት ለመስጠት የሚደረገው ሕዝቡ ያልመከረበት ጉዳይ መሆኑን የጫንጮ ነዋሪዎችን በመጥቀስ ጋዜጣው ዘገባውን ይቀጥላል።
አንድ የጫንጮ አርሶአደር በመሬታቸው ላይ ለልጆቻቸው ቤት ለመስራት እንዳልተፈቀደላቸው ገልፀዋል። ሌላው አርሶ አደር ደግሞ መሬታቸውን በአነስተኛ ክፍያ በአካባቢው ሹመኞች ተነጥቀው ከይዞታቸው መነሳታቸው ተናግረዋል። ሙሰኛ የሆኑ ፖለቲከኞችና አስተዳዳሪዎች አይወክሉንም በማለት ሕዝቡ መቃወሙን ዶክተር መረራ ጉዲና ለጋዜጣው ገልጸው፣ የተቃውሞው መነሻ የመገፋት፣ የፍትና የነጻነት እጦት ነው ሲሉ ያክላሉ።
አንድ ስሙን መግለጽ ያልፈለገ ወጣት የኦሮሚያ ክልል ምሁር በበኩሉ ሕዝቡ የሚፈልገውና የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች እና መንግስት የሚሰራው አይገናኙም ብሎአል። "ሕዝብ ይሁንታን ሳይሰጥ ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም። በየዓመቱ ከመቶ ሺህ በላይ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ተመርቀው ይወጣሉ። የሥራ ዋስትናን ጨምሮ የዴሞክራሲ ጥያቄዎቻቸውን የሚመልስ ተቋም የለም። የተሰማንን ስሜት ለመግለጽ ነፃነት የለንም። ይህ ማለት ደግሞ ነፃ ያልሆነ ሕዝብ የእድገትና ብልፅግና ተቋዳሽ አይሆንም።" በማለት አክሏል።
መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ አንድ የቀጠናው ዲፕሎማት "ምንም እንኳ ስርዓቱ ጠንካራ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በቋፍ ላይ የምትገኝ አገር ናት" ብለዋል።

No comments:

Post a Comment