Thursday, December 24, 2015

ወያኔ ድብቅ ፍላጎቱን ለማሳካት የህዝብ ደም እስከመቼ እንዳፈሰሰ ይቀጥላል??? (የአብስራ ዳኛቸዉ)


  ሃገራችን ኢትዮጵያ ክብሯ ተነፍጎ የህዝቦቿ መብት እና ጥያቄ ተረግጦ ያለፍላጎቷ በብሄር እና በጎሳ ተከፋፍላ በጥቂት እራስ ወዳዶች በተያዘ ስልጣን እንዳሻቸው እያደረጉ የሀገር ፍቅር እና ንፁህ አእምሮ የሌላቸውን በሆዳቸው በመደለል የራሳቸው አሽከር በማድረግ ለእውነት እና ለህዝብ እኩልነት የቆሙትን ደግሞ በፈለጉት መንገድ በማስወገድ የራሳቸውን ድብቅ ፍላጎት ለማሳካት የህዝብ ደም በማፍሰስ እድሜያቸውን ለማራዘም ከበፊቱ የበለጠ ቀጥለዋል።

ሰሞኑን ከበፊቱ በበለጠ በሀገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው የንፁህ ህዝብ ደም መፍሰስ ከላይ በመግቢያዬ እንደገለፅኩት ትልቅ ተጠቃሽ ማረጋገጫ ነው። የወያኔ ባለስልጣናት አዲስ አበባን ማስፋፋት አለብን በማለት የሚይዙት የሚጨብጡት ያስጣቸው አ/አ የሀገራችን ዋና መዲና እና ከዛም አልፎ የአፍሪካም ስለሆነች ከበፊቱ ሰፋ ብላ መዋብ አለባት የሚለው አስጨንቋቸው አይደለም። በውስጣቸው እንደ እባብ መርዝ የተደበቀ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ነው። ይሄውም አ/አን ከሚያዋስናት የኦሮሚያ ክልል መሬት ላይ ወደ አ/አ ክልል ካስገቡ በኃላ ከዚህ በፊት እንደለመዱት መሬቱን ተቀራምተው ለራሳቸው እና ለዘመዶቻቸው በማድረግ በውጪ ሀገራት በሚገኙ ባንኮች ከሀገራችን ዘርፈው ያሸሹትን ረብጣ ገንዘብ ላይ በመደመር የሀብት መጠናቸውን ለማሳደግ ነው። በውጪ ካስቀመጡት ዶላር በተጨማሪ ደግሞ በአንድ የመንግስት ተቀጣሪ ደሞዝተኛ ሊገነባ አይደለም ሊታሰብ የማይችል የተቀማጠለ መኖሪያ በመገንባት ህዝባችን የሚቀመስ አጥቶ ወያኔዎች አዲስ ቤታቸውን እያስመረቁ በውስኪ ይራጫሉ። ምናልባት ኦሮሚያስ ቢሄዱ መሬቱን የሚያዝበት ራሱ ወያኔ አይደለ ወይ ልትሉኝ ትችላላችሁ ልክ ነው አልተሳሳታችሁም ነገር ግን ወያኔ መሬቱን በኦሮሚያ ክልል እንዳለ ልቸብችበው ቢል ያሰበውን ያህል ገንዘብ ማጋበስ አይችልም። መቼስ አ/አ መስተዳድር ስር ያለው የመሬት ዋጋ ይጠፍችኃል ብዬ አላስብም።ለዚህ ደግሞ በአ/አ እና ዙሪያዋ ከገዛ መሬታቸው የተፈናቀሉ ገበሬዎች የወያኔን ድብቅ የፍላጎት ማሳያ ምስክር ናቸው።
ታዲያ ይህን ድብቅ ፍላጎታቸውን የተገነዘበው ህዝብ በግፍ ሲበደል የገዛ ሀገሩን ለቆ በመሰደድ ያልሆነለት ደግሞ ጭካኔያቸውን እየተመለከተ ምንም ማድረግ ባለመቻሉ እየተብሰለሰለ በችግር ና በከፋ ህይወት ውስጥ መኖር ግድ ሆኖበት ሳለ እነሱ ግን ልባቸውን የደፈነው ትምክህት እና አጋባሽነት አይኑን አፍጦ እየወጣ ይገኛል።
ሰሞኑን በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች እየታየ ያለው ተቃውሞ የሚያሳየው ይሄንኑ ነው። በተለይ በኦሮሚያ የወያኔን ማስተር ፕላን ማስፋፊያ እቅድ በመቃወም ተቃውሟአቸውን የገለፁ ኢትዮጵያውያን ዜጎቻችን ላይ ቅንጣት ያህል ርህራሄ ሳይኖራቸው ለሆዳቸው አድረው ከወያኔ ጋር በተጣበቁ ወታደሮች ተጨፍጭፈዋል። በተለያዩ ድህረ ገፃችና በሚዲያዎች ላይ እንደተመለከትነው በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ማለትም በወለጋ፣አንቦ፣ሃሮማያ፣ሁሌቦራ፣ ዲላ ያሉ ተማሪዎች እና እንዲሁም አመያ፣ቦረና፣አወዳይ፣አንቦ፣ምዕራብ ወለጋ፣ምዕራብ ሸዋ፣ጀልዱ፣ቡራዩ፣ እንዲሁም ወሊሶ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። በሰለጠነው አለም የህዝብ ተቃውሞ ይከበራል። መንግስታት ከህዝብ ፍላጎት ውጪ መሆን እንደሌለባቸው ተገንዝበው ህጋቸውን እስከመቀየር ይደርሳሉ ለምን ቢባል ለነሱ ከህዝባቸው ፍላጎት በላይ ምንም ነገር አይቀድምም። በወያኔ እጅ የወደቀው ወገኔ ግን እውነትን ይዞ በአደባባይ ወጥቶ ሲቃወም አደባባይ ላይ ደሙ ፈሰሰ። እናት ዘጠኝ ወር በሆዷ ይዛ አምጣ ወልዳ አስተምራ ለማዕረግ ያደረሰችውን ወጣት ከጉያዋ እንዳይወስዱባት በመማፀኗ በጥይት ተደብድባ ተገደለች። ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች ማለት ይሄ ነው። ዳሩ ልጇን ላታስጥል ደሟ ፈሶ ቀረ ልጇም በግፈኞች ጦር ቆሰለ።በሌላ ቦታ ደግሞ ልጁ በሰላም ከቤት ወጥቶ ሳይመለስ በዛው የቀረበት አባት እንባውን እያፈሰሰ በገዛ ሀገሩ ፍትህ አጥቶ አንገቱን ደፋ። ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ወጣቶች ከወያኔ በተለቀቁ አውሬዎች ግንባር ግንባራቸውን ተነደሉ። በዚህ አይነት ሁኔታ ከ80 ሰው በላይ ህይወቱን አጥቷል። እኔ ወገኖቼን የምጠይቀው እውነት ወንጀል ሰርተዋል ወይስ ወያኔ ያሻውን ሲያደርግ መቃወም የህይወት ዋጋ ያስከፍላል??? እርግጥ ነው ክቡር የሰው ልጅ ህይወት በወያኔ መነፅር ቦታ የለውም ወይንም ደግሞ ወያኔ እንዲያዝንልን ሰው በላ ካድሬ መሆን አለብን።
በተመሳሳይ ሁኔታ በጎንደርም የተከሰተው ነገር ልብ የሚያደማ ነው። ወያኔ ከጎንደር መሬት ላይ ቆርሶ ለሱዳን ለመስጠት ሽርጉድ እያለ ነው። ወያኔ ይህንን የሚያክል ለም መሬት ለሱዳን መስጠት የፈለገው የጎረቤት ፍቅር አስጨንቆት ወይም ሱዳኖች መሬት ካልመፀወታችሁን ብለው ደጅ ስለጠኑ አይደለም። ከዚህም ሌላ ሱዳኖች ጥንት ያባቶቻችን ዕርስት ነበር ለኛ ይገባናል ካልሆነ ነፍጥ እናነሳለን ብለውም አይደለም። ምናልባት ወገኖቼ ታዲያ ለምን ይሆን ወያኔ ከ1600ኪሜ. በላይ ቦታ ከውዲቷ ሀገራችን ቆርሶ መስጠት የፈለገው ልትሉ ትችላላችሁ። መልሱ በመግቢያዬ እንደተናገርኩት ወያኔ ድብቅ ፍላጎቱን ለማሳካት በማሰቡ ነው። ይሄውም ከጎንደር ቆርሶ ለሱዳን የሚሰጠው መሬት የአደራ መሬት ነው እንጂ እስከነአካቴው የሱዳን ሆኖ እንዲቀር አይደለም።ምክንያቱም ወያኔ እንደሚታወቀው ታላቋን ትግራይ የመመስረት እቅድ አለው ከዚህ አንፃር እንደምናውቀው ትግራይ የሚታረስ። ለም መሬት የላትም ቢኖራትም እጅግ በጣም ጥቂት ነው። ስለሆነም የወጠኑት ተሳክቶ የአሁኗ የኢንደስትሪ ከተማ መቀሌ አስፈላጊ የሆነውን የግብርና ምርት በኃላ በእጅ አዙር ወደራሷ በመመለስ ግዛቷ ከምታደርገው ከዛሬው ጎንደር መሬት ይሆናል።
ታዲያ ይህንን የተረዳው የጎንደር እና የአካባቢው ህዝብ የአባቶቼን መሬት አሳልፌ አልሰጥም በማለት ነው ተቃውሞውን የገለጸው። ወያኔ ህዝቡን ለማሳመን እንዳቀናበረው ተረት ተረት ከሆነ በቀኝ ግዛት ጊዜ እንግሊዛዊያን ሱዳንን በሚያስተዳድሩበት ጊዜ ቦታው ወደ ሱዳን ግዛት እንዲሄድ ኢትዮጵያ ተስማምታለች ነው የሚለው። ያንን ውል እየተገበርኩ ነው የሚለው ። ከተለያዩ ቦታዎች የተወጣጡ የሃገር ፍቅር የሚሰማቸው ወገኖች ኮሚቴ አቋቁመው ወያኔ መሬታችንን ቆርሶ ለመስጠት እያደረገ ያለው ነገር እጅጉን ስላስቆጣቸውና የሃገራችንንም ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ስለተረድት  ድምጽቸውን ለአለም ለማሰማት የአቅማቸውን እየደከሙ ነው። ኢትዮጲያዊያን ወገኖቻችን በኢ-ሜልና በፋክስ ፒቲሽን በማሰባሰብ ለአለም አቀፍ ድርጅቶች ተቃውማችንን በመግለፅ ከዚህ ኮሚቴ ጎን መቆም ይኖርብናል።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በወልቃይት እና አካባቢው ያሉትን ነዋሪዎች ወደ ትግራይ ክልል ያለአግባብ እና ያለህዝቡ ፍላጎት ማካተቱ ነው። በመሰረቱ የወልቃይት ህዝብ የሚናገረው አማርኛ ቋንቋ ነው ሲቀጥል ደግሞ ህዝቡ ከትግራይ ወግና ባህል ይልቅ ተወልዶ ያደገበትን የአማራውን ክልል ነው በይበልጥ የሚያቀው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የህዝብን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው በግድ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ መደረጉ ነው የተቃውሞው መንስኤ።
እንደሚታወቀው ወያኔ ብሔርን ከብሔር ማናከስ በዋነኛው የዕድሜ ማራዘሚያ መንገዱ ነው። ለዚህም ነው ከአመታት በፊት በአማራ ክልል ስር የነበረውን የቅማንትን ህዝብ ወደ ትግራይ በማቀላቀል የራሱን ካድሬዎች በመሾም እና መሳሪያ በማስታጠቅ በቅማንት ህዝብ ስም አድርጎ የአማራ ተወላጆችን  እየጨረሰ በመሆኑ ነው። ባለቤቷን በእንደዚህ ሁኔታ ያጣች አንዲት የአማራ ተወላጅ ድርጊቱ የማን እንደሆነ በጋእድ እያነባች ገልጻለች።
ሌላው የህዝብ አመጽ ወያኔ በጎንደር እስር ቤት ውስጥ እሳት ሲነሳ ነፍሳቸውን ለማዳን በወጡ እስረኞች ላይ የቶክስ እሩምታ በመክፈት ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆነ ሰዎች በመግደሉ ነው። ፍርዱን ለኢትዮጰያ ህዝብ እንስጠውና መጀመሪያ ክቡር የሰው ህይወትን ማዳን ይቀድማል ወይስ አመለጡ ብሎ በጥይት እስከወዲያኛው እንዲያሸልቡ ማድረግ?
የኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ የወያኔ ክፉ ምግባሩ ብዙ ነው ህንዲህ በአጭሩ ተዘርዝሮ የሚያልቅ ስላልሆነ ወደ ማጠቃለያ ልምጣ እኛ ድምጻችን ተነጥቆ ፣ለፍትህ አጥተን ፣እየተራብንና የኑሮ ንረት እያንገላታን ችለን እየተገዛንላቸው ወያኔዎች ግን ጥጋብ አንገታቸውን አደንድኖታል። የንጹህ ሰው ደም በከንቱ እየፈሰሰ አባቶቻችን አስከብረው ያቆዩአትን ዞሮ መግቢያችንን እና መጠሪያችን የሆነች ሃገራችን የኢትዮጵያን እየበለቱ እና እየሸረፉ ሊጨርሱብን ነው።ነገ ስሟን ብቻ ሊያስቀሩልን ከፍ ዝቅ እያሉ ነው። ዛሬ እኛ ዝም ብለን ብናይ ነገ የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን አንድንም። ኢትዮጵያዊነት ማንነቴ ነው ብለን ካመንን ሁላችንም በየፊናችን እቺን ምትክ የሌላት ሃገራችንን እና ህዝባችንን በቡድን ሆነው ከሚመዘብሩ የወያኔ ባለስልጣናት እንታደጋት። ከመቶ አመት ባርነት የአንዲት ቀን ነጻነት ለህሊናችንም ሆነ ለሃገራችንም ትልቅ ቁም ነገር ነው። ባርነት ይባቃን።

No comments:

Post a Comment