Thursday, December 31, 2015

የአገራችን መሬት ሲቆረስ ፣ ህዝባችን ሲጐዳ እጆቻችንን አጣምረን አንቀመጥም! — ከቀድሞው የኢትዮጵያ የሀገር የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አርበኞች ማህበር

ከቀድሞው የኢትዮጵያ የሀገር የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አርበኞች ማህበር የቀረበ ወቅታዊ ጥሪ

እኛ የቀድሞው የኢትዮጵያ የሀገር የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት ዓባላት ለአለፉት 25 ዓመታት በውድ የሃገራችን ሕዝብ ላይ ወያኔ/ህውሃት መራሹ ቡድን የፈፀመውና እየፈፀመ ያለውን ግፍ ፣ በደልና ሰቆቃ እንዲቆም የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ትግል መሆን እንዳለበት እናምናለን ። ይሁን እንጅ የሕዝባችንን ሰቆቃና መከራ፣ ስደትና ዕልቂት ከምንም ባለመቁጠር ይባስ ብለው የሃገሪቷን ልዑላዊነት ለታሪካዊ ጠላቶቻችን አሳልፈው ለመስጠት ሽር ጉድ በማለት ላይ ይገኛሉ
Former Ethiopian Defense Force Veterans Association
በኢትዮጵያ የረጅም ታሪክ ውስጥ የሃገሪቷን ዳር ድንበር ለባዕድ አሳልፎ ለመስጠት የተደራደረ መንግስት ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም ፣ ሃገሩንና ድንበሩን እንዲጠብቅ አደራ የተሰጠውም ወታደርና የፖሊስ ሠራዊት የዚህ እኩይ ተግባር ተባባሪ የሆነበት ዘመን አልታየም።
ከሁሉም በላይ የህውሃት አቀንቃኝ ካድሪዎች በየጊዜው ከሚጎነጉኑት የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ የሃገሪቷን ታላላቅ ብሄረሰቦች እርስ በርስ በማናቆር የጥላቻ ዘር በማህከላቸው በመበተን ስልጣኑን ለማራዘም ሁነኛ መሳሪያ አድርጎት ይገኛል። እንደእኛ እምነት ይህ ተንኮል በርግጥም ይህን ግፈኛ ሥርዓት ሃያ አምስት ዓመት እንዲቆይ ረድቶታል ብለን እናምናለን።
ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ይህ ሥርዓት በሃገራችን ታላላቅ ሃይማኖት መሃከል ጣልቃ በመግባት ለራሱ መሰሪ ተግባር በሚያመች መልኩ በማዋቀርና የሃይማኖት መሪዎችን በማሰር፣ በማንገላታት ፣ በመግረፍንና ብሎም ለስደት በመዳረግ የሃይማኖት ነፃነትን ገፏል ።
በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ሃይሎችንም በማሰርና በመግደል የቀሩትንም እንዲሰደዱ በማድረግ ድርጅቶቻቸውን በማፍረስ ህዝባችን ለሰላም ያለውን ተስፋ እንዲጨልምበት አድርጓል በማድረግም ላይ ይገኛል።
በከተሞች ልማት ስም ህዝቦችን ከቀያቸውና ከመሬታቸው በማፈናቀል ለውጭና ለሃገር ውስጥ ቱጃሮች መሬት በመሸጥ ህዝቡን ለእንግልትና ለስደት ዳርጎት ገበሬውን መሬቱን በመንጠቅ ለጐዳና ተዳዳሪነት ሲዳርግ ፤ ብሶቱንም በሰላማዊ መንገድ ለማሰማት የወጣውን ህዝብ ደግሞ በጥይት መደብደቡን ተያይዞታል ።
የመከላከያ ፣ የፖሊስና የደህንነት አደረጃጀትና መዋቅር በአንድ አናሳ ብሔር የተያዘ በመሆኑ ፤ በስልጣን ተዋረድም ከላይ እስከ ታች በሙስና እንዲዘፈቁ ምቹ ሁኔታን በማመቻቸት ስርዓቱ ግለሰቦችን በሙስና እንዲከብሩና የአገሪቱ አንጡራ ሃብት እንዲባክን አድርገዋል ።
ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ !
እኛ የቀድሞው የኢትዮጵያ የሀገር የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላት ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት ከአካል እስከ ህይወት መስዋዕትነት ስንከፍል እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው ። በጊዜው ስለ እነዚህ መሰሪ ኃይሎች ለሕዝባችን ስንገልፅ የነበረውም አንዳንች ስህተት እንዳልነበረ ለማረጋገጥ ችለሃል፥ አሁንም እኛ የሕዝባችን እና የሃገራችን ችግር ችግራችን ፣ ሰቆቃውም ሰቆቃችን መሆኑን ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመግለፅ እንወዳለን።
በመሆኑም የዚህ ግፍ አገዛዝ በቃ ሊባል እንደሚገባው እንረዳለን ። ስለዚህ ወትሮም የገባነውን ቃል ኪዳን በማደስ እኛ የቀድሞው የኢትዮጵያ የሀገር የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት ዓባላት አቅማችንና ሙያችን በሚፈቅደው ሁሉ ከሕዝባችን ትግል ጎን የምንቆም መሆናችንን እናረጋግጣለን ።
ስለዚህ ግፍ ሲበዛ ዝምታ አይመረጥምና
ውድ የአገር የመከላከያ ሰራዊት ሆይ –
1. እያንዳንዱ የቀድሞው ሰራዊት አባላት በያለህበት ሆነህ በመደራጀትና በመቀናጀት ፣ እርስ በእርስ በመናበብ ብሶት ከወለደው ከጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ጐን እንድሰለፍ ጥሪ እናቀርባለን ።
2. በየትኛውም የአገሪቷ ክልል በሚደረገው የነፃነት ትግል የተቀጣጠለውን ህዝባዊ አመፅ እንድትቀላቀል በሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ስም እንጠይቃለን ።
3. ለስርዓቱ እድሜ መራዘም ምክንያት የሆነው የሁለቱ ታላላቅ ህዝቦች (የአማራና የኦሮሞ) እንዲሁም ከተቀረው ህዝባችን ጋር ልዩነትን በማስወገድና በመቻቻል የጋራ ጠላት ለሆነው የወያኔ ቡድን ትግልህን በማቀናጀት ክንድህን አንሳ ።
4. የአጋዚ ልዩ ኃይል ኰማንዶ ማዕከል በመባል የሚታወቀው የሥርዓቱን ዕድሜ አራዛሚና ጠባቂ ሰራዊት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየፈፀመ ካለው ከጭካኔ ተግባሩ እጁን እንዲሰበስብና እንዲታቀብ ታደርግ ዘንድ በኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ስም ጥሪ እናቀርባለን ።
5. ከህዝብ አብራክ የወጣህ እንደመሆንህ መጠን ፣ ያንተ ወገን አባትህ ፣ እናትህ ፣ ወንድምህ ፣ እህትህ ፣ አጐትህ ፣ አክስትህ እስከመቼ ድረስ እየታሰሩ ፣ እየተቀጠቀጡ ፣ እየተደበደቡ ፣ ከገዛ አገራችው እየተሰደዱ ፣ በግፍ እየተገደሉ የሚኖሩት ? ስለዚህ አንተ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋሻና መከታ የሆንከው ሰራዊት ሆይ በአገራችን እየደረሰ ያለው ግፍና በደል ያንተም ነውና ይህንን አስከፊ የጥፋት ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ከህዝባዊ አመፁ ጐን እንድትቆም በኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ስም እንጠይቃለን ።
ድል፣ፍትህ፣ ነፃነትና እኩልነት ለኢትዮጵያ ህዝብ !
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !

No comments:

Post a Comment