Thursday, December 10, 2015

አምነስቲ ኢንተርናሽናል መላው ዓለም በእስር ቤት ያሉትን ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞችን እንዳይዘነጋ ጥሪውን አቀረበ

ኀዳር ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀንን ምክንያት በማድረግ ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሽብር ሕግ ተከሶ ከአራት ዓመታት በላይ በእስር የሚማቅቀውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ካለ ወንጀላቸው ከስራ ገበታቸው ታፍነው በወሕኒ የሚማቅቁትን ኢትዮጵያዊና ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጓቾችን መላው ዓለም ለአፍታም ሊዘነጋቸው እንደማይገባ መግለጫ አውጥቷል።

ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ለሶስቱ የአልጀዚራ ጋዜጠኞች ፒተር ግሬትስ፣ መሃመድ ፋህሚና ባሄር ሙሃመድ ድምጹን እንዳሰማ ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሕግ ውጪ ታስረው የሚገኙትን እስክንድር ነጋ፣ተመስገን ደሳለኝ፣የሱፍ ጌታቸው፣ ሰሎመን ከበደ፣ ውብሸት ታዬ፣ ሳልህ ኢድሪስ፣ ተስፋልደት ታዬን ጨምሮ አያሌ ጋዜጠኞች በእስር እንደሚገኙ አስታውሶ የጸረሽብር ሕጉ የጋዜጠኞችን ነጻነት የሚጋፋና መብታቸውን የሚጥስ መሆኑን አመልክቷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከዓመት በላይ በእስር ቤት ቆይተው የተለቀቁትን የዞን 9 ጦማሪያንን መንግስት ክሳቸውን አንስቶ በነጻ መልቀቁ የሚያሳየው ነገር ቢኖር ገዥው ፓርቲ በሕግ ስም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚጥስ መሆኑን ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ካለምንም ቅድመ ሁኔታዎች በእስር የሚያሰቃያቸውን ጋዜጠኞች በነጻ እንዲለቅ አሳስቦ መላው ዓለም ከኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች ጎን እንዲቆም ጥሪውን አቅርቧል።

No comments:

Post a Comment