Monday, December 28, 2015

መንግስት በሃይል ሊያዳፍነው የሞከረው ተቃውሞ እንደገና አገረሸ

ታኀሳስ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ መንግስት አጋዚ የሚባለውን ጦሩን በማሰማራት ሊጨፈልቀው ያሰበው ህዝባዊ ተቃውሞ እንደገና አገርሽቶ በርካታ ተማሪዎች ታስረዋል። በወለጋ ዩኒቨርስቲ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ የአጋዚ ወታደሮች በወሰዱት እርምጃ በርካታ ተማሪዎች ተደብድበው ታስረዋል። ተማሪዎቹ ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል ወደ ጫካዎችና አጎራባች ከተሞች ቢያመልጡም ወታደሮቹ እግር በእግር እየተከታተሉ በመደብደብ አስረዋቸዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ወታደሮቹ ከትናንት በስቲያ በአምቦ ዩኒቨርስቲ ገብተው በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ድብደባ ያደረሱ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችም ተይዘው ታስረዋል።
ዛሬ ደግሞ በሰሜን ሸዋ ኤጄሬ ከተማ ተማሪዎች ተቃውሞ ሲያሰሙ ውለዋል። ተቃውሞውን ተከትሎ ፖሊሶች በወሰዱት እርምጃ ተማሪዎች ተጎድተዋል።
መንግስት የተነሳበትን ህዝባዊ ተቃውሞ በሃይል ለመጨፍለቅ ባደረገው ሙከራ እንደ ምስራቅ አፍሪካ የሰብአዊ መብት ሊግ 122 ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ድርጅቱ የሟቾቹን ስም ፣ የትውልድ ቀንና ቦታ በዝርዝር አቅርቧል።
ህዝባዊውን ጥያቄ በሃይል ለመጨፍለቅ ከፍተኛ ሰራዊቱን ያሰማራው መንግስት፣ በተጨማሪም ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ ታዋቂ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን ይዞ አስሯል። 4 አመታት እስር ቤት ቆይተው በድጋሜ የተፈቱት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ም/ል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በድጋሜ ሲታሰሩ፣ ምክትል ዋና ጸሃፊው አቶ ደጀኔ ጣፋም እንዲሁ ታስረዋል።

No comments:

Post a Comment