Thursday, December 24, 2015

አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች የኦፌኮ መሪዎች ታሰሩ

ኢሳት (ታህሳስ 14 ፣ 2008)
የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ኦፌኮ ከፍተኛ አመራር አቶ በቀለ ገርባ ከሰዓታት በፊት በመንግስት ሃይሎች ታሰሩ። 21 ደህንነቶችና ታጣቂዎች አዳማ የሚገኘውን የአቶ በቀለ ገርባ መኖሪያ ቤት ለ 5 ሰዓታት ያህል ሲበረብሩና ሲፈትሹ እንደዋሉ ለማወቅ ተችሏል።
ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ ለአምስት ሰዓታት ከተካሄደው ፍተሻና ብርበራ በኋላ፣ 12 ሰዓት ላይ አቶ በቀለ ገርባ በመኪና ወደአዲስ አበባ ተወስደዋል ተብሏል።
የኦፌኮ ም/ፕሬዚደንት አቶ በቀለ ገርባ፣ የአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ዞኖችን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም ፓርቲያቸው በሚያደርገው እንቅስቃሴ ንቁ ተሳትፎ ከሚያደርጉ መሪዎች አንዱ እንደሆኑ ይታወቃል።
አቶ በቀለ ገርባ ቀደም ሲልም ለ4 ዓመታት ወህኒ ውስጥ መቆየታቸው ይታወሳል። በፖለቲካ ምክንያት ከነሃሴ 2003 ጀምሮ በወህኒ ቤት የነበሩት አቶ በቀለ ገርባ፣ ከእስር የተለቀቁት በቅርቡ በመጋቢት 2007 ዓም እንደነበር ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላንን በመቃወም የተገደሉ የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ 86 መድረሱ ሲገለጽ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ወህኒ ቤት መወሰዳቸውም መረዳት ተችሏል።
ሌላው የኦፌኮ አመራር አቶ ደጀኔ ጣፋ መታሰራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የኦፌኮ የወጣቶች ክፍል ምክትል ሃላፊ አቶ ጉርሜሳ አየናውም በፖሊስ ተይዘው መወሰዳቸው ታዉቋል። ከዚህም በተጨማሪ በሻሼማኔና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ቦታዎች የነበሩ የኦፌኮ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የዩንቨርስቲ መምህራ፣ በምርጫ 2007 የተሳተፉ የኦፌኮ አባላትና ታዛቢዎች ከየአካባቢያቸው ተለይተው እየታሰሩ መሆናቸውን ዶ/ር መረራ ጉዲና ለኢሳት ገልጸዋል።
ህዝቡን  በማሰር፣ በመግደል፣ እንዲሁም በማዋከብ አገር መምራት እንደማይቻል የጠቆሙት ዶ/ር መረራ፣ መንግስት የሰላማዊ ሰዎችን ሰብዓዊ መብት ከጣሰ በኋላ ተመልሶ ተቃዋሚዎችንና ህዝቡን የሚከስበት ድርጊት እንዳስገረማቸው ተናግረዋል።
ለምዕራብያውያን ፍጆታ ሲባል ዲሞክራሲ እንዳለ ለማስመሰል ህወሃት-ኢህአዴግ  የሄደበትን መንገድ ያመላከቱት ፕሮፌሰር መረራ፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት የምትገዛበት ጭቆናዊ አገዛዝ ከበፊቱ የተለየ አለመሆኑን አስረድተዋል።
መንግስት ሰላማዊ ሰዎችን በመግደል ምንም አይነት ለውጥ እንደማያመጣም ዶ/ር መረራ ለኢሳት ገልጸዋል።
ዶ/ር መረራ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያገባቸው የፖለቲካ ሃይሎች በሙሉ በመተባበር በአገራች ለውጥ እንዲመጣ ካልታገሉ፣ አሁን እንደሚደረገው አይነት የተናጠል ትግል የትም እንደማያደርስ ለኢትዮጵያ ህዝብ መልዕክት አስተላልፈዋል።

No comments:

Post a Comment