Friday, December 11, 2015

በኦሮምያ የሚካሄደው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው።

ታኀሳስ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምእራብ አርሲ ዞን ከሻሸመኔ በ60 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘዋ አዳባ ከተማ ከፍተኛ ተቃውሞ የተካሄደ ሲሆን፣ የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ አንድ ሰው በጥይት መመታቱ ታውቃል። የቀበሌ ጽህፈት ቤቱ እና የወረዳው የፍርድ ቤት መዝገብ ሙሉ በሙሉ በቃጠሎ ወድሟል።

ተመሳሳይ ተቃውሞ በነቀምትም በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ነዋሪዎች ወደ አምቦ የሚወስደው መንገድ በመዝጋት ተሽከርካሪዎች እንዳይተላለፉ አድርገዋል።

በአዋሳ ዩኒቨርስቲ የተደረገውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ተማሪዎች፣ በተለይም ጥቁር ለብሰው የተገኙ ተማሪዎች ተደብድበዋል። ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ተማሪዎችም ታስረዋል።
በወሊሶ ደም አፋሳሽ የሆነ ግጭት ከተካሄደ በሁዋላ የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ አባላት ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል። ሃሙስ በተደረገው ተቃውሞ ቁጥሩ እስከ 60 ሺ የሚገመት ህዝብ ለተቃውሞ እንደወጣ ተገምቷል። በተቃውሞው “ወኔ የሌለው ያገር ሸክም ነው “የወያኔ ኑሮ ይለያል ዘንድሮ ” “ዋይ ዋይ ተለያየን ” በማለት ህዝቡ መፈክር አሰምቷል። ፖሊስ የሃይል በወሰደው እርምጃ ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል ።4 ሰዎች እግራቸው ላይ በደረሰው የጥይት ጥቃት እግራቸው እንደሚቆረጥ እንደተነገራቸው ምንጮች ገልጸዋል።
በሉቃስ ሆስፒታል የገቡት ቁስለኞች ብዛት ከሆስፒታሉ አቅም በላይ በመሆኑ ሰራተኞች አዳሪ ሆነው እንዲሰሩ ታዘዋል። የከተማው ነዋሪ የደረሰበትን ጥቃት ተከትሎ በቅርብ የተገነቡትን የወሊሶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ህንፃንና የዞን አስተዳደር ህንፃ መስታዎቶችን አርግፏል። የ02 ቀበሌ ፅ/ቤት የተቃጠለ ሲሆን ኮምፒውተሮች ሰነዶች እና ሞተር ሳይክል አብረው ተቃጥለዋል። የዞኑ አስተዳዳሪ በነበሩት በአቶ ነጋ መኖሪያ ቤትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ዛሬ አርብ ደግሞ በግምት 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ጉሩራ በተባለች መንደር ባለስልጣኑ ስልጣኑን ተጠቅሞ የያዘውን ሰፊ ቦታ ቆርቆሮውን በሙሉ ነቅለው የጣሉ ሲሆን በይዞታው ላይ የነበረውን ቤት ሙሉ በሙሉ አቃጥለዋል።
አንድ የከተማው ነዋሪ ” ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ጦር ግንባር የዘመትኩ አይነት ሰሜት እስኪሰማኝ ድረስ ከተማዋ በወታደር ተወራለች አፈሳውና ዱላው ተጠናክሮ ቀጥሏል” ብሎአል።
በሆድሮጉድሩ ተቃውሞው ቀጥሎአል። የጂማ አዲስ አበባ መንገድም ተዘግቷል። በባኮ፣ ጌዶ፣ አምቦና ጊንጪም እንዲሁ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፖሊስ አባላት በአካባቢው ተሰማርተዋል።አሁን ዘገይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ በምእራብ አርሲ አሰሳ ከተማ ከፍተኛ ውጥረት አለ።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የወሰዱትን ከልክ ያለፈ እርምጃ የሚያወግዙ የተቃውሞ ሰልፎች በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እና በኔዘርላድስ ሄግ ተካሂደዋል። በጄኔቫ የተለያዩ አለማቀፍ ተቋማትን ማእከል ያደረገ ተቃውሞ መካሄዱን ለታ ባይሳ ገልጿል።
ዘሄግ የነበረው ተቃውሞ ደማቅ እንደነበር ጋዜጠኛ ደመቀ ነጋሳ ተናግሯል ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባን አዲሱን ማስተር ፕላን በመቃወም ኦፌኮ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቷል በዩንቨርሲቲ ተማሪዎች የተጀመረውና መላውን ኦሮሚያን ያናወጠው በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መስፋፋት ሰበብ አድርጎ የአርሶ አደሩን መሬት ለመቀራመት የታቀደውን የሕወሃት ሴራ በማውገዝ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ኦፌኮ በአዳማ ሕዝባዊ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ጠርቷል።
መነሻውን ከአዳማ መስቀል አደባባይ ያደረገውና ቅዳሜ ከጥዋቱ 3 ሰዓት በሚጀመረው ሰላማዊ ሰልፋ ላይ የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ፕሬዝዳንት ዶ/ር መረራ ጉዲናና አቶ በቀለ ገርባ በስፍራው እንደሚገኙ ድርጅቱ አስታውቋል።
በዚህ ወሳኝ ሰዓት የህወሓት መራሹ ቡድን ስልጣን ላይ ለመቆየት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የትኛውንም አይነት የሽብር ተግባር ተንኮል እና ጥቃት ከመፈፀም እንደማይቆጠብ ሰላማዊ ሰልፈኞች የፖለቲካ መሪዎች እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያኖች እንዲገነዘቡ ሲል ኦፌኮ ማስጠቀቂያ ሰጥቷል።
እየተካሄደ ያለው የመብት ፣ የነፃነት ፣ የፍትህ ፣ የእኩልነት ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተቀጣጥሎ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ህዝብ ዐይኑን እና ጣቱን ህወሓት ላይ በመቀሰር የጭቆና እና ባርነት እድሜውን በአንድነት ታግሎ ማሳጠር ይገባዋል።ሕዝቡ የጠላትን ደባ አውቆ በህወሓት ተልካሻ ፣ አሰልቺ እና ተደጋጋሚ ፕሮፖጋንዳ ተጠቂ እንዳይሆን ለመከላከል መሆኑንም ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።
በሌላ በኩል የመንግስት ባለስልጣናት ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ እና የህዝቡን ጥያቄ ሌላ አቅጣጫ እንዲይዝ ሙከራ እያደረጉ መሆኑን ከአስተማማኝ ምንጮች መረጃዎች ደርሰውናል።
ማስተር ፕላኑን በመቃወም ሰልፍ የወጡ የዩኒቨርሲቲ ታዳጊ ወጣት ተማሪዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ በአዲስ አበባ መነጋገሪያ መሆኑንም ዘጋቢያችን ገልጿል።
አንድ የአምቦ ተወላጅ መሆኑን የገለጸ አስተያየት ሰጪ ፣ማስተር ፕላኑ የኦሮሞን ሕዝብ በማፈናቀል ፤ለድህነት የሚዳርግ እንጂ ሕዝቡን የሚጠቅም አለመሆኑን ለመረዳት ባለፉት ዓመታት በኢንቨስትመንት መስፋፋት ስም የተፈናቀሉ ገበሬዎች የት እንዳሉ ማየት በቂ ምስክር ነው ብለዋል፡፡ ገበሬዎች ለዓመታት ከኖሩበትና መተዳደሪያቸው ከሆነ መሬት ላይ በ20 እና በ30 ሺ ብር በመፈናቀላቸው ዛሬ ብዙዎቹ ቤተሰባቸውን በትነው ለልመና መዳረጋቸው የአደባባይ ሐቅ ነው ይላሉ፡፡ እናም ከዚህ አንጻር ማስተር ፕላኑን መቃወማችን አግባብ ነው ሲሉ ያክላሉ፡፡
የኦሮሞ ወጣት እያለ ያለው ማስተር ፕላኑ« ገበሬዎቻችንን ያፈናቅላል፣ ሕገወጥ የመሬት ወረራንና ሙስናን ያስፋፋል ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ለምን አነሳህ ፣ዝም ብለህ ያልኩህን ልትሰማ ይገባል» በማለት እየተሰጠ ያለው የሃይል እርምጃ ሕዝባዊ አመጽንና እምቢተኝነትን ከማስፋፋት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ገዥው ፓርቲ አለመረዳቱ አሳዛኝ ነው ሲል ድርጊቱን ኮንኖታል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሰዎች ማስተር ፕላኑን በመቃወማቸው ብቻ ባዶ እጃቸውን አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች ላይ ቃታ መሳብ የለየለት አምባገነንት ነው፣ እንዲህ ኣይነት መንግስትም ለሕዝብ ጥቅም ያስባል ማለት አይቻልም ብሎአል።
አንድ የህግ ምሁር በበኩላቸው ” ዘንድሮ ሕገመንግስቱ የጸደቀበት 21 ኛ ዓመት ነው፡፡ ነገር ግን ሕገመንግስቱ ላይ አዲስአበባ «በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ መሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፣ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል» በሚል የሰፈረው ባለፉት 21 ኣመታት አለመከበሩን ጠቅሶ፣ ራሱ ያወጣውን ሕገመንግስት ማክበር የተሳነው መንግስት አሁን ደግሞ በማስተር ፕላን ሰም የኦሮሚያን መሬት ለመቀራመት የሚያደርገው ጥድፊያ በምንም መልኩ ተቀባይነት አይኖረውም” ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከተቀጣጠለው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ሰኣት በአዲስአበባ ትልቅ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ የሆነ ሲሆን መንግስት በውስጥ የተፈጠረበትን ቀውስ መፍታት ሲያቅተው ችግሩን ያቀጣጠሉት ኦነግና ግንቦት 7 ናቸው በማለት ለማላከክ ያደረገውን ጥረት አሳፋሪ ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ለ30 ኣመታት ሊተገበር ታቅዶ የነበረው የአዲስበባና በዙሪያዋ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ ማስተር ፕላን የኦሮሚያን 6 ከተሞች፣ 8 የገጠር ወረዳዎች ያካትታል፡፡
በሌላ በኩል በማስተር ፕላኑ ዙሪያ ተቃውሟቸውን የሚያሰሙ ተማሪወችና የኣካባቢው ኗሪዎች፣ሌሎችም ይህ ጉዳይ ያገባኛል ብለው በተነቃነቁ ዜጎችም ላይ በየጊዜው የሚደርስባቸውን ጭፍጨፋ አፈናና ግድያ የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፎረም በምዕራብ አውስትራሊያ አውግዟል።
በጎንደርና ኣካባቢዋ የተነሳውን ህዝባዊ ኣመጽ ለማፈን የሚደረገውን ወታደራዊ ዘመቻና፣ በተለይም በጸጥታና ምርመራ ሃይሎች የሚካሄደውን የጅምላና ህገ ወጥ ቅጣትን በማውገዝ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለለውጥ እንዲነሱ ጥሪ አቅርቧል።

No comments:

Post a Comment