Monday, December 21, 2015

የኦህዴድ ከፍተኛ ባለስልጣናት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ክልሉን ለቀው እንዲወጡ ጠየቁ

ታኀሳስ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአጋዚ ጦር በህዝቡ ላይ የወሰደውን እርምጃ በጽኑ አውግዘዋል። የኦሮሞ ህዝብ በአጋንንት ተመስሎ ተሰድቧልና ተሳዳቢው ባለስልጣን ይቅርታ ይጠይቅ ብለዋል።

መንግስት ለሞቱት ዜጎች ሃላፊነቱን እንዲወስድና ለህዝብ ጥያቄ መልስ እንዲሰጥ አሳስበዋል።በአዲስ አበባ የሚገነቡት ፎቆች የማን ናቸው? ሲሉም ጠይቀዋል።አርጅተናል አልቻልንም ስልጣናችንን እናስረክብ ያሉ አመራሮችም አሉ።

ሰፊ ሰአት በሚሸፍነው ስብሰባ የሚከተሉት ሃሳቦች ቀርበዋል።
የመጀመሪያው ባለስልጣን በአሁኑ ሰአት እየተደረገ ያለዉን በሁለት አቅጣጫዎች እመለከተዋለሁ” ይላሉ። አንደኛው ” የኦሮሚያ መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ለ3 ሳምንታት ያክል በነበረዉ ግጭት ህዝቡ ላይ ትልቅ ጉዳት አድርሰዋል። መቼስ ጆሮአችን እየሰማና አይናችን እያየ ስለሆነ ሰዎቹ ጉዳት የደረሰባቸው ለህዝብ ጥቅም በመጮሃቸው ነዉ። በአሁኑ ሰአት እየተደረገ ያለዉ ነገር ጥሩ አይደለም። ተማሪዎች የሚያደርጉት ተቃውሞ በ1997 ዓም የጀመረና እኛ ዩኒቨርሲቲ ጨርሰን ከወጣን በሁዋላም የቀጠለ ነዉ። የአሁኑን ተቃውሞ የተለዬ የሚያደርገዉ እየተቃወመ ያለዉ ተማሪው ብቻ አለመሆኑ ነው። አሁን እየተቃወመ ያለዉ ህዝቡ ነዉ። ጥያቄው የተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የህዝቡ ጥያቄ ሆኗል።”
ባለስልጣኑ ንግግራቸውን በመቀጠል ” መከላከያ ሰራዊት ህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለዉ በደል በጣም የሚያስቆጣና መንግስት ያለመኖሩን የሚያሳይ ነዉ። ኦህዴድ ኦሮምያን እያስተዳደረ ከሆነ እዉነትም ለሃገሩና ለህዝቡ የሚቆረቆር ከሆነ ፣ ህዝቡን እየጨፈጨፈ ያለዉን ሰራዊት ከክልሉ ያስወጣ። ቤቶችን አቃጥለዋል። ነዋሪዎችን ከቤታቸው እየጎተተ በማዉጣት በጥይት ገድለዋቸዋል። በመንግስት ሆስፒታሎች ዉስጥ በመግባት ሰራተኞችን እየደበደቡ ነው። እናት በልጆቿ ፊት በጥይት ተገድላለች፡፡ እንደዚህ አይነቱ ክስተት በሀገራችን የመጀመሪያ ነዉ። ከጣሪያ ላይ ዲሽ በማዉረድ omn ትከታተላላችሁ ተብሎ እየተሰባበረ ነው። ህዝቡ መረጃዎችን ከየት ያግኝ?” ብለዋል።
ተናጋሪው ንግግራቸውን ይቀጥላሉ “አምቦ ላይ ፣ወለጋና ሌሎች የኦሮሚያ አከባቢዎች ላይ እየተፈጸም ያለዉ በomn ስለተላለፈ ነዉ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም፤ በአይናችን እያየነዉ ያለነዉ ነዉ። በሚያስተዳድር አካልና በሚተዳደረዉ ህዝብ መካከል ትልቅ ችግር አለ፤ህዝቡ ላይ የደረሰበትን በደል መሪዉ ካላወቀ ህዝቡ የራሱ መንግስት አለዉ ለማለት ከባድ ነዉ። ሌላዉ አካል እንደፈለገ አፉን የሚከፍትበት ከሆነ ምን መንግስት አለ ይባላል?ህዝቡ ችግር ደርሶብናል በሚልበት ሰአት ጦሩን አስታጥቆ የሚያስጨጭፍ ከሆነ በአሁኑ ሰአት የኦሮምያ መንግስት ለህዝቡ ምን እያደረገ ነዉ ያለዉ?ህዝቡ የሚያደርገው ተቃዉሞ ትክክል ነዉ። የራሱ ሀብት እየተዘረፈበት ነዉ ። ይህን ጉዳይ ይሄ ትውልድ ካልተቃወመው ለሚመጣዉ ትውልድ ምን ጥሎለት ሊሄዲ ነዉ?” ይላሉ።
ባለስልጣኑ ንግግራቸውን በመቀጠል ” ስለራሳችን ክልልና ስለራሳችን ሀብት መከራከርና መቃወም ያለብን ባለቤቶቹ ነን። ዛሬ ችግር ተፈጠረ ብላችሁ ከምትሰበስቡን ችግሩ ከመነሳቱ በፊት ለምን አልሰበሰባችሁንም? ስለማያገባን ነዉ?የኦህዴድ ትልቁ ችግር የህዝቡን ጥያቄ ያዳምጣል እንጂ መልስ የሚሰጠዉ ሌላ አካል መሆኑ ነው። የእዉቀት ችግር ይሁን፣ የስልጣን ችግር ይሁን አይታወቅም። የሚያስተዳድረዉ አካል ያለበትን ችግር የማይዉቅ ከሆነ ፣ለህዝቡ ጥያቄ መልስ መስጠት እስካልቻለ ድራስ የኦሮሚያ ችግር ነገም ቢሆን የሚቀጥል ይሆናል። በአሁኑ ሰአት ትልቅ ችግር ገጥሞታል። ይህን ችግር መፍታት ካልቻለ ለምን ደክሞኛል ይህቺን አገር ማስተዳደር አልቻልኩም ብሎ ማስተዳደሩን አያቆምም? ” ብለዋል።
ሌላው ባለስልጣን ደግሞ እንዲህ ይላሉ ” ይሄ መንግስት መጀመሪያ ለማስተር ፕላኑ መልስ ከመስጠቱ በፊት ህይወታቸዉን እያጡ ላሉት ዜጎች መልስ መስጠት አለበት። ስለዚህ በአፋጣኝ የታጠቀዉ ሠራዊት ከአካባቢው ማዉጣት አለበት። ደሙ እየፈሰሰ ላለው ህዝብ መታሰብ አለበት። የኦህዴድ ተወካዮች ዛሬም እንደ ትናንቱ ስህተት እየሰሩ ነዉ ።ትናንትና ዋሽቶ ከነበረ ዛሬም ያንን እየደገመ ነዉ ያለዉ። ህዝባችን እያለቀብን ነዉ ያለዉ። ሌላዉ አካል የሚናገራዉ ሌላ፣ ኦህዴድ የሚናገረዉ ሌላ። ህዝቡን ከማታለል ያለዉን ነገር በግልጽ ለምን ተናግሮ ችግሮችን ለመፍታት አይሞክርም?።” ተናጋሪው ንግግራቸውን በመቀጠል “በአሁኑ ሰአት ኦህዴድ ላይ ትልቅ ጥርጣሬ አለኝ። ዛሬ እሱ እያለ ይህ ሁሉ ግፍ የሚፈፀም ከሆነ ነገ እንዴት አምነነዉ አብረን ልንሰራ እንችላለን?አሁን ስህተት ሰርቶ ከሆነ ስህተቱን ተናግሮ ህዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ፣ እልቂቱ ቁሞ የታጠቀዉ ሰራዊት ከአካባቢው ወጥቶ ሰላም መዉረድ አለበት። ” ብለዋል።
ቀጣዩ ተናጋሪ ደግሞ እኔ ብዙ ጥያቄዎች አሉኝ ይላሉ። “በአሁኑ ሰአት ኦሮምያን ማነው የሚያስተዳድራት?ከትላንትና በፊት በሚዲያ እንደሰማነዉ ከሆነ አጋንንቶችን ልክ እናስገባቸዋለን ተብሎአል። እኛ ምን ለማምጣት ነዉ እዚህ የምንሰበሰበዉ? ትልቅ ሀገር ትልቅ ህዝብ አጋንንት ከተባለ የኦህዴድ መኖር ምንዋጋ አለዉ?በዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ጥያቄ ሲያቀርቡ ለምን የዩኒቨርሲቲዉ ዳይሬክተር መልስ አልሰጣቸውም?የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም ጥያቄ ሲያቀርቡ ለምን መልስ አልተሰጣቸውም? ለምን የጥያቄዎቹ መልስ ጥይት ሆነ?ዲሞክራሲ ተብሎ ለምን ህዘቡ ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጣ በጥይት ይገደላል ? አንደኛዉን ለምን እንደ ደርግ አቋሙን ግልጽ አድርጎ አይገድልም?እኔ አሁንም ደግሜ ደጋግሜ መናገር የምፈልገዉ፦እዉነትም ለኦሮሞ ህዝብ ቁመናል የምትሉ ከሆነ፣ ህዝቡን እየጨረሰ ያለዉን ጦር በአስቸኳይ ከክልሉ አስወጡ። ህዝባችንን በሌላ አካል አታስጨርሱብን። ”
ቀጣዩ ተናጋሪ ባለስልጣን ደግሞ እንዲህ ይላሉ ” በአሁኑ ሰአት ገንፍሎ የወጣው የህዝብ ቁጣ እንደሚባለዉ ነው። ይህም የሆነው የመጨርሻ ደረጃ ላይ በመድረሱ ነዉ። ስራዉ ከመጀመሩ በፊት መንግስት ህዝቡን ማወያየት ነበረበት። ልማት ቢለማ ለህዝቡ ነዉ ፣የሚያለማዉም ህዝቡ ስለሆነ የህዝብ ፍቃደኝነት ያስፈልጋል። ’50 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ ምን ያመጣል? ልክ እናስገባቸዋለን፣ በግድም ቢሆን እናስፈጽመዋለን’ ብለውናል። ለህዝቡ እቆማለሁ የሚል ሰው እንዴት እንደዚህ ይላል ብሎ የጠየቀ አካል ባለመኖሩ በጣም ነዉ የሚያሳዝነዉ። ሌላዉ አካል እንደዚህ ሊናገረን የቻለዉ ኦህዴድ በከፈተለተ መንገድ በመጠቀሙ ነዉ።” የመከላከያ ሠራዊት የአገሩን ዳር ድንበር ያስከብራል እንጂ ህዝቡን አይጨርስም፣ ከየት እንደመጡ አናዉቅም፤ አማርኛ አይችሉ። ኦሮምኛ አይችሉ። ከሌላ ቦታ አማጥቶ ህዝባችንን እያስጨረሰ ስለሆነ ይህ ጉዳይ ቶሎ መቆም ይኖርበታል።” ብለዋል።
ሌላው ተናገሪ ደግሞ የመድረኩን አስፈላጊነት በማንሳት ንግግራቸውን ይቀጥላሉ ” መድረኩ በጣም አስፈላጊ ነዉ፣ ከቤቱ ብዙ ሀሳቦች ተነስተዋል። እኔ በተጨማሪነት የምስጠዉ ሀሳብ፣ ይህ ሁሉ ጥፋት የአመራራችን ዉጤት ነዉ። ህዝባችን የሚያነሳዉ ጥያቄ ትክክለኛና የመብት ጥያቄ ነዉ። አሁን ብዙ ሰዉ ተገድሏል።ህዝባችን ለምን በመከላከያ ሰራዊትና በፌዴራል ፖሊሲ ይጨፈጨፋል?በጋምቤላ በተከበረዉ የብሄር ብሄረሰቦች በአል ላይ ተግኝቼ ነበር። በወቅቱ የሱዳን ፕሬዝዳንት ይገኛሉ ተብሎ ነበር። እሳቸዉ የሚመጡት ከጎንደር ተቆርሶ ለሱዳን ለሚሰጠዉ ለም መሬት የስምምነት ፊርማ ለመፈርም ነው ተብሎ
ተነግሮን ነበር። ይህ ጉዳይ በጣም አሳዝኖኛል። ምክንያቱም ስለሚመለከተኝ ነዉ።የክልላችን ጉዳያ ደግሞ በበለጠ ይመለከተኛል። ኦሮሚያ የኛ ናት። እንደ አንድ ኦሮሞ ያገባኛል። በማስተር ፕላኑ ምክንያት የተነሳዉ የህዝብ ተቃዉሞ ከተጀመረ 1 ወር ሊሞላ ነዉ ። የጭለሞ ጫካ ተቃጥሏል፤ብዙ ጥፋቶችና ዉድመቶች እየተፈጸሙ ነዉ። ይህን መንግስት በአፋጣኝ ሊያቆመዉ ይችል ነበር ” ሲሉ ገልጸዋል።
ሌላ ተናገሪ ደግሞ ይቀጥላሉ ” የዚህ ችግር መንስዔ የኦህዴድ የማስፈጸም አቅም ማጣት ነዉ ።ኦህዴድ የህዝባችንን ክብር ለማስጠበቅ አልቻለም ። እኛም እንደ ኦህዴድ አመራሮች ተዋርደናል። ህዝባችንንም አዋርደናል። በግለሰቦች ደረጃ ህዝባችንን እያሰደብን ነዉ።ወደዳችሁም ጠላችሁም ትፈጽማላችሁ እየተባልን ነዉ። በዲሞክራሲ ትተዳደራለች በሚባል አገር ዉስጥ ግለሰቦች ህዝባችንንና እኛን እያዋረዱን ነዉ። ስለልማት ማዉራት በአሁኑ ሰአት ምንም ዋጋ የለዉም። ማውራት ያለብን ስለሰዉ ልጅ ክብር ነዉ ።በአጋዚና በፌዴራል ፖሊስ ህጻን ሽማግሌ ሳይባል እየተጨፈጨፈ ነዉ፡፡ 50 ሚሊዮን የኦሮሞ ህዝብ ስለተዋረደ ነዉ ይህ ሁሉ ችግር ሊመጣ የቻለዉ። በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉት ባለ 12 እና 20 ፎቆች የማን ናቸዉ?የኦሮሞ ህዝብ በመሬቱና በሃብቱ ላይ የበይ ተመልካች ሆኗል።የእነዚህ ሁሉ ድርጅቶች ዋርዲያ የኦሮሞ ልጅ ነዉ። እሱ ዘበኛ የሚሆነዉ ባለቤቶቹ ከዉጭ እስከሚመጡ ድረስ ነዉ። ሲመጡ ይባረራል።የኦሮሚያን መሬት ዘርፎ የተልፈሰፍሱ የኦህዴድ አመራሮች እያሉ የሚሰድቡን እነሱ እነማን ናቸዉ? ይሉና ” ይህን ችግር ለማስቆም ከተፈለገ opdo እንደ ድርጅት እራሱን ማስከበር ያኖርበታል፤ በመንግስት ሚዲያዎቶች ህዝባችንን የሰደበዉግለሰብም በግልጽ ይቅርታ መጠየቅ አለበት” ሲሉ አጠቃለዋል።
ቀጣዩ ተናጋሪ ባለስልጣን ደግሞ እንዲህ ይላል ” እኔ opdo ወይም ኢህአዴግ አገሪቷን ሲቆጣጠር የ6ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩኝ ። ከዛ ጀምሮ ዩኒቨርሲቲ ጨርሼ እስክወጣ ድረስ ኦሮሞ በመሆናችን ስንደበደብ፣ ስንታሰር፣ ስንገደል እና ከቤታችን ስንባረር ነበር። ያን ሁሉ ሲያስፈጽም የነበረዉ ኦህዴድ ነዉ። ስለዚህ አሁን የምንወያየዉ ኦህዴድ ምን ለዉጥ ያመጣል ብለን ነዉ?አቅም ካለዉ አሁኑኑ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት ከክልላችን ይዉጣ ። የማስተር ፕላኑ እቅድ ይሰረዝ። ለሞቱትና ለተጎዱት ቤተሰብ ካሳ ይከፈል”
ሌላው የኦህዴድ አባል ደግሞ ” ይሄ ችግር በማስተር ፕላኑ ሳይሆን በኦሮሚያ መንግስት ላይ ባለ ንቀት የመጣ ነዉ። ኦሮሚያ የሚተዳደረዉ በክልሉ ሳይሆን በፌዴራል መንግስት ነዉ። ለዚህም ነዉ ህጻናትንና ሽማግሌዎችን በአደባባይ የሚጨፈጨፉት።ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ ይላል አማራ፣ ኦህዴድም ተንቋል” በማለት ተናግረዋል።
ቀጣዩ ተናጋሪ ባለስልጣን ደግሞ ” አሁን እዚህ ኦህዴድን ወክለን የምንወያየዉ ምን ልናመጣ ነዉ ? በ25 አመታት ጉዞዋችን ለህዝባችን ያመጣነዉ ሀዘንና መከራ ብቻ ነዉ። ስለዚህ አሁን የምንሰራዉ ነገር ያስጨንቀኛል። ይህን ሁሉ መከራ 40 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝባችን መሸከም ስላቃተው የመጣ ነው ” ብለዋል። ሌሎችም በርካታ ተናጋሪዎች ተመሳሳይ አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን፣ አንደኛው ባለስልጣን ”
አሁንም የህዝቡን ጥያቄ ለማፈን ብለን ሌላ ጥፋት እየፈጸም ነዉ፤ እሱም በ50 ብር የቀን አበል ሰዎችን እያታለልን ነው። የሴቶች ሊግ፣ የወጣቶች ሊግ እየተባለ የሚደረገዉ ዉይይት ተጨማሪ ጥፋት ነውና በአስቸኳይ ይቁም” ብለዋል።
ሙሉ ትርጉሙ እንደደረሰን በልዩ ዝግጅት እንደምንለቀው ለመግለጽ እንወዳለን።

No comments:

Post a Comment