Monday, January 4, 2016

በዲላ ዩንቨርስቲ በተከሰተው ግድያ የተነሳ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው መውጣታቸው ተገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 25 ፣ 2008)
ባለፈው ሐሙስና ቅዳሜ ጠዋት በዲላ ዩንቨርስቲ በእጅ በተወረወረ ቦምብ ጥቃትና በስለት ተወግተው 4 ተማሪዎች መሞታቸውን ከዲላ የአይን እማኞች ለኢሳት ተናግረዋል። ከተጎጂዎቹ ውስጥ በቦምብ ጥቃት የሞቱት በተለምዶ “ሰመራ” ተብሎ በሚጠራው ካምፓስ የሚኖሩ ሁለት ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ሌሎች ከ10 የማያንሱ ተማሪዎች ደግሞ በቦምብ ፍንዳታውና በጩቤ ተጎድተው በዲላ ሬፈራል ሆስፒታል ህክምና እያገኙ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በተጨማሪውም ባለፈው ቅዳሜ ጠዋት ሶስት ተማሪዎች በስለት መጸዳጃ ቤት ውስጥ ታርደው መገደላቸውን በግቢው ውስጥ የነበሩ እማኞች ገልጸዋል። ጥቃቱን የሰነዘረው አካል  ማን እንደሆን እስካሁን ያልታወቀ ቢሆንም፣ ድርጊቱ ምን አልባትም በመንግስት ካድሬዎች የብሄር ግጭት ለማስነሳት ሆን ተብሎ ሳይፈጸም እንዳልቀረ ተገምቷል።
አርብ ማታና ቅዳሜ ጠዋት በተፈጸሙት በእነዚህ ዘግናኝ ድርጊቶች የተደናገጡት ተማሪዎች፣ እጅግ በመረበሻቸው የዩንቨርስቲውን ግቢ ለቀው ወጥተዋል ሲሉ የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
መንግስት በበኩሉ ከቦንብ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ ተማሪዎችን ጨምሮ ብዛት ያላቸው ሰዎችን እንዳሰረ ታውቋል። ለቦንብ ፍንዳታው ሃላፊነትን የወሰደ ሰው፣ድርጅት፣ ወይም አካል ባይኖርም፣ ድርጊቱን የፈጸሙት በመንግስት ትዕዛዝ የተሰጣቸው ካድሬዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ በብዙ ፖለቲካ ተንታኞች ተገምቷል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ የእጅ ቦምብ ተወርውሮ ቢያንስ 24 ሰዎች እንዳቆሰለ ኣይዘነጋም። ከዚህ በተጨማሪም በሆሮጉድሩ በትምህርት ቤት ቦምብ ተወርውሮ ተማሪዎችን እንደጎዳ ከዚህ እሳት መዘገቡ ይታወሳል። ሆኖም የመንግስት አካላት ጉዳዩን እናጣራለን ከማለት ውጭ እስካሁን የምርመራ ሂደቱን ለህዝብ አላሳወቁም።
ከዚህ በፊት የአሜሪካ ኤምባሲ ባስተላለፋቸው መረጃዎችና በዊኪሊክስ ለህዝብ በተሰራጩ ዘገባዎች መሰረት፣ የህወሃት መንግስት ህዝብን በጅምላ የሚጨርስ የፈንጅና ቦንብ ማፈንዳት ድርጊት ላይ ተሰማርቶ እንደነበር መጋለጡ ይታወሳል። የዛሬ 4 ዓመት የወጣው ዘገባ እንደሚያስረዳው እኤአ በ2006 በአዲስ አበባ የደረሱትን ሶስት የቦምብ ጥቃቶች ያደረሰው የኢትዮጵያ መንግስት እንደሆነ ገልጾ፣ የህወሃት መንግስት የኤርትራን መንግስትና የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን ተጠያቂ ለማድረግ ህዝቡን እንደፈጀ ተገልጿል።
አብዛኞቹ የዲላ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ዛሬ ሰኞ ጓዛቸውን ጠቅልለው ከግቢ እንደወጡ ቢታወቅም፣ የመንግስት ጸጥታ ሃይሎች ግን ተማሪዎች ወደአገራቸው እንዳይሳፈሩ ሲከላከሉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። የተወሰኑ ተማሪዎችም ወደአዋሳ በመሄድ ወደቤተሰቦቻቸው ለመሄድ ትራስፖር አጥተው ተቸግረው እንደሚገኙ ኢሳት ያነጋገራቸው ተማሪዎች ገልጸዋል። በሰመራ ግቢ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት ሙሉ በሙሉ የተቋረጠ ቢሆንም፣ የፌደራል ፖሊስ ግን ተማሪዎቹ ወደ ዩንቨርስቲ ግቢ ተመልሰው እንዲገቡ እያስገደዳቸው እንደነበር የአይን እማኞች ከስፍራው ዘግበዋል።
ለአንድነት የሚቆም መንግስትና ወገን በሌለበት ግቢ ውስጥ መቆየቱ እጅግ አስፈሪ ነው ያሉት ተማሪዎች በበኩላቸው፣ “ሰሞኑን 4 ተማሪዎች ሞተዋል፣ ነገ ተረኞቹ እኛ ላለመሆናቸን ምን ማረጋገጫ አለን?” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። አሁን ያላቸው አማራጭ ወደቤተሰቦቻቸው በመሄድ በሰላም መኖር እንደሆነ ተማሪዎቹ ለኢሳት ተናግረዋል።
“በትምህርት ተቋም ውስጥ ቦምብ እንዴት ሊፈነዳ ይችላል? ቦምብስ ሊኖረው የሚችለው ማነው? ሁኔታው እጅግ በጣም አስጊ በመሆኑ በዚህ ሁኔታ በግቢው ውስጥ መቆየት የሚሆን ነገር አይደለም” ስትል አንድ ስሟ እንዳይገለጽ የፈለገች ተማሪ ስጋቷን አክላ ገልጻለች።  ይህች ተማሪ፣ የመንግስት ሃይሎች“ራሳቸው ቦንቡን እንደማያፈነዱት ምን ማረጋገጫ አለ?” በማለት የህወሃት መንግስት በሽብርተኝነት ሊጠየቅ እንደሚገባ ገልጻለች።
ከቀናት በፊት በዩንቨርስቲዉ ላይ ከደረሰዉ የእጅ ቦንብ ፍንዳታ በተጨማሪም በቅጥር ግቢዉ አንድ ማደሪያ ህንጻ ላይ የደረሰ የእሳት ቃጠሎ አለመረጋጋት ማስፈኑን እና የትምህርት ሒደቱ እንዲቋረጥ ማድረጉ ታዉቋል።
የዩንቨርስቲዉ ተማሪዎች ሰኞ ሙሉ ለሙሉ ከግቢዉ ለቀዉ መዉጣታቸዉንም ከሀገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የመንግስት ባለስልጣናት በአደጋዉ ሁለት ተማሪዎች መሞታቸዉን ቢያረጋግጡም አደጋዉ እንዴት እና በማን አካል እንደተፈጸመ ምርመራ እየተካሄደ ነዉ ሲሉ ምላሽ መስጠታቸዉን ሮይተርስ ዘግቧል።
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀስዉ ተቃዉሞ ቀጥሎ እንደሚገኝም ከሀገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል። ሰኞ ከሰአት በኋላም በአዳማ ዩንቨርስቲ ተቃዉሞ ተቀስቅሶ የፀጥታ ሀይሎች እርምጃ መዉሰዳቸዉ ተመልከቷል። ይሁንና በዩኒቨርስቲዉ ተማርዎች ላይ የደረሰን ጉዳት ለማወቅ የተደረገ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
የፀጥታ ሀይሎች እየወሰዱ ያለዉ የሀይል እርምጃና እስራት ተቃዉሞዉ በአዲስ መልክ እንዲያገረሽ ማድረጉን እማኞች አስረድተዋል።
ተቃዉሞዉ ሰኞ እለት ከአዳማ ባሻገር በምስራቅና ምእራብ ሐረርጌ እንዲሁም በምእራብ ወለጋ መቀጠሉን ታዉቋል። በምስራቅ ሐረርጌ በቆቦና በዶዶር ስርአቱን በመቃወም አደባባይ ሲዉጡ፣ በምእራብ ሐረርጌ ሒረና እና በምእራብ ወለጋ ሻቶቢ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተቃዉሞዉ ቀጥሏል።

No comments:

Post a Comment