Friday, January 29, 2016

የመሬት መንቀጥቀጥ ሸሽተው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲሄዱ የነበሩ የሃዋሳ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች የመኪና አደጋ ደረሰባቸው

ጥር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሃዋሳ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ለአስራ አምስት ቀናት ትምህርት መቋረጡን የዩንቨርሲቲው አስተዳደር መግለጹን ተከትሎ ግቢውን ለቀው ወጥተዋል። በአንድ ተሽከርካሪ ላይ ተጭነው ከግቢው በመውጣት ወደ ወላጆቻቸው በመሄድ ላይ ከነበሩት ተማሪዎች ውስጥ ወደ በመቂ እና ሞጆ ከተሞች መዳረሻ አካባቢ የመኪና አደጋ ደርሶባቸዋል። የአደጋው መንስኤ የሚጓዙበት ተሽከርካሪ ከአዲስ አበባ ወደ ሀዋሳ ሲጓዝ ከነበረ ኤፍ ኤስ አር አይሱዙ የጭነት መኪና ጋር በመጋጨቱ ምክንያት አምስት ተማሪዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸውን ማጣቸውን ዘ ኢትዮጵያነር ድረገጽ በምስል አስደግፎ ጉዳተኞችን አውጥቷል።
በሃዋሳ የደረሰውን ርዕደ መሬት ሸሽተው ሲሄዱ የመኪና የሞት አደጋ ከደረሰባቸው ተማሪዎች በተጨማሪ ከፍተኛና ዝቅተኛ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል።
በሃዋሳ ከተማ በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ በተደጋጋሚ ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል። የመሬት መንቀጥቀጡ በተለይ በሃዋሳ መምህራን ኮሌጅ ተማሪዎች ላይ የተወሰነ አካላዊ ጉዳት አስከትሏል። በመንግስት በኩል ስለ አደጋውና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምንም ዓይነት መግለጫ አለመሰጠቱ በተማሪዎቹና በወላጆቻቸው ላይ ከፍተኛ ስነልቦናዊ ጫና ፈጥሯል።
በተጨማሪም በአዋሳ ያሉ የሱቅ በረንዳቸው የፈረሰባቸውን ነጋዴዎችን ንብርት የክልሉ ፖሊስ በመኪና በመጫን ዝርፊያ ፈጽሟል። ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው ነጋዴዎች አቤቱታቸውን ሰሚ አካል አላገኙም። የዓይን እማኞች ከስፍራው እንዳስታወቁት ፌስታል አዙረው እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩ ወጣትና ታዳጊ የጎዳና ላይ ነጋዴዎችንም ጭምር ፖሊስ የያዙት በመቀማት ድብደባ በመፈጸም ላይ ነው።

No comments:

Post a Comment