Monday, January 18, 2016

የአማራ ክልል ነዋሪዎች የተለያዩ ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው

ጥር ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በህብረተሰቡ ውስጥ የሚነሱ ቅሬታዎች ዘርፈ ብዙ ናቸው።

በምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር ደምበጫ፣ ቡሬ ዙሪያ፣ ጃቢጠህናን እና ወምበርማ ወረዳዎች የቀበሌ አመራር የሆኑ የኢህአዴግ አባላት በወል ግጦሽ መሬት ወረራ ላይ በስፋት እየተሳተፉ ነው። በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ደግሞ የመሬት ችግር መፍትሄ የሚሰጠው አካል አልተገኘም፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን በመሃል ሳይንት ወረዳ ደግሞ ለማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ተብሎ የነዋሪዎች ቦታዎች ተወስደዋል፤ አትክልቶቻቸው ተጨፍጭፈውባቸዋል። ከ70 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መሬታችን ሲወሰድና ንብረታችን ሲወድም ካሳ አልተከፈለንም የሚል ደብደባ ቢጽፉም መልስ አላገኙም።

በዚሁ ዞን ደላንታ ወረዳ ከፍተኛ የሆነ የመብራት ችግር በመኖሩ ባንክ ቤት፣ ዳቦ ቤቶች፣ ወፍጮ ቤቶች ስራቸውን ለመስራት እንዳልቻሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።
በዋግ ኸምራ ዞን አበርገሌ ወረዳ ከፍተኛ የውሃ እጥረት በመከሰቱ መንግስት ውሃ ያቅርብልን ካልሆነም ወደ ተከዜ ወስዶ ያስፍረን የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። በደቡብ ጎንደር ዞን ታችጋይንት ወረዳ ከፍተኛ የውሀ ችግር ተከስቷል።
በሰሜን ወሎ ዞን በራያ ቆቦ ወረዳ ወደ መቀሌ የሚዘልቀው የባቡር መንገድ የቁፋሮ ስራ ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ እየተሰራ በመሆኑ ለመስኖና ለመጠጥ ውሃ አገልግሎት የሚውል ካናል ዘግቶ ለከፍተኛ የውሃ ችግር ዳርጎናል ሲሉ ነዋሪዎች ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል። በዚሁ ዞን አስተዳደር መቄት፣ ራያ ቆቦ፣ ዋድላ፣ ወልዲያና ጉባላፍቶ ወረዳዎች የጤፍ ዋጋ በኪሎ ከ23 ብር በላይ ወይም በኩንታል ከ2300 በላይ በመናሩ ህዝቡ ምሬቱን እየገለጸ ነው፡፡
ደቡብ ወሎ ዞን በኩታበር ወረዳ የበርበሬ ዋጋ ከ250 -270 ደርሷል። በደሴ ከተማ አስተዳደርም የዳቦ ዱቄት በመጥፋጡና የዳቦ እጥረት ተከስቷል። የዳቦ ዋጋም መጠኑ ቀንሷል። በዚህ ሳምንት በሰቆጣ ከተማ የተለያዩ ጥራጥሬዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ ባቄላ በጣሳ 37 ብር፣ ጤፍ በጣሳ 36 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት በኪሎ 80 ብር፣ ማሽላ በጣሳ 18 ብር እየተሸጠ ነው።
በደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ ወረዳ፣ በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ፣ በኦሮሚያ ዞን ባቲ ከተማ ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር ሜጫ፣ ቡሬ ዙሪያና ቋሪት ወረዳዎች ከፍተኛ የሆነ የስኳርና ዘይት እጥረት ተከስቷል።
በሌላ በኩል ከድርቅ ጋር በተያያዘ በምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ በድርቅ የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ሲጠና 4000 ሆኖ ሳለ 1000 ነው የሚል መረጃ ስለተሰጠ ለችግር ተዳርገናል በማለት ድርቅ የተከሰተባቸው የቀበሌ ነዋሪዎች ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል፡፡ በሰሜን ወሎ ዞን ግዳንና ላስታ ወረዳዎች ደግሞ ምንም አይነት ሰብል እንዳላመረትን እየታወቀ፣ የምግብ እህል እርዳታ አልተደረገልንም፣ በአመላመል ሂደቱ ላይም ሰፊ የሆነ አድልዎ እየተፈፀመ በመሆኑ ለችግር ተዳርገናል ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
በአዊ ብሄረሰብ በጃዊ ወረዳ ለስኳር ልማት ስራ ቦታቸውን እንዲለቁ የተጠየቁ ሰዎች ካሳ አልተሰጠንም የሚል ቅሬታ እያቀረቡ ነው። በደቡብ ጐንደር ዞን አስተዳደር እስቴ ወረዳ በአለማያ ቀበሌ ውስጥ አርሶ አደሮች መሬታችን ለኢንቨስትመንት ተሰጥቶብናል በማለት ጥያቄ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው አላገኙም።
በሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ በባቡር መንገድ ግንባታ ምክንያት የእርሻና የግጦሽ መሬት የተወሰደባቸው ከ30 በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ለመሬቱ የተሰጠን የካሣ ክፍያ መሬቱ ከሚያስገኘው ጥቅም ጋር ተመጣጣኝ አይደለም በሚል ቅሬታ ያነሱ ቢሆንም ለቅሬታው መልስ የሚሰጣቸው አላገኙም። በኦሮም ዞን በባቲ ከተማ የሁሉቆ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደሮች መንግሥት ለተደራጁት ግለሰቦች የቤት መስሪያ መሬታችንን በመስጠቱ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል።
በደዋ ጫፋ ወረዳ በባቡር ሀዲድ መስመር ዝርጋታ ምክንያት የካሳ ክፍያ ባለመፈፀሙ 14 አባወራዎች ጥያቄ እያቀረቡ ነው። በሰሜን ወሎ ዞን በራያ ቆቦ ወረዳ 022 ቀበሌም ቁጥራቸው 25 የሚደርሱ አርሶ አደሮች የእርሻ መሬታቸውን ይኸው መንገድ ነክቶባቸው እያለ ካሳ ለመቀበል የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር አቅርቡ በመባላቸውና እስካሁን የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ያልተሰጣቸው መሆኑን እየተቃወሙ ነው ።

No comments:

Post a Comment