Tuesday, January 5, 2016

77 ኢትዮጵያዊያዊያን ስደተኞች በዛንቢያ ተያዙ

ታኀሳስ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የዛንቢያ የስደተኞች ጉዳይ ከፓሊስ ጋር በመተባበር በሕገወጥ መንገድ ወደ አገራችን ገብተዋል ያላቸውን ቁጥራቸው 77 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን በዋና ከተማዋ ሉሳካ ካባንግዌይ አቅራቢያ በቁጥጥር ስራ ማዋሉን አስታውቋል።
በአንድ ቶዮታ ሬጉስ መኪና ላይ ተጭነው ሲጓዙ የነበሩ 10 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ለመያዝ አሰሳ ሲያደርጉ በስፍራው ሌሎች ተጨማሪ 67 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ከተደበቁበት መያዛቸውን ገልፀዋል።
ከተያዙ ውስጥ 19 የሚሆኑት ሕጋዊ የመግቢያ ቪዛ የሌለው የኢትዮጵያ ፓስፖርት መያዛቸውንና የተቀሩት ምንም ዓይነት ማንነታቸውን የሚገልጽ ዶክመንት አለመያዛቸውን ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል።
የስደተኞች ጉዳይ ቃል አቀባይ የሆኑት ናማቲ ኒሽንካ የመኪናው አሽከርካሪ ዛምቢያዊ ሾፌር ሳይያዝ ማምለጡንና የተያዙት 77 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በሉሳካ ማእከላዊ እስርቤት ውስጥ ሆነው የፍርድ ሂደታቸውን እንደሚጠባበቁ ኦል አፍሪካ ዘግቧል።
በተጨማሪም በኬኒያ ሕገወጥ ስደተኞችን ቤት ከቤት ማሳደዱ መቀጠሉንና በኢዞሎ ግዛት አንድ ኢትዮጵያዊና ሶስት ቱርካዊ ዜጎች በአሰሳ መያዛቸው ታውቋል። ባለፉት ወራቶች ብቻ በኬንያ ታንዛኒያ ድንበር አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ሲሞክሩ የተያዙት ኢትዮጵያዊያን ቁጥራቸው ከ90 እንደሚበልጥ የናይሮቢ ፖሊስ አዛዥ ጃፖቴ ኮሜን ጠቅሶ ሲቲዝን ዲጅታል ዘግቧል።
ገዥው መንግስት ባለ ሁለት አሃዝ ምጣኔ ሃብታዊ ለውጥ አምጥቻለው እያለ በአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ቢናገርም፣ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በተለይ ወጣቶች በ አገራቸው የነፃነት የስራ ዋስትና ስላጡ ስደትን እንደ አማራጭ ለመውሰድ ተገደዋል።

No comments:

Post a Comment