Tuesday, January 12, 2016

በጅማ ዩኒቨርስቲ ቦንብ ሲፈነዳ በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ደግሞ ተማሪዎች ተደብደቡ

ጥር ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ተማሪዎች እንደገለጹት ፣ ትናንት ምሽት ላይ መብራት ከጠፋ በሁዋላ የእጅ ቦንብ የተወረወረ ሲሆን፣ ፍንዳታውን ተከትሎ የመንግስት ታጣቂዎች ወደ ተማሪዎች ማደሪያ ክፍል እየገቡ ደብድበዋቸዋል። በፍንዳታው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ተማሪዎቹ ፍንዳታውን ያደረሱት ወታደሮች ናቸው ይላሉ። ፍንዳታው ተቃውሞ ሊያሰሙ ይችላሉ በሚሉዋቸው ተማሪዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሆን ብሎ የተቀናበረ መሆኑን የሚያሳየው ከፍንዳታው በፊት መብራት መጥፋቱና ከመቅጽበት ተሰልፈው ይጠባበቁ የነበሩ ወታደሮች በተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመራቸው ነው ይላሉ። ከክፍላችን እየደበደቡ ያስወጡን ወታደሮች፣ እየተቀባበሉ ደበደቡን ሲል አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ተማሪ ተናግሯል።
በዩኒቨርስቲው ወይም በመንግስት በኩል ፍንዳታውን ተከትሎ የተሰጠ መግለጫ የለም። ውጥረቱ አሁንም እንዳለ መሆኑን የሚገልጹት ተማሪዎች፣ የመማር ማስተማሩ ሂደት ተቋርጧል።
በሃሮማያ ዩኒቨርስቲና አካባቢዋ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እና ህዝቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያካሂዱ ውለዋል። ይህንን ተከትሎ ከፍተኛ ተኩስ ይሰማ እንደነበር አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ መምህር ገልጿል። መምህሩ እንዳለው ወደ ዩኒቨርስቲው መግቢያ በር ላይ ደም ፈሶ ይታያል።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት መሰማራቱን የገለጸው መምህሩ፣ ወታደሮች በህዝቡ ላይ ሲተኩሱ መመልከቱን ገልጿል። አካባቢው የጦር ቀጠና ይመስላል ያለው መምህሩ፣ መምህራንና ሰራተኞች አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን አክሏል።
ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ ወታደሮቹ ወደ ተማሪዎች ክፍል በመግባት ከፍተኛ ድብደባ ፈጽመዋል። ትናንት በነበረው ተቃውሞ ደግሞ 2 ተማሪዎች መሞታቸውን የክልሉ ወኪላችን ገልጿል።
ከሳምንት በፊት በዩኒቨርስቲው ተደርጎ በነበረው ስብሰባ ላይ ” ኦፒዲዮ የራሱ ሳንባ የለውም፣ የሚተነፍሰው በህወሃት ሳንባ ነው” ብሎ የተናገረው መምህር ታሪኩ ታስሯል።
በሌላ በኩል የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ጉዳይ አቋሙን ይፋ እንዲያደርግ ተጠይቋል። ታዋቂው የሰብአዊ መብት ድርጅት ሂውማን ራይትስ ወች ባወጣው መግለጫ፣ የህብረቱ ባለስልጣናት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን በሚያነጋግሩበት ወቅት ፣ ለተቃውሞ በሚወጡ ኢትዮጵያውያን ላይ የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱትን እርምጃ በተመለከተ ግልጽ መልእክት ሊያስተላልፉላቸው ይገባል ብሎአል።
“የአውሮፓ ህብረት ዝምታውን በመስበር የጸጥታ ሃይሎች በኦሮሞ ተቃዋሚዎች ላይ የሚወስዱትን እርምጃ ሊያወግዝ ይገባል” ያሉት ፣ በሂውማን ራይተስ ወች የአውሮፓ የአድቮኬሲ ዳይሬክተር ሎቲ ሌይክት፣ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ እርድታ የሚሰጠው ህብረቱ፣ ተቃዋሚዎች ለሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች መንግስት በጠመንጃ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በንግግር እንዲፈታ ግፊት እንዲያርጉ ጠይቀዋል።

No comments:

Post a Comment