Tuesday, January 19, 2016

የአዲስ አበባ መስተዳድር ማስተር ፕላኑን በግሉ ለመተግበር አቅም የለውም ተባለ

ጥር ፲ (አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከ150 ላላነሱ ሰዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በኦህአዴድ በኩል ተቀባይነት እንደሌለው መገለጡን ተከትሎ የአዲስ አበባ መስተዳድር በአስተዳደር ክልሉ ስር በሚገኙ ቦታዎች ላይ እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ቢጀመርም፣ እንቅስቃሴው ከእልህና ከግራ መጋባት የመጣ በመሆኑ ውጤታማ አይሆንም ሲሉ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ።
ከመጀመሪያው ጀምሮ በእቅዱ የተለያዩ ደረጃዎች የተሳተፉ ምንጮች እንደሚሉት፣ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እቅድ ዋና አላማ፣ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ለመጣው ቤት ፈላጊ ህዝብ የመኖሪያ ቤቶች መስሪያ ቦታ መፈለግ፣ ለዲያስፖራው መኖሪያ ቤት መገንቢያ እንዲሁም፣ የተለያዩ የዘመኑ ባለሃብቶች ለሚያቀርቡት የቦታ ጥያቄ መልስ መስጠት ነበር። በአዲስ አበባ ያለው ባዶ ቦታ፣ ከቦታ ፈላጊው ህዝብ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ነው የሚሉት ምንጮች ፣ መስተዳድሩ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን በግዛቱ ስር በማድረግ ፣ የመሬት ጥያቄዎችን ለመመለስ ያወጣው እቅድ፣የኦሮምያ ክልል እቅዱን ሊቀበለው ባለመቻሉ ሊሳካለት አይችልም። ሰፋፊ ቦታዎችን ከኦሮምያ ክልል እስካልወሰደ ድረስ ለሚቀርብለት የቦታ ጥያቄ መልስ ለመስጠት አየችልም፣ ከዚህ አንጻር ሲታይ ማስተር ፕላኑን በራሴ እተገብረዋለሁ ማለት ህልም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
መስተዳድሩ ሁለት አማራጮች እንዳሉት የሚገልጹት ምንጮች፣ አንደኛው አማራጭ በተለያዩ ባለሃብቶች በተለይም በሼክ አላሙዲንና በህወሃት ከበርቴዎች ያለግንባታ ታጥረው የተቀመጡትን ቦታዎች መልሶ በመውሰድ ለአጭር ጊዜም ቢሆን፣ የቦታ እጥረቱን ለመቅረፍ መሞከር፣ ካልሆነም ደግሞ ” ከእንግዲህ በአዲስ አበባ የሚሰጥ ቦታ የለም” ብሎ ማስታወቅና ዜጎች ሌላ አማራጭ እንዲፍለጉ ማድረግ ነው ይላሉ። ሁለቱም አማራጮች ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ዋጋ የሚያስከፍሉ በመሆኑ መንግስት ደፍሮ እዚህ ውሳኔ ላይ ላይደርስ እንደሚችል የሚገልጹት ምንጮች፣ ምናልባትም በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን በልዩ ሁኔታ በፌደራል መንግስት ስር እንዲተዳደሩ በማድረግ መሬት የመሸጡን ሂደት ሊቀጥሉበት ይችላሉ ተብሎ ቢታሰብም፣ በቅርቡ ከታየው ተቃውሞ አንጻር ይህም አማራጭ ለጊዜው ዝግ ነው ብለዋል።
የማስተር ፕላኑ መቅረት ቤት እየገነቡ በመሸጥ ሊገኝ የታሰበውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማድረቁንም እነዚሁ ወገኖች ይገልጻሉ። በኦሮምያ የታየው ተቃውሞ ከፖለቲካዊ ተጽእኖው ይልቅ ኢኮኖሚያዊው ተጽእኖው ይበልጣል የሚሉት ወገኖች፣ የኦሮምያ ክልል በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አርሶአደሮች እንደማይፈናቀሉ ዋስትና ከሰጠ ደግሞ ችግሩ ይባባሳል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በምእራብ ሃረርጌ በመኢሶ እንዲሁም በወለጋ ነቀምት፣ ዛሬም ተቃውሞ ተካሂዷል። በተለይ የመኢሶ ተቃውሞ ደም አፋሳሽ መሆኑን ከአካባቢው የተላኩ መረጃዎች ያሳያሉ።
በኦሮምያ የተካሄደው ተቃውሞ የተለያዩ የአለም ሚዲያዎችን ትኩረት ስቧል። መንግስት ተቃውሞውን ለመጨፍለቅ የሚሄድበት መንገድ ሰላምና አለመረጋጋቱን እያባባሰው እንደሚሄድ የተለያዩ ጸሃፊዎች እያሳሰቡ ነው።

No comments:

Post a Comment