Wednesday, January 13, 2016

ኦህዴድ ማስተር ፕላኑን ትቼዋለሁ ቢልም ተቃውሞ ግን ቀጥሎአል

ጥር ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢህአዴግ አንድ ክንፍ የሆነው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አዲሱን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መተውን ባስታወቀ ማግስት በአምቦ፣ በአርሶ ኬፈሌና በሌሎችም የኦሮምያ ክፍሎች ተቃውሞው ቀጥሎአል።
በአምቦ የተካሄደው ተቃውሞ ደም አፋሳሽ የነበረ ሲሆን፣ አንድ ሰው መገደሉና በርካቶች መቁሰላቸው ታውቋል። ከቆሰሉት መካከል ህጻናትም ይገኙበታል።
ከአምቦ ከተማ በተጨማሪ በ ጃርሶ ወረዳ ቀሬ ጎሓ ከተማ ፣ በበደኖ፣ አርሲ፣ ሆድሮ ጉድሩና ሌሎችም ከተሞች ተቃውሞዎች ተካሂደዋል።
በሌላ በኩል ኦህዴድ ያወጣውን መግለጫ የኦፌኮው ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና አጣጥለውታል። ኦህዴድ ክልሉን የመምራት የሞራል ብቃት ስለሌለው ስልጣኑን ለህዝብ ያስረክብ ብለዋል።
ዶ/ር መረራ ፣ ዋናው ጥያቄ ” አዲስ አበባ ለምን ሰፋ አልሰፋ ሳይሆን፣ ለወደፊቱ አርሶደአሩ እንዳይፈናቀል ምን ዋስትና አለው” የሚለውን መመለሱ ላይ በመሆኑ፣ መግለጫው ይህንን ጥያቄ የሚመልስ አይደለም ይላሉ
በኦህዴድ የተሰጠው መግለጫ ተቃውሞውን ያስቆመዋል ወይ ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር መረራ አይመስለኝም የሚል መልስ ሰጥተዋል። “ህዝቡ ይህ ድርጅት ወይም ያ ድርጅት ስለመራው ሳይሆን በራሱ ጊዜ ነው የተነሳው የሚሉት ዶ/ር መረራ፣ ጥያቄው ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር የተያያዘ መሆኑን፣ ዛሬ እንኳን ቢበርድ ነገ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment