Thursday, January 28, 2016

በአፍሪካ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተባባሰ መምጣቱ ተገለጸ

ጥር ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ተከትሎ አጠቃላይ በአሃጉሩ የሸቀጥ ዋጋ እየናረ ነው። የአፍሪካ ሕብረት የኤኮኖሚ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አንቶኒ ሞንታይ እንዳሉት የሸቀጦች ዋጋ መውረድ፣ የዶላር የወለድ መጠን በአሜሪካ መናር፣ አሳሳቢ ድርቅና የጎርፍ አደጋዎች በሃጉሪቱ ያለውን ምጣኔሃብታዊና ማኅበራዊ ችግሮች ይበልጥ አባብሰውታል ።
ዶ/ር አንቶኒ “ችግሩ በመባባሱ ምክንያት የስራ አጡ ቁጥር እየጨመረ፣ የኑሮ ልዩነት እየሰፋ፣ ጤናማ ያልሆነ የንግድ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ፣ የዋጋ ግሽበት እያስከተለ ነው ” ብለዋል
ወደ ውጪ የሚላኩ የኤክስፖርት ምርቶች በማሽቆልቆላቸው ምክንያት ትርፍ ባለመኖሩ የሃጉሪቱ ገቢ ቀንስዋል። ድርጅቶችም ሰራተኞችን በመቀነሳቸው የስራ አጡ ቁጥር አሻቅቧል። የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ በከፍተኛ ሁኔታ በማደጉ በሃጉሪቱ ኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሯል።
የኤሊኖ አየር መዛባትን ተከትሎ በተለያዩ የአፍሪካ አገራትይ ውስጥ በአገር ውስጥና ወደ ውጪ በሚላኩ የግብርና ምርቶች ላይ አስከፊ የሆነ ተፅዕኖ ፈጥሯል።በሃይድሮ ኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ረገድም በድርቁ ሰበብ ውሃ በወንዞችና በግድቦች ውስጥ ባለመኖሩ የኃይል አቅርቦቱ ተስተጋጉሏል።ይህም በማዕድን ማምረቻዎች፣ፋብሪካዎች በመስኖ እርሻዎችና በንጹህ ውሃ አቅርቦት ላይ የከፋ አደጋ እንዲደርስ ማድረጉን የአፍሪካ ሕብረት ተሰብሳቢዎች አስተውቀዋል።

No comments:

Post a Comment