Wednesday, January 27, 2016

በኮንሶ የሚታየው ውጥረት እንደቀጠለ ነው

ጥር ፲፰ (አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኮንሶ ህዝብ ራሱን ችሎ በዞን እንዲተዳደር ያቀረበው ጥያቄ ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ በርካታ ሰዎች ለእስር ከተዳረጉ በሁዋላ አሁንም አካባቢው በልዩ ሃይል ፖሊሶች እንደተከበበ መሆኑን ነዋሪዎች ከስፍራው ገልጸዋል። የልዩ ሃይል አባላት ከጥያቄው ጀርባ አርበኞች ግንቦት7ቶች አሉበት በማለት ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎች፣ አሁን ደግሞ ” ጥያቄው የእኛ አይደለም” ብላችሁ ፈርሙ በማለት በግድ ለማስፈረም ሙከራ እያደረጉ ነው። የልዩ ሃይል አባላትና የወረዳው ሹሞች መግባባት አለመቻላቸውን፣ አስተዳዳሪዎቹ ጥያቄው የህዝብ ነው የሚል አቋም በማራመዳቸው አንዳንዶች ከሃላፊነት እንዲነሱ ተደርጓል።
የህዝቡን ጥያቄ አቅጣጫ ለማስለወጥ ሆን ብለው በማቀነባበር ቡርጂዎች ግጭት እንዲቀሰቀስ ለማድርግ የተሞከረ ቢሆንም፣ በሁለቱም ወገን የሚገኙ ነዋሪዎች ይህ ሆን ተብሎ ግጭት ለመፍጠር የተቀነባበረ ነው በማለት ወደ ግጭት አለመግባቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ከቡርጅና ከኮንሶ የሆኑ 2 ሰዎች መገደላቸውን፣ ግድያው የተፈጸመው ሆን ተብሎ ግጭት ለመቀስቀስ ታስቦ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል፤ ግድያውን የልዩ ሃይሎች እንዳቀነባበሩት ሲታወቅ ግን ህዝቡ ወደ ግጭት አለመግባቱን ነዋሪዎች አክለው ተናግረዋል።
የኮንሶ አገር ሽማግሌዎች ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያምን ለማነጋገር ወደ አዲስ አበባ መሄዳቸውና ለዛሬ ቀጠሮ ተይዞላቸው እንደነበር ቢታወቅም፣ ስለተሰጣቸው ምላሽ ይህን ዜና እስካቀናበርንበት ሰአት ድረስ ለማወቅ አልቻልም።
በአካባቢው አሁንም ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉ ነው። አንዳንድ የመንግስት መስሪያቤቶችም አገልግሎት መስጠት አቁመዋል።

No comments:

Post a Comment