Tuesday, January 12, 2016

በአርባምንጭ ከተማ ወጣቶች በወያኔ ሃይሎች በገፍ እየታደኑ በመታሰር ላይ ናቸው ተባለ

በአርባምንጭ ከተማ ብዙ ወጣቶች የግንቦት 7 አባል ናችሁ በሚል ሰበብ ተጠርጥረው ዕርቃናቸውን ግርፋትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸሙባቸው ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ። 20 አመት እድሜ ላይ የሚገኙ ዮሴፍ ይስሃቅና፣ እንዳሻው ወንድይፍራው ከዚህ በፊት በአርባምንጭ ከተማ ከጓደኞቻቸው ጋር ሲዝናኑ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ እያንዳንዳቸው በ2ሺ ብር ዋስትና እንደተለቀቁ፣ “ወያኔን ሰድበዋል፣ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ግንኙነት አላቸው” በሚል ሰበብ እንደተደበደቡ በስፍራው የነበሩ እማኞች አስታውቀዋል።
ከታሰሩት 7 ወጣቶች 5ቱን ከለቀቁም በሁዋላ፣ ዮሴፍ ይስሃቅና እንዳሻው ወንድይፍራውን መልሰው እንዳሰሯቸው ተነግሯል። ወጣቶቹ አሁን ለሶስተኛ ጊዜ ከታሰሩ በኋላ ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለው ግርፋት እንደተፈጸመባቸው ታውቋል። ከሁለት ሳምንት በፊትም በዚሁ አርባምንጭ ከተማ ሌሎች ብዙ ወጣቶች ታፍሰው እንደታሰሩና ድብደባ ከተፈጸመባቸው የተወሰኑት እንደተለቀቁ የመንግስትን ብቀላ በመፍራት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ እማኞች ከአርባምንጭ ለኢሳት ተናግረዋል። ወጣቶች ዮሴፍ ይስሃቅና፣ እንዳሻው ወንድይፍራው ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ ታስረው የተፈቱ ቢሆንም፣ ለሶስተኛ ጊዘ ከታሰሩ በኋላ ወደአዋሳ ተወስደዋል ከሚል ወሬ ውጭ ያሉበት ቦታ አይታወቅም ተብሏል። “ፖሊሶች ወጣቶቹን ራቁታቸውን ወደከተማ ይዘዋቸው እንደወጡ፣ አዋሳ እንደደረሱና ከዚያ በኋላ ወዴት እንደተወሰዱ የታወቀ ነገር የለም” ሲሉ እኚሁ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት ሰው ለኢሳት ገልጸዋል። ሁለቱ ወጣቶች ወደአዲስ አበባ ቃሊቲ ተወስደው ሊሆኑ እንደሚችል የኢሳት ምንጮች ገምተዋል። በዚሁ አርባ ምንጭ አካባቢ አርበኞች ግንቦት 7 አባላት በሆኑ ልጆቻቸው ሳቢያ ወላጆችና ዘመዶቻቸው ላይ ከዚህ በፊትም በመንግስት ካድሬዎች ከፍተኛ ችግርና መከራ ይደርስ እንደነበር ኢሳት ዘግቦ እንደነበር ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment