Friday, January 8, 2016

ኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች ያነሱት የመብት ጥያቄ ተገቢ ነው፣ የትጥቅ ትግል የጀመሩትን መደገፍ አለብን ሲሉ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ አስታወቁ

ኢሳት (ታህሳስ 29 ፣ 2008)
የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች ያነሱት የመብት ጥያቄ ተገቢና የሚግደገፍ ነው ሲሉ ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ምሁር ገለጹ። በከተሞች መስፋት ሃብታም የመሆን እድል የልተመቻቸለት አርሶ አደሮች ወደ ድህነት እየተገፉ፣ ባለጊዜ በዕርሱ መሬት እንዲበለጽግ መንገድ ሲጠርግ ተቃውሞ መጀመራቸው ትክክል ነው ያሉት ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ፣ ይህ በኦሮሞዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ላይ ሊደርስ የሚችል በመሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊያወግዙት እንደሚገባ ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም አካባቢ ችግሮች መኖራቸውን የጠቀሱት ታዋቂው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ፣ መፍትሄውም የጋራ እንደሆነ ለፖለቲካ ሃይሎች በአንድነትና በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ብዙ ብሄረሰቦችና ሁለት ትልልቅ ሃይማኖች ባሉበት ሃገር መቻቻልና መከባበር እንዲሁም ለጋራ ችግር በጋራ መቆም ያስፈልጋል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። ግባችን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሆንና መስዋዕትነቱ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሆን እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።
ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ከእንግዲህ በምርጫም ሆነ በሰላማዊ ትግል ስልጣን ይለቃል የሚል ዕምነት የለኝም ያሉት ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ፣ የትጥቅ ትግል ለማድረግ የተነሱትንና የጀመሩትን መደገፍ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። የትጥቅ ትግል ብለው የሚንቀሳቀሱ የምናውቃቸው ስለኢትዮጵያ ሲሉ የተነሱ ናቸው ሲሉም አክለው ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment