Monday, January 11, 2016

የወልቃይትን ህዝብ ለማሳመን የተላከው ቡድን እስካሁን አልተሳካለትም

ጥር ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ያለፍለጎታቸውን ወደ ትግራይ ክልል በመጠቃለላችን ወደ አማራ ክልል እንዛወር በማለት የጠየቁ የወልቃይት ነዋሪዎችን ሲያግባባ የነበረው ከአማራ ክልል ከልዩ ልዩ መስሪያ ቤቶች የተወጣጣው ቡድን ለአንድ ወር ያክል ጊዜ በአካባቢው ተሰማርቶ የማሳመን ስራ ለመስራት ቢሞክርም እስካሁን ተልዕኮው ባለመሳካቱ ለተጨማሪ ጊዜ በወልቃይት ለመክረም ተገዷል፡፡

የክልሉ ጸጥታ ጉዳዮች፣ ፍትህ፣ፖሊስና መከላከያን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ተሿሚዎችን ያካተተው ቡድን ከአንድ ወር በላይ በወልቃይት የከረመ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ልዩ መመሪያ በየቀኑ እየተጠሰጠው መሆኑን የውስጥ አዋቂዎች ተናግረዋል፡፡
‹‹ነገሮች እስከሚረጋጉ ድረስ በትግራይ ክልል ስር ቆዩ ›› የተባሉት የወልቃይት ነዋሪዎች እንደሚሉት ‹‹አማርኛ እንናገራለን ፣አረብኛም እንናገራለን ፣ትግርኛም ሆነ ሌሎችን የሃገራችን ቋንቋዎች ብንናገርም ትግረኛ ስለምትችሉ ወደ ትግራይ ክልል ትጠቃለላላችሁ የተባልነውን አንቀበልም፡፡ወደ ክልላችን መልሱን ›› በማለት አጥብቀው ሲሟገቱ ተሰምተዋል፡፡
የአማራ ክልል አመራሮችና ተሿሚዎች ‹‹ወደ ክልላችን እንቀላቀል ›› ያሉትን የወልቃይት ነዋሪዎች ‹‹ እባካችሁ ወደ ትግራይ ክልል ሂዱ ፡፡›› በማለት ለረዥም ጊዜ ልመና ማቅረባቸው በጣም እንዳሳዘናቸው ጉዳዩን የሚከታተሉ ምንጮች ገልጸዋል።
የክልሉ አመራሮች ሙሉ በሙሉ ለህውሃት ታማኝነታቸውን ለማሳየት የወልቃትን ህዝብ ተንበርክከው መለመናቸው እና በማስፈራራት ሃሳባቸውን ለማስቀየር የሚያደርጉት አካሄድ እጅጉን እንዳስገረማቸውና እንዳሳፈራቸው እነዚሁ ምንጮች ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment