Friday, January 15, 2016

ሂውማን ራይትስ ወች “መንግስት የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን መሰረዙ ለተቃዋሚዎች ትልቅ ድል ቢሆንም ውሳኔው ዘግይቷል” አለ


ጥር ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሂውማን ራይትስ ወቹ ፍሊክስ ሆርን ፣ ደም አፋሳሽ ከሆነው የ9 ወራት ተቃውሞ በሁዋላ መንግስት ተቃዋሚዎች ላቀረቡት ጥያቄ ፣ የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በመሰረዝ መልስ ቢሰጥም፣ ኦሮምያን ለማረጋጋት ግን የዘገየ ውሳኔ ነው ብሎአል።
መንግስት ተቃዋሚዎች ላቀረቡት ጥያቄ መልስ መስጠቱ ያልተለመደ ነው የሚለው ሆርን፣ ለተቃዋሚዎች ደግሞ ትልቅ ድል ነው መሆኑን ገልጿል።
በመጀመሪያ ተቃውሞው ስለ አዲስ አበባ መስፋፋት ነበር፣ይሁን እንጅ መንግስት ዜጎችን በስፋት ሲያስር፣ ሲገድልና ሌሎችን ጭካኔ የተሞላባቸው እርምጃዎች ሲወስድ፣ ተቃውሞው ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አልፎ ሌሎችም ጥያቄዎች ማካተቱን ገልጸዋል።ምንም እንኳ የተወሰኑ ግጭቶች ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ ተቃውሞዎች ሰላማዊ ናቸው።መንግስት ጭካኔ የተሞባለት እርምጃ መውሰዱ ተቃዋሚዎቹ ታሪካዊ ብሶቶችን ሁሉ እንዲያነሱ እንዳደረጋቸው ሆርን ገልጸዋል።
ምንም እንኳ መንግስት ማስተር ፕላኑን መተውን ቢያስታውቅም ፣ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ግን አልቀየረም። በእየለቱ ሰዎችን መግደልና ማሰሩ፣ በተለይም በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ ቀጥሎአል።
ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች መንግስት እቅዱን ይሰርዘዋል የሚል እምነት የላቸውም። ነገር ግን እቅዱ ኖረ አልኖረ መንግስት፣ፖሊሲውን እስካልለወጠ ድረስ አርሶአደሮቹን ማፈናቀሉን አያቆምም። መንግስት የአካባቢውን ሰዎች እንደ ልማት አጋር አድረጎ በመውሰድ ካላማከረ፣ የመሬት ባለቤትነታቸውን መብት ካልጠበቀና ጸረ ልማት የሚለውን አመለካከቱን ካልቀየረ እንዲህ አይነት ተቃውሞዎች ሊቀጥል እንደሚችል ሆርን በጽፋቻው አመልክተዋል።
መንግስት ለጊዜው ሁኔታውን ለማረጋጋት ከፈለገ የታሰሩትን በአስቸኳይ መልቀቅ አለበት የሚሉት ሆርን፣ የሚታመን አጣሪ ኮሚቴ በማቋቋም የደረሰውን አደጋ መመርመር አለበት። በኦሮሞ ህዝብ ላይ እስከዛሬ የደረሰውን የመብት ጥሰት በመመርምር መልስ መስጠት እንዳለበትም ሆርን አስታውሰዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ዩኒቨርሲቲዎችን ዒላማ ያደረጉ የቦምብ ፍንዳታዎች በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች መካሄዳቸው በመንግስት የተቀነባበሩ ናቸው የሚለውን ጥርጣሬ እያጎላው መጥቷል።
በሚያዚያ 2006 ዓ.ም የማስተር ፕላኑን ዕቅድ በመቃወም በ11 በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲዎች ተቃውሞ ተቀስቀሶ ከ20 በላይ ተማሪዎች እንደሞቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ በወቅቱ በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ እግርኳስ በቴሌቪዥን እየተመለከቱ በነበሩ ተማሪዎች ላይ የተወረወረ ቦምብ ፈንደቶ አንድ ተማሪ ወዲያውኑ ሲሞት 70 ያህል ተማሪዎችን ቆስለው ነበር።
በቅርቡ በዲላ ዩኒቨርሲቲ በተከሰተ የቦምብ ፍንዳታ ሁለት ተማሪዎች ሲሞቱ ስድስት ያህሉ መቁሰላቸው የሚታወስ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታ በያዝነው ወር መጀመሪያ በጂማ ዩኒቨርሲቲ ምሽት ላይ በተወረወረ ቦምብ ከ30 ያላነሱ ተማሪዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሷል።
መንግስት ሁሉንም ፍንዳታዎች ጸረ ሰላም ሃይሎች አደረሱት የሚል ተደጋጋሚ መግለጫ ቢሰጥም ፣እስከዛሬ አንድም ሰው አለመያዙ ጥቃቱ በመንግስት የደህንነት ሃይሎች የተቀነባበረ ሳይሆን አይቀርም የሚለውን የብዙዎች ግምት አጠናክሮታል።
ተቃውሞ በበረታባቸው ዩኒቨርሲዎች እንዲህ ኣይነት ጥቃት በመንግስት ሃይሎች ከተሰነዘረ በሃላ እንደገና ራሱ መንግስት ሰላምና መረጋጋት አምጪ ሆኖ በመቅረብ ተማሪዎች በፍርሃት ዝም እንዲሉ የሚጠቀምበት ስልት ነው የሚል
ግምት እንዳላቸው ዘጋቢያችን የተማሪዎችን አስተያየት አሰባስቦ የላከው ዘገባ ያመለክታል።
በኦሮምያ የሚካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ በምስራቅ ሃረርጌ በበደኖና በአንዳንድ አካባቢዎች ዛሬም ቀጥሎ ውሎአል። በበደኖ በነበረው የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ተማሪዎች ተቃውሞ፣ በርካታ ተማሪዎች በፖሊሶች ተደብድበዋል። ከ30 በላይ ተማሪዎች መታሰራቸውን አንድ የአይን እማኝ ገልጿል።

No comments:

Post a Comment