Wednesday, January 27, 2016

ባለፈው አመት በምስራቅ አፍሪካ ጭቆናው ተባብሶ መቀጠሉን ሂውማን ራይትስ ወች ገለጸ

ጥር ፲፰ (አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ታዋቂው የሰአብዊ መብት ድርጅት ባወጣው ዘገባ የምስራቅ አፍሪካ መንግስታት የሰብአዊ መብት አያያዞችን ለማሻሻል ያደረጉት ጥረት አነስተኛ መሆኑንና በአንዳንድ አገሮች ተባብሶ የቀጠለበት ሁኔታ እንደነበር ገልጿል።
ኢትዮጵያ እና ቡሩንዲ በተወሰነ መጠን ደግሞ ዩጋንዳ ሃሳብን በማፈን፣ የሰዎችን የመሰብሰብ ነጻነት በመንፈግ እንዲሁም ከምርጫ በፊትና በሁዋላ በሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ቀዳሚዎች ሆነዋል።
ሩዋንዳ የተቃውሞ ሃሳቦች እንዳይስተናገዱ የያዘችውን አቋም የቀጠለችበት ሲሆን፣ ኬንያ ደግሞ የጸጥታ ሃይሎች ለሚፈጽሙት ወንጀል ተገቢውን እርምጃ መውሰድ አልቻለችም።በደቡብ ሱዳንም የሰአብዊ መብት ጥሰቱ እንደአዲስ ቀጥሎአል።
በፈንጆች አቆጣጠር በ2015 በቡሩንዲ የታየው የፖለቲካና ሰብአዊ ቀውስ የአመቱ ከፍተኛ ቀውስ መሆኑን የጠቀሱት በሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ዳይሬክተር ዳንኤል በቀለ፣ ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳና ኬንያም መሰረታዊ በሚባሉት የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ መሻሻል አለማሳየታቸውን ገልጸዋል። በምስራቅ አፍሪካ ምርጫና ጸረ ሽብር ትግል የሚሉት ጉዳዮች በፖለቲካና ሰብአዊ መብቶች ላይ ተጽኖ የሚያደርጉ ጉዳዮች መሆናቸውን የድርጀቱ ዳይሬክትር ኬንዝ ሮዝ በሪፖርቱ መግቢያ ላይ ገልጸዋል።
ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ የምስራቅ አፍሪካ መሪዎች ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የሚፈጽሙትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዲያቆሙ፣ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ድርጅቶችና ሚዲያውን በመውቀስ ከተጠያቂነት ለመሸስ ከመሞከር ይልቅ የጸጥታ ሃይሎቻቸው ለሚፈጽሙት ህገወጥ ግድያዎች ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ለፍርድ እንዲያቀርቡዋቸው ጠይቀዋል።

No comments:

Post a Comment