Monday, January 11, 2016

በኦሮምያ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ህዝባዊ ተቃውሞውን ግንባር ቀድም ሆነው እየመሩት ነው

ጥር ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከወር በላይ ያስቆጠረው በኦሮምያ የሚካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ እንደገና በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ሃይሉን ጨምሮ ሲካሄድ ሰንብቷል። መንግስት ከፍተኛ ሰራዊት በማሰማራትና ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ በመውሰድ ተቃውሞውን ለማብረድ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም በክልሉ የሚገኙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በሚጫወቱት የመሪነት ሚና ተቃውሞ አድማሱን አስፍቶ ቀጥሎአል።በጀማ፣አሮማያ፣ መዳወላቡ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች በክልሉ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ከማወገዛቸውም በላይ፣ ተቃውሞውን ተከትሎ የታሰሩት ዜጎች እንዲፈቱ፣ የጸጥታ ሃይሎች ክልሉን ለቀው እንዲወጡ እንዲሁም ጥያቄያቸው እንዲመለስላቸው ጠይቀዋል።

ተቃውሞአቸውን ተከትሎ ተማሪዎች ተደብድበዋል፣ ቁጥራቸው በውል ያልተወቀ ተማሪዎችም ታስረዋል። በተመሳሳይ መንገድ በምእራብ ሃረርጌ በዋጩ ከተማም ህዝባዊ ተቃውሞው ሲካሄድ ውሎአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መድረክ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በክልሉ ህዝብ ላይ እየፈጸሙ ያለውን ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ አውግዝው፣ መንግስት ግድያውን በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠይቀዋል።
መድረክ በአቋም መግለጫው የሕዝቡ ሰላማዊ ጥያቄዎች በሚነሱባቸው አከባቢዎች ጥያቄዎቹን በኃይል ለማፈን ተሰማርቶ የሚገኘው የጸጥታ ኃይል እየፈጸማቸው የሚገኙት የግድያ፣ የእስራትና የማንገላታት እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ ሕዝቡን ቀስቅሳችኋል በሚል ሰበብ ለእስራት የተዳረጉት የኦፌኮ/መድረክ አባላትና በሰላማዊ ትግሉ በመሳተፉቸው ምክንያት ለእስራት የተዳረጉት ዜጎች በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ በሰላማዊ የመብት ጥያቄ በመሳተፋቸው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ወገኖች ቤተሰቦች ተገቢው ካሳ በመንግሥት እንዲከፈላቸው፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የግድያና የማንገላታት ተግባራትን የፈጸሙ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ፣ እንዲሁም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መንግሥት ከኦፌኮ/ መድረክና ከሌሎችም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ካለአንዳች ቅድመ ሁኔታ በመወያየትና በመደራደር ለሕዝቡ ፍትሀዊና ሕጋዊ ጥያቄ በአስቸኳይ ሕገመንግሥታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቋል።
አቶ በቀለ ገርባ ፣ የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር፣ -አቶ በቀለ ነጋ የኦፌኮ ዋና ጸሐፊና የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፤(በቁም አሥር ላይ የሚገኙ)፣ አቶ ደጀነ ጣፋ የኦፌኮ ም/ዋና ጸሐፊ፣ አቶ ደስታ ድንቃ የመድረክና የኦፌኮ የወጣቶች ሊግ ሊቀመንበርና የኦፌኮ የኦዲት ኮሚቴ አባል፣ አቶ ጉርሜሳ አያኖ የኦፌኮ የወጣቶች ሊግ ም/ሊቀመንበርና የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴ አባል፣ አቶ አዲሱ ቡላላ የኦፌኮ ወጣቶች ሊግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ ደረጀ መርጋ የኦፌኮ የወጣቶች ሊግ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ አቶ ዓለሙ አብዲሳ የኦፌኮ ወጣቶች ሊግ ዋና ጸሐፊ፣ አቶ ጣሕር የኦፌኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንዲሁም አቶ እስማኤል በኢሉባቦር ዞን የዳርሞ ወረዳ የኦፌኮ ተጠሪ እና ሌሎችም በርካታ የኦፌኮ/መድረክ አባላት መታሰራቸውን፣ እና በመቶዎች የሚቆጠሩትም መገደላቸውን መድረክ በመግለጫው ጠቅሷል።

No comments:

Post a Comment