Friday, January 15, 2016

“ያለንበት ዘመን ጨለማና መከራ የበዛበት ነው”ሲሉ አርሶአደሮች ተናገሩ

ጥር ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ በድርቁ በተጎዱ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመዘዋወር ተጎጂዎችን ለተመለከቱት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ያለባቸውን ችግር የተናገሩት አርሶአደሮች ‹‹ አሁን ያለንበት ዘመን አስከፊ የሆነ አሰቸጋሪ ጊዜ ነው ፡፡››በማለት እየደረሰባቸው ያለውን የውሃ ችግር በምሬት ቢናገሩም እስካሁን ምንም መፍትሄ እንዳልተሰጠ ተጊጂዎች ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ የደረሰብን ድርቅ ታይቶ የማይታወቅ እጅግ አሳዛኝ ነው ›› ያሉት ተጎጂዎች ዛሬ የደረሰብን ድርቅ አያቶቻችንም ‘እንዲህ አይነት ቀን አይተን አናውቅም !’ያሉት ዘመን ላይ ነው የደረስነው፡፡ ›› በማለት ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
ከመኖ እጥረት ጋር ተያይዞ እንስሳቶች በሞት አደጋ ሲሆኑ ነዋሪውም በመሰደድ ላይ መሆናቸውን እና ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በደረሰው ተደጋጋሚ ችግር እንስሶች እንኳን ስጋቸው ሊበላ ቆዳቸው ተገፎ የማይጠቅምበት ሁኔታ ላይ ነው ሲሉ ያሉበትን ዘመን አሳዛኝነት ገልጸዋል፡፡
በድርቁ ሰለባ ከሆኑት መካከል ሌላው ተጎጂ አርሶአደር ሲናገሩ ‹‹አሁን ያጋጠመን የተፈጥሮ ብትር አያት ቅድመ አያቶቻችን ተመተውበት የማያውቁበት ነው፡፡ውሃ እየጠጡ መራብ የነበረ ነው፡፡ከብት ውኃ እየጠጣ ገለባ ካለበት አካባቢ ተገዝቶ እየመጣ አብልቶ በመሸጥ ለቀጣዩ ዓመት ወረት ይሆነን ነበር፡፡ ለሚመጣው መልካም ዘመን ይተርፈን ነበር፡፡›› ካሉ በኋላ ‹‹በዚህ ዓመት ከብቱ ለገበያ የሚደርስበት ሁኔታ የለም ፣ መንግስትም እየሰራ ያለው ለራሱ፣ለልጆቹና ለወገኖቹ በሚመች መልኩ ሲመራ ቆየ እንጅ እንደኛ ያለውን አካባቢ አላየም፡፡›› በማለት በአካባቢያቸው የመሰረተልማት ባለመሟላቱ ከድርቁ እልቂት የተረፉትን ከብቶች ገበያ ለማድረስ እስከ አምስት ቀናት እንደሚፈጅባቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹አሁን ዘመኑና ወራቱ እንደኔም ሆነ እንደሌላው አርሶአደር ጨለማ ነው፡፡ጥገግ ነው፡፡›› በማለት በከባድ የመከራ ጊዜ ላይ እንዳሉ በመግለጽ ‹‹መስራት የማይደክመን ሰለቸን የማንል ብርቱ ገበሬዎች ብንሆንም በውሃ ጥም ተንቃቅተን እንሰሳውና ሰው አለቀ፡፡ ኢትዮጵያዊነታችን ሳይታወቅ መሞት የለብንም፡፡›› በማለት በምሬት ተናግረዋል፡፡
‹‹እኛ ካላመረትን መንግስት የት ያመጣዋል? ለምኖነው! ›› የሚሉት ተጎጂ አርሶአደሮች በርካታ ነዋሪዎች ውኃ በማጣት መሰደዳቸውን በመናገር መንግስት እንዲታደጋቸው የልመና ቃል አሰምተዋል፡፡
የገዥው መንግስት አመራሮች የችግሩን ጥልቀት ቢመለከቱም የችግሩን ስፋት አይተው በበታች አመራሮች ላይ ጣት ከመቀሰር ውጭ፤ ያደረጉት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ህብረተሰቡ ቀየውን በመተው እየተሰደደ መሆኑን ተጎጂዎች ተናግረዋል፡፡
ከመንግስት እጅ እርዳታ እናገኛለን በማለት ቢጠብቁም ምላሽ እንዳጡ የሚናገሩት ተጎጂዎች ‹‹የገዥው መንግስት አመራሮች በአካል ተገኝተው ቢመለከቱም ለደረሰው ችግር አፋጣኝ ምላሽ ባለመኖሩ በረሃብ ከምንሞት በማለት ወደአቅራቢያ ከተሞች በመሄድ ለመለመን ተገደናል፡፡›› በማለት ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ ተሰደው የመጡ ተጎጅዎች ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ኤጀንሲ በድርቅ ለተጎዱት ኢትዮጵያውያን የሚውል 50 ሚሊዮን ዶላር አፋጣኝ እርዳታ ጠይቋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የምርቱ መጠን 90 በመቶ ድረስ ቀንሷል የሚለው ድርጅቱ ፣ በምስራቁ የአገሪቱ ክፍል ምርት የሚባል ነገር ጨርሶ መጥፋቱን ገልጿል።
የውሃ ችግሩ ዝናብ እስከሚጀምርበት መጋቢት ወር ድረስ ይቀጥላል። ይህ አመት የከፋ ነው የሚሉት የድርጅቱ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ሚ/ር አማዱ አላሁሬ፣ አሁን የሚታየው ዋጋ መጨመሩን ከቀጠለ፣ የምግብ ክምችቱ ከተራቆተ ፣እንስሳት በምግብ እጥረት ከተዳከሙና የምርት መጠኑ ከቀነሰ፣ ምግብ የማግኘት ተስፋው የተመናመነ ይሆናል ። የተመድ የምግብ ኤጄንሲ ችግሩ የከፋ ይሆናል በማለት እያስጠነቀቀ ቢገኝም፣ መንግስት ግን ገንዘብ ለመለመን እንዲመቻቸው ችግሩን ያጋንናሉ እያለ ይወቅሳቸዋል።
መንግስት እስካሁን 300 ሚለዮን ዶላር አውጥቶ ችግረኞችን መርዳቱን ገልጿል። በዚህ አመት አጠቃላይ የሚያስፈልገው መጠን 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው።

No comments:

Post a Comment