Monday, January 4, 2016

በኦሮሚያ የመለስ ፓርኮችና የአደባባይ ፎቶግራፎች ተቃጠሉ


ኢሳት (ታህሳስ 25 ፣ 2008)
በኦሮሚያ ክልል ከማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የተነሳው ተቃውሞ ሰሞኑን እንደገና አገርሽቶ በተለይም በምስራቁ የአገራችን ክፍል ከፍተኛ አለመረጋጋት መከሰቱን ከስፍራው የሚወጡ ዘገባዎች አመለከቱ።
በምዕራብ ሃረርጌ ዞን ሂርና ከተማ እና በምስራቅ ሃረርጌ ዞን በደኖ ወረዳዎች በህወሃት/ኢህአዴግ ታጣቂዎችና በነዋሪው ህዝብ መካከል ከፍተኛ ግጭትና ፍጥጫ እንደነበር የአይን እማኞች ከስፍራው ለኢሳት ተናግረዋል።
በበደኖና በሂርና አርብ የጀመረው ተቃውሞው እስከዛሬ ሰኞ ድረስ እንደቀጠለም ታውቋል። በሁለቱም አካባቢዎች አውራ ጎዳናዎች ተዘግተው እንደነበርና፣ ህዝቡም ተቃውሞ ሲያሰማ እንደሰነበተ እሳት ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኤጀሬ ሰሜን ሸዋ የመለስ ዜናዊ ፓርክ ቅዳሜ ምሽት ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል። ከሁለት ሳምንት በፊትም በጀልዱ የሚገኘው የአቶ መለስ ዜናዊ ብሄራዊ ፓርክ መቃጠሉን ኢሳት ዘግቦ እንደነበር ይታወሳል። የአቶ መለስ ፎቶግራፎችም በአንዳንድ ኦሮሚያ አካባቢዎች እንደተቃጠሉ ለማወቅ ተችሏል። በአርሲም ሰሞኑን በአደባባይ የተሰቀሉ የአቶ መለስ ዜናዊ ፎቶዎች እንደተቃጠሉ በስፍራው የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል።
የአቶ መለስ ዜናዊ ፓርክና ፎቶግራፍ ማቃጠል ላይ ህዝቡ ለምን እንዳተኮረ የተጠየቁት አንድ የኢጄሬ አካባቢው ነዋሪ፣ አቶ መለስ ዜናዊ በአገዛዝ ዘመናቸው ያመጡት ጎጠኝነት እና አገሪቷን በዘውግ በመከፋፈል ላይ የተመሰረተ የአስተዳደር ስርዓት ህዝቡን ለከፍተኛ ጭቆናና ብዝበዛ ኣንደዳረገው ገልጸው፣ ይህን ጭቆናና ብዝበዛ ለመቃወም በስማቸው የተሰየመውን ፓርክና ፎቶግራፍ አቃጥለነዋል ብለዋል።
“አገሪቷ በሙት መንፈስ መመራት የለባትም” ያሉት እኚህ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት ሰው፣ “የመለስ ራዕይ ከሚሉት ቅዠት ህዝቡን ነጻ ማውጣት አለብን” ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
ሌሎች እሳት ያነጋገራቸው ሰዎችም በአቶ መለስ ዜናዊ የተሰየሙት ፓርኮችና በየአደባባዩ የተሰቀሉት ፎቶግራፎች እየተቃጠሉበት ያሉበት ምክንያት አሁን በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች በገሃድ እየታየ ያለውን ጭቆናና ግፍ ያመጡብን አቶ መለስ በመሆናቸው ይህንን ለመቃውም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል።

No comments:

Post a Comment