Saturday, December 23, 2017

አዲስ አበባ(DR.Tadesse Biru Kersmo)

ስለአዲስ አበባ አዘውትረን የምንናገርበትና የምንጽፍበት ወቅት እየመጣ ነው !!!
አዲስ አበባ - አጠገቧ ባሉ ከተሞች ሕፃናትና አዛውንት በአጋዚ ጥይት ሲቆሉ የማትሰማ፤ ብትሰማም ምላሽ የማትሰጥ ከተማ ናት። ማዕከላዊ፣ ቃሊቲና ቂሊንጦን ይዛ ስለእነዚህ የማታውቅ ለመምሰል የምትጥር፤ የገዛ ራስዋን እየሸነገለች የምትኖር ከተማ ናት።
አዲስ አበባ - በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿ በኑሮ ውድነት የሚጠበሱባት፤ በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ሀብታሞች ደግሞ የመቶ ብሮች ኖቶችን በጭፈራ ቤት ዘፋኞች አናት ላይ የሚነሰኑስባት የጉድ ከተማ ነች።
አዲስ አበባ - ለሁለት ሚሊዮን ነዋሪዎች በተሠራ መሠረተ ልማት ከ8-10 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ የሚገለገልባት በሕዝብ ብዛት ልትፈነዳ የደረሰች ከተማ ነች።

አዲስ አበባ - ሕንፃ እንደ እንጉዳይ እየበቀለባት በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ነዋሪዎቿ አስፋት ዳር እና በረንዳ ላይ የሚያድሩባት፤ የድሀ ሕይወት የረከሰባት ከተማ ነች።
አዲስ አበባ - ነባር ነዋሪዎቿ ወደ ከተማዋ ዳር ተወርውረው አዳዲስ ሰፋሪዎች መሀል ከተማውን በወረራ የያዙባት፤ ለወራሪዎች እንጂ ለነዋሪቿ የማትመች ከተማ ነች።
አዲስ አበባ - ይህ ሁሉ ችግር እያለባት የኤፍ ኤፍ ሬድዮ ጣቢያዎቿ ስለእንግሊዝ ፕሪመር ሊግ ጨዋታ ሲናገሩ ውለው የሚያድሩባት፤ በአዳዲስ ቻናሎች ተከታታይ ፊልሞች የሚታዩባት፤ ወጣቱ ውሎው ጫት ቤት የሆነባት አሳዛኝ ከተማ ናት።
አዲስ አበባ ......
አዲስ አበባ ....
ከእንግዲህ ግን አዲስ አበባ እንዲህ አትቀጥልም!!!!አዲስ አበባ ስትነቃ መላዋ ኢትዮጵያ በፈጣን ለውጥ ሂደት ውስጥ ትገባለች።

No comments:

Post a Comment