Wednesday, December 27, 2017

በአዳማ ከተማ አገዛዙን በማውገዝ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደ

ታህሳስ 17 ቀን 2010 ዓም በአዳማ ከተማ ጥቁር ዓባይ እና ቦኮ ሚካኤል በመባል በሚጠሩት አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች አገዛዙን የሚያወግዙ የተለያዩ መፈክሮችን አሰምተዋል።
ከአራት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ በዘለቀው ትእይንተ ሕዝብ ላይ ነዋሪዎቹ ኢህአዲግ አይገዛንም፣ ንጹሃን ዜጎችን መግደልና ማፈናቀል ይቁም፣ ፍትህና ነጻነት እንፈልጋለን የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል። አርሶ አደሮች፣ የቀን ሰራተኞች፣ ተማሪዎች በጋራ በአንድ ድምጽ የህወሃት ኢህአዴግን አገዛዝ ባወገዙበት ወቅት ለተወሰነ ሰዓት መንገዶች ዝግ ሆነው ነበር።

የከተማዋ ፖሊሶችና የመከላከያ ሰራዊት አካባቢውን በመክበብ በኃይል አድማው እንዲበተን አድርገዋል። ከከተማው ውጪ የሶደሬን መስመር ተከትሎ ከሉጎ ገ/ማኅበር እስከ አዋሽ መልካሳ መንገድ ያለውን የአርሶ አደሮችን መሬት ለመቀራመት መስተዳደሩ የጀመረው አሰራር ለግጭቶች መቀስቀስ መነሻ ሆኗል።
ባለፈው ወር የአዳማ ከተማ አስተዳደር በሊዝ ስም መሬትን በሸንሽኖ ለመሸጥ እንዲመቸው የነባር ባለይዞታ አርሶ አደሮችን መኖሪያ ቤቶች ማፍረስ መጀመሩን ተከትሎ ቤታችን በላያችን ላይ አይፈርስም ባሉ ባለይዞታዎችና በጸጥታ ኃይሎች መሃከል ግጭት መቀስቀሱ ይታወሳል።
በግጭቱም አቶ ወርዶፋ የተባሉ አንድ አርሶ አደር በሶስት የፖሊስ ጥይት ተመተው ሕይወታቸው አሁንም አደጋ ላይ ያለ ሲሆን አንድ ፖሊስም በወቅቱ ጉዳት ደርሶበታል። በምስራቅ ሸዋና አካባቢው ስርዓቱን የሚያወግዙ ተቃውሞዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ አድማሳቸውን እያሰፉ መጥተዋል።

No comments:

Post a Comment