Friday, December 1, 2017

የሃረማያ የጤና ሳይንስ ፋኩልቲ ተማሪዎች ትምህርት አቋረጡ

የዩኒቨርስቲው ም/ል ፕሬዚዳንት ከስልጣን ተነስተዋል
የሃረማያ ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ ተማሪዎች በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ግቢውን ለቀው ከወጡ በሁዋላ፣ ዛሬ ህዳር 22 ቀን 2010 ዓም ደግሞ የጤና ሳይንስ ቅርንጫፍ ተማሪዎች ጓደኞቻቸውን ተከትሎ ትምህርት አቋርጠው ግቢውን ለቀው ወጥተዋል።
ተማሪዎቹ “5 አመት ሙሉ ከለፋን በሁዋላ በማጠቃለያ ፈተና አሳበው ሊጥሉን” ይፈልጋሉ በማለት አዲሱን የምዘና ፈተና የሚቃወሙት ሲሆን፣ መንግስት “በመምህራን በቃት ላይ ጥያቄ ካለው ትኩረቱ መምህራን ላይ እንጅ ደግሞ እዚህ ደረጃ በደረሰው ተማሪ ላይ ሊሆን አይገባም” በማለት እርምጃውን ተቃውመዋል። ተማሪዎቹ “መከላከያ ድንበር መጠበቅ እንጅ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ምን ይሰራል? ከግቢያችን ይውጣ፣ በቦረና ለደረሰው እልቂት ወያኔ ሃላፊነቱን ይውሰድ፣ ፍትህ ይሰጥ፣ ወያኔ አብቅቶለታል፣ በቃን” የሚሉ መፈክሮችንም አሰምተዋል። 

በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የኦሮምያ ፖሊስ ቢታይም፣ በተማሪዎቹ ላይ የወሰደው እርምጃ የለም።
በሌላ በኩል “ከመከላከያ ጋር ግንኙነት አላቸው ለህወሃት መረጃ ያቀብላሉ” በማለት ተማሪዎች ከስልጣን እንዲነሱላቸው የጠየቁዋቸው የዩኒቨርስቲው ም/ል ፕሬዚዳንት ዶ/ር በላይነህ ለገሰ እና የተማሪዎች የአገልግሎት ክፍል ዳይሬክቶሬት የሆኑትን አቶ ደረጀ ዩኒቨርስቲው ከስልጣናቸው ተነስተዋል።
ዛሬ የሃረሪ ክልል እና የምስራቅ ሃረርጌ ባለስልጣናት ሀረር የሚገኙ ተማሪዎችን መንገድ ላይ ሰብስበው፣ “ እባካችሁ ትምህርታችሁን ጀምሩ ጥያቄያችሁ ይመለስላችሁዋል” ብለው ቢማጸኑም፣ ተማሪዎች ግን ፈቃደኛ አልሆኑም። “አሁን ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ሄደው ባለበት ሰአት፣ እኛ ተለይተን የምንማርበት ሁኔታ አይኖርም’ ያሉት ተማሪዎች፣ ጥያቄዎች አንድ በአንድ መመለሳቸው በመገናኛ ብዙሃን ተገልጾ ሁሉም ተማሪዎች እንዲመለሱ ጥሪ ካልቀረበ በስተቀር ትምህርት አንጀምርም ብለዋል።
ሃረማያ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ከ40 ሺ ያላነሱ ተማሪዎችን ያሰለጥናል።

No comments:

Post a Comment