Friday, December 1, 2017

አቶ አብዲ ሙሃመድ የመከላከያ መሪዎችን እና የህወሃት ባለስልጣኖችን እየተማጸኑ ነው

አቶ አብዲ ሙሃመድ የመከላከያ መሪዎችን እና የህወሃት ባለስልጣኖችን እየተማጸኑ ነው
በኢትዮ ሶማሊ ክልል የሚታየው የህዝቡ ሁኔታ ያስፈራቸው የሶማሊ ክልል መሪ አቶ አብዲ ሙሃመድ የህወሃት የጦር መኮንኖችንና ባለስልጣናትን እርዳታ እየተማጸኑ ነው።
በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚያ ቀውጥ መከሰቱን ተከትሎ የህዝቡ ተቃውሞ እለት እለት እያየለ በመምጣቱ ስርዓት አልበኝነት ሊፈጠር ይችላል የሚል አስተያየት እየተሰጠ ሲሆን፣ አቶ አብዲ የራሳቸው ጎሳ አባላት ሳይቀሩ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቄ እያደረጉዋቸው መሆኑን በመግለጽ፣ የህወሃት ባለስልጣናት ሙሉ ድጋፍ እንዲሰጡዋቸው በመወትወት ላይ ናቸው።አቶ አብዲ “ወደ ውጭ አገር እንደሚሄዱ ወይም ጫካ እንደሚገቡ” እስከማስፈራራት መድረሳቸውን የሚገልጹት ምንጮች፣ በተለይም ከአገር የመውጣት እድል ካጋጠማቸው በርካታ ሚስጢሮችን ሊያወጡ እንደሚችሉ መዛታቸው የህወሃት ባለስልጣናት መወሰን እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። አቶ አብዲ ህወሃት ገሸሽ እንዳደረጋቸው ለአመራሩ ገልጸዋል።
በክልሉ የሚታዬው ስርዓት አልበኝነት መጠናከር አሁንም በክልሉ የሚኖሩ የሌሎች ብሄር ተወላጆች ስጋት ላይ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል። በተለይ በውጫሌ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ንብረታቸውን እየተቀሙ እንዲሁም በሌሊት እየተወሰዱ እየተገደሉ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች
አመልክተዋል።
የኢኮኖሚው መላሸቅ የፈጠረው ጫና እያየለ ቢመጣም፣ የሶማሊ ልዩ ሃይል አባላት አሁንም በአካባቢው በሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት አላቆሙም። ባለፈው ሳምንት 28 ሰዎች በሞያሌ እና በነገሌ ቦረና አካባቢ መገደላቸውን ኢሳት ዘግቧል። የአገሪቱ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትርም ይህንኑ አረጋግጠዋል። የሶማሊ ክልል ባለስልጣናት ለወራት በዘለቀው ግጭት ተጠያቂ የሆኑ አካላትን አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ሚኒስትሩ ቢገልጹም፣ ውሳኔውን ለማስፈጸም በሂደት ስለሚወሰደው እርምጃ የተናገሩት ነገር የለም።
በሌላ በኩል በቀን እስከ 3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የምታገኘው ሶማሊ ላንድ ከኦሮምያ የሚላከው ጫት እና ፍራፍሬ በመቋረጡ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ተዳርጋለች። የሃገሪቱ መሪ ሰሞኑን ለአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የንግድ እንቅስቃሴው እንዲጀመር ተማጽኖ አቅርበዋል።

No comments:

Post a Comment