Wednesday, December 27, 2017

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተከሰተውን ግጭት ለማባባስና የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናትን ተጠያቂ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀመረ።

 በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተከሰተውን ግጭት ለማባባስና የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናትን ተጠያቂ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀመረ። በሕወሃቱ አመራር አቶ ጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነት መስሪያ ቤት ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በሰፊው በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑንም መረጃዎች አመልክተዋል። ይህንን ለማስፈጸም የፓርቲና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የመዝናኛ ጣቢያ ጋዜጠኞችን ጭምር የጉዞና የውሎ አበል ከፍሎ ማሰማራቱን መረዳት ተችሏል። የሕወሃት ተቋማት ከሆኑት ኢ ኤን ኤን ቴሌቪዥን እንዲሁም አይጋ ፎረም ከተባለው ድረገጽና በፌስ ቡክ ላይ የተሰማሩ የህወሃት አባላትን ጨምሮ ወደ ጅጅጋ የተጓዙት ጋዜጠኞች ተፈናቃዮቹ ወደሚገኙበት በተሽከርካሪ ተጉዘው ተፈናቃዮቹን ማነጋገራቸው ታውቋል። የተመረጡ ሰዎችን ብቻ በጋራ እንዲያነጋግሩ በተመቻቸበት በዚህ መድረክ ኦሮሞዎች ጥቃትና ግፍ ፈጸሙብን የሚሉ የሶማሌ ክልል ተወላጆች አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ተደርገዋል። አሰቃቂ የሚባሉ ግፎች በተተረኩበት በዚህ መግለጫ የኦሮሚያ ክልል
ባለስልጣናት በተለይም አቶ አባዱላ ገመዳና የመንግስት ቃል አቀባዩ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ በሕግ እንዲጠየቁ ተፈናቃዮቹ መጠየቃቸውን አይጋ ፎረም የተባለው የሕወሃት ደጋፊ ድረገጽ በድምጽ አሰራጭቷል። ግጭቱን ሊያባብሱ የሚችሉ ዘግናኝ ትዕይንቶችን በድምጽ በማያያዝ ሪፖርቱን ያሰራጨው አይጋ ፎረም በሀገሪቱ ህግ ያልተመዘገበና ፈቃድ የሌለው ቢሆንም ጋዜጠኛ ጅጅጋ ድረስ በመላክ ለጆሮ የሚቀፍ ሕዝብን ወደ ግጭት የሚወስድ ዘገባ ማሰራጨቱ ታውቋል። ኢ ኤን ኤን በተባለው ሕወሃቶች አዲስ ባዋቀሩት ቴሌቪዥን በምስል ይሰራጫል ተብሎ የሚጠበቀው ሪፖርት የደህንነቱ ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ የኦሕዴድን ባለስልጣናት ለማስፈራራት ያቀናበሩት እንደሆነም ተመልክቷል። ይህም ቅንብር የኦሕዴድ መሪዎችን አስፈራርቶ እንደዚህ ቀደሙ በሕወሃት ፍላጎት ለማስኬድ የታለመ ሲሆን የብአዴን መሪዎችን ደግሞ በቅማንት ጉዳይ ላይ ተጠያቂ የሚያደርግ ፊልም በመቀናበር ላይ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ግጭት የኦህዴድ አመራሮች ከሕወሃት በተቃራኒ መሄዳቸውን ተከትሎ የተከሰተ መሆኑ ይታወቃል። በሕወሃቱ የጦር ጄኔራል አብርሃ ወልደማርያም የቅርብ አመራር ይሰጠዋል የሚባለው የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል ፖሊስ ድንበር ጥሶ ገብቶ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጥቃት በማድረሱ ግጭቱ መቀስቀሱ ይታወሳል። በዚህ ጥቃትና በተሰጠ የአጸፋ ምላሽ በሁለቱም ወገን ሰላማዊ ሰዎች ማለቃቸው፣በመቶ ሺዎች መፈናቀላቸው ይታወሳል። የሕወሃቱ አይጋ ፎረም አቶ አባዱላ ገመዳና ቃል አቀባዩ ነገረ ሌንጮ ለፍርድ ይቅረቡ የሚለውን አስተያየት ያስተላለፈበት ምክንያት ግን አልታወቀም።

No comments:

Post a Comment