Thursday, December 7, 2017

የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ አባይ ወልዱን ከትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትነት ለማንሳት የሚደረገው ሙከራ ተቃውሞ እንደገጠመው ምንጮች ገለጹ

የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ አባይ ወልዱን ከትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትነት ለማንሳት የሚደረገው ሙከራ ተቃውሞ እንደገጠመው ምንጮች ገለጹ። ለተቃውሞ ምክንያት የሆነውም የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከልጣናቸው ሳይወርዱ አቶ አባይ ወልዱ መነሳት የለባቸውም በሚል እንደሆነም ታውቋል። በዚህ ሳቢያ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን በቅድሚያ ለማውረድ በሕወሃት ጣልቃ ገብነት እንቅስቃሴ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ብአዴን አስቸኳይ ስብሰባ የጠራ ሲሆን ብአዴኖች የህወሃትን ጣልቃ ገብነት ለማስወገድና የአቶ ገዱን ስልጣን ለማስቀጠል የኦህዴድን ድጋፍ መጠየቃቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። የጎንደር ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ከተካሄደበት ከሃምሌ 2008 ጀምሮ በሕወሃት ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ትችት እንዲሁም ዘለፋ ጭምር እየተሰነዘረባቸው የቀጠለው አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ከልጣን ለማንሳት ከዘጠኝ ወራት በፊት የተደረገው ሙከራ ሕዝባዊ ተቃውሞን በመስጋት መታፈኑን የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት አቶ አባይ ወልዱን ለማንሳት አቶ ገዱን በቅድሚያ ከስልጣን ማውረድ ጥቂት በማይባሉ የሕወሃት ደጋፊዎች ቅድመ ሁኔታ ሆኖ መቅረቡም ተሰምቷል። በአቶ ስብሃት የሚመራው ቡድንም ብአዴን ውስጥ ከሚገኙ የህወሃት ደጋፊዎች ከእነ አቶ አለምነህ መኮንን ጋር የቅንጅት ስራ መጀመሩም ተመልክቷል። የሕወሃት ደጋፊዎችን ጥያቄ ለመመለስ በሚል በአቶ ገዱ ላይ ርምጃ ለመውሰድ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመግታት በዞንና በወረዳ የሚገኙ የብአዴን አመራሮችና አባላት እንዲሁም የኦህዴድ አመራሮች እንዲንቀሳቀሱ በብአዴን አባላት ዘንድ ጥሪ በመተላለፍ ላይ መሆኑንም መረዳት ተችሏል። በአቶ ስብሃት ነጋ የሚመራው የሕወሃት ቡድን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን የማውረድ እንቅስቃሴ ከተሳካለት በኦሮሚያ ክልል በእነ አቶ ለማ መገርሳ ላይ ተመሳሳይ ርምጃ ከመውሰድ እንደማይመለስ ምንጮቹ ይገልጻሉ። ሁለቱ ድርጅቶች ማለትም ኦህዴድና ብአዴን፣ ደኢህዴንን ጨምሮ በየተራ ከመመታት ተባብረው የህወሃት ግፊትን መግታት እንደሚገባቸው የፖለቲካ ምሁራን አስተያየታቸውን በመስጠት ላይ ናቸው።

No comments:

Post a Comment