Friday, December 8, 2017

የህወሃት አገዛዝ ትዕግስተኛውንና በፈሪሃ እግዚአብሔር በተመሠረተ ጨዋነት ላይ የሚኖረውን ሕዝባችንን ወዳልተፈለገ ብጥብጥ እንዲያመራ እየገፋፋው ነው ሲል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ።

የህወሃት አገዛዝ ትዕግስተኛውንና በፈሪሃ እግዚአብሔር በተመሠረተ ጨዋነት ላይ የሚኖረውን ሕዝባችንን ወዳልተፈለገ ብጥብጥ እንዲያመራ እየገፋፋው ነው ሲል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ። “ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም ፥ ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም ”በሚል ርዕስ መግለጫ ያወጣው ቅዱስ ሲኖዶስ በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን እጅግ ኋላ ቀር በሆነ ፖለቲካ አገርን ለመምራት መሞክር በዘመኑ ያለመኖርን ያህል ይቆጠራል በዓለም መድረክ ፊትም ያጋልጣል ብሏል ። ቅዱስ ሲኖዶሱ እግዚእብሔርን አጋዥ በማድረግ እርስ በርሳችሁ እየተረዳዳችሁ፥ በጸሎትና በምህላ ይህን ክፉ ቀን አሳልፉ ሲል በእግዚአብሔር ስም ጥሪውን አስተላልፏል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ “ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም ፥ ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም”በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫው ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ ስም የዕለት ጥቅም ለማግኘት የሚጥሩ ፖለቲከኞች እንዳያታልሏችሁ ሲል አደራውን አስቀምጧል። የሲኖዶሱ መግለጫ ሲቀጥልም የህወሃት አገዛዝ ወደ ስልጣን ሲመጣ አስፈሪውን ደርግ አባሮ ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ እየፈጸመው ያለው ተግባር ግን ከደርግ እጅጉን ይከፋ ሆኗል ብሏል። ሲኖዶሱ እንደሚለው ዜጎቻችን በእንግልትና በስደት ላይ ሆነው ለሽያጭ ሲቀርቡ ማየት፣የመቶ አመት አሮጊት በራሳቸው ዜጎች በግፍ ተደብድበው እንዲገደሉ ሲደረግና የዕለት ተዕለት የህዝብን ሰቆቃ መስማት ልብን የሚያደማ ድርጊት ነው ብሏል ሲኖዶሱ። እግዚአብሔር
ከተማን ካልጠበቀ ፥ ሥልጣንንም እርሱ ካላከበረ በቀር የጠነከረ ወታደር በማቆምና መሣሪያ በማስታጠቅ ሥልጣንን ማቆየት በፍጹም አይቻልም ብሏል ሲኖዶሱ በመግለጫው። ሲኖዶሱ እንደሚለው በአሁኑ ጊዜ ሕዝባችን አንድ በመሆንና በሰላማዊ መንገድ መብቱን ለማስጠበቅ ጥረት በማድረግ ላይ ነው። አገዛዙ ደግሞ ባልሞት ባይ ተጋዳይነት ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ ትዕግሥተኛውንና በፈሪሃ እግዚአብሔር ላይ በተመሠረተ ጨዋነት የሚኖረውን ሕዝብ ወዳልተፈለገ ብጥብጥ እየገፋፋው ነው ብሏል። ይህ ደግሞ በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን እጅግ ኋላ ቀር በሆነ ፖለቲካ ሀገርን የመምራት ያህል ይቆጠራል ይላል የሲኖዶሱ መግለጫ። ከየትኛውም የሕወሃት ፖለቲከኛ አንደበት ኢትዮጵያ የሚል ቃል ሰምተን አናውቅም ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ የዚህ አገዛዝ ዋናው መለያ በህዝብ ውስጥ ልዩነትና ዘረኝነትን ማስፈን ነው ሲል ገልጿል። እናንተ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብራችሁ የኖራችሁ አሁንም የምትኖሩ ናችሁ ፣ለዕለት ጥቅም የቆሙ ፖለቲከኞች አያታሏችሁ ፣ እነርሱ ያልፋሉ እናንተ ግን ሁልጊዜ ትኖራላችሁ ፣ እናንተ ስታልፉ ልጆቻችሁ ይተካሉ በማለት ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ ትማጸናለች ብሏል መግለጫው። መግለጫው በፖለቲካ ስም የዕለት ጥቅም ለማግኘት የሚጥሩ ፖለቲከኞች እንዳያታልሏችሁ አደራ ብላለች ቤተክርስቲያኗ ብሏል ። እናንተ የተለያየ ቋንቋ የምትናገሩ ነገር ግን በአንድ ምድር የምትኖሩ አንድ ሕዝብ ናችሁ ፣ ታሪክ የሚያስረዳው ይህንን ሀቅ ነው ። ልዩ ናችሁ የሚሏችሁ ፖለቲከኞች ሌላ ሥራ አጥተው የናንተን ልዩነት ለሥራ ማግኛ ለማድረግ ነውና ተጠንቀቁ ብላለች ቤተክርስቲያኗ። እናንተ አብራችሁ የኖራችሁ ፣ለወደፊትም አብራችሁ የምትኖሩ ጨዋና ኩሩ ሕዝብ ናችሁ በሚል ጽሁፉን ያሰፈረው የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ እግዚእብሔርን አጋዥ አድርጋችሁ ፣ እርስ በርሳችሁ እየተረዳዳችሁ በጸሎትና በምህላ ይህን ክፉ ቀን አሳልፉ ሲል ጥሪውን አስተላልፏል።

No comments:

Post a Comment