Friday, December 8, 2017

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኛ ባለመሆኑ የመብት ጥሰቶች በሌላ ገለልተኛ አካል እንዲጣራልን ሲሉ እስረኞች ጠየቁ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኛ ባለመሆኑ የመብት ጥሰቶች በሌላ ገለልተኛ አካል እንዲጣራልን ሲሉ እስረኞች ጠየቁ
በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ የተከሰሱ 38 እስረኞች በሸዋ ሮቢት እስር ቤት ውስጥ እያሉ በምርመራ ስም ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እንደተፈጸሙባቸው አቤቱታ ማቅረባቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲያጣራ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።
ኮሚሽኑ በበኩሉ አጣርቼዋለሁ ያለውን የምርመራ ውጤት ለፍርድ ቤትና ለተከሳሾች እንዲደርስ አድርጓል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ በሪፖርቱ ላይ አስተያየት ካላቸው እንዲያቀርቡ ከመደበኛው ቀጠሮ ውጭ ለህዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲቀርቡ ጠርቷቸው ነበር።
የተከሳሾቹ ጠበቆች በበኩላቸው ቀጠሮው በምርመራ ሪፖርቱ ላይ አስተያየት ለመስጠት እንደሆነ ባለመገለፁ አስተያየታቸውን በጽሁፍ ይዘው አለማቅረባቸውን አሳውቀው አስተያየታቸውን ከመደበኛ ቀጠሮ በፊት በጽሁፍ እንደሚያስገቡ ተናግረዋል።
ያለጠበቃ በግላቸው የሚሟገቱት 18ኛ ተከሳሽ አቶ አንጋው ተገኘና 3ኛ ተከሳሽ አሸናፊ አካሉ በአካል ቀርበው በቃል አስተያየታቸውን ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል።

''ድብደባው በሁለት ዙር የተፈጸመ ነው። አንደኛው ዙር እኔን ጨምሮ በ175 ሰዎች ላይ ከነሃሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም የተፈፀመ ሲሆን ከተደበደብነው ውስጥ 6 በመቶው ብቻ ነው በሪፖርቱ ላይ የቀረበው። በሁለተኛው ዙር ላይ በስቅላትና በቶርች የተደረገ ሲሆን ይህም አልተመረመረም። ሰብዓዊ መብት ኮምሽንን ፈርተነዋል። ለኢህአዴግ መረጃ እየሰጠ እያስደበደበን ነው። ኢንስፔክተር ዓለማየሁ የተባለ ድብደባ የፈፀመብን ፖሊስ በብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ስብሰባ በቴሌቪዥን አይተነዋል። አሁንም ለእኛ ለመናገር አደጋ ነው። አሁንም የተፈፀመብን እንደገና ይጣራልን።'' በማለት አቶ አንጋው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
3ኛ ተከሳሽ አሸናፊ አካሉ በበኩሉ ''ኮምሽኑ በሪፖርቱ ላይ ተገኘ በተባለው ጉዳይ ላይ ምክረ ሃሳብ ይስጥ ያለው እኛን የደበደበውን ፖሊስ ነው። ፖሊስ ከመደበቅ ውጭ ሊያጣራ አይችልም። ሊያጣራ የሚገባው ሌላ ገለልተኛ አካል ነው።" ሲሉ የኮሚሽኑ አሰራር ግልጽነት የጎደለው መሆኑን ተናግሯል።
አቶ ጌታቸር እሸቴ በበኩላቸው ''ከአሁን በፊት በነበረው የምስክር መስማት ሂደት ዐቃቤ ህግ መኩሪያ ዓለሙን እሱ ራሱ ቆሞ ነው ያስገረፈን በማለቱ አቃቤ ህጉም "ምን ታደርጋለህ? ቀርጨሃለሁ!" ማለቱን በማስታወስ እንዲመዘገብለት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርቧል። ተከሳሾቹ ሸዋ ሮቢት ተደብድበው በግድ እንዲያምኑ የተደረጉትን፣ ዐቃቤ ሕግ ባለበት እየተናገሩ በቪዲዮ መቀረፃቸውን ለፍርድ ቤቱ መግለጻቸው ይታወሳል።
"የአቃቤ ህግ ምስክር ሆነው በእኛ ላይ የመሰከሩት ከእኛ ባልተናነሰ የተደበደቡት ናቸው። መብላት አቅቷቸው እኛ ነበር የምናበላቸው። ምስክሮቹም እንደኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል። ተገደው ነው የመሰከሩብን። የእነሱም ጉዳይ ሊጣራ ይገባዋል።" ሲሉ 31ኛ ተከሳሽ አቶ ጌታቸር እሸቴ በምስክሮቹም ላይ ሰቆቃ መፈጸሙን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።
"በድብደባ ምክንያት የተፈጠረብንና ያሳየነው ጠባሳ አልተመዘገበም። ኮሚሸነሩ ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚያብሄር በፓርላማ ቀርበው የቃጠሎውን ምክንያት የመልካም አስተዳደርና የአመራር ችግር ነው ብለው ሪፖርት አቅርበዋል። እኛ ደግሞ የተከሰስነው ከ6 ወር በፊት ተደራጅተው ሽብር ፈፀመዋል ተብለን ነው። ፍርድ ቤቱ እና ፓርላማው ህጋዊ ተቋም ናቸው። በመሆኑም ፓርላማ ላይ የቀረበው ሪፖርት ለፍርድ ቤቱም ሊቀርብ ይገባል። የገደሉ፣ ገልብጠው የገረፉን የወንበዴ ቡድኖችም ሊጠየቁ ይገባል። ህጉ በእኛ ብቻ ሳይሆን በእነሱም ላይ ተግባራዊ መሆን አለበት። የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችም በተመሳሳይ ተገደው ነው የመሰከሩብን።" ሲል 33ኛ ተከሳሽ አቶ ሸምሱ ሰኢድ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
8ኛ ተከሳሽ አቶ ኢብራሂም ካሚል በበኩላቸው "እምነታችንን አንቋሽሸዋል፣ ፂማችን በላይተር አቃጥለዋል፣ በደረቅ ምላጭ ላጭተውናል። ይህ የሰብአዊ መብት ሪፖርት እንዲጣራ እንዳቀረብን ተፅፏል። ግን የተፈፀመብንን አላጣራም። እኔ ከሽዋሮቢት ተመልሼ ፍርድ ቤት ስቀርብ ዳኛ ታረቀኝ ፂሜ በዛ ሁኔታ ተላጭቶ እንደማያውቁኝ ጠይቀውኛል። ሊጣራልን ይገባል።" በማለት የተፈጸመባቸውን የመብት ጥሰት ለችሎቱ አሰምተዋል።
"የሰብአዊ መብት ኮምሽን በምክረ ሃሳቡ የፌደራል ወንጀል ምርመራን ነው ያጣራ ያለው። የሰብአዊ መብት ጥሰቱን የፈፀመብን ይህ ቡድን ነው። ይህ ቡድን መርምሮ ያሳውቃል ማለት ለመሸፋፈን ነው። ፍርድ ቤቱ ጊዜውን ማጥፋት የለበትም። ጉዳዩን ለማጣራት ሌላ ገለልተኛ አካል መቋቋም አለበት። የደረሰብን የስነ ልቦና ጉዳት እንዳለ ሆኖ ተረግጠናል፣ ዓይናችን፣ እግርና ወገባችን ተጎድቷል። ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ነው፣ ምርመራ ክፍል አይደለም። በመሆኑም ሊጠየቅ ይገባል።" በማለት 1ኛ ተከሳሽ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ለችሎቱ ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment