Thursday, December 14, 2017

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ “በጨለንቆ የተፈጸመውን ዘግናኝ ፍጅት በዝምታ ማየቱ እውቅናውን እንደሰጠ ይቆጠራል” ሲል የኦሮምያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ

የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ በፌስ ቡክ ገጽ ላይ በኦሮምኛ ባወጣው ጽሁፍ የመከላከያ ሰራዊቱ በህግ የተሰጠውን መብት ጥሶ በህዝብ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ሲል ይከሳል። በአገሪቱ ህገመንግስት መሰረት የመከላከያ ሰራዊቱ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ እያለ እንደዚህ አይነት ወንጀሎች ሲፈፀሙ ከእውቅናው ውጭ ከሆነ መርምሮ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ሲገባው፣ ይህንን በማድረግ ፋንታ ተመሳሳይ ወንጀሎች ሲፈጸሙ እያየ ዝምታን መምረጡ እየተፈጸመ ላለው ወንጀል እውቅና መስጠቱን ያሳያል ሲል አቶ ሃይለማርያም ተጠያቂ አድርጓል። 
የአገር መከላከያ ሰራዊት በማንኛውም ጊዜ ለህገመንግስቱ ታዛዥ በመሆን ለፖለቲካ ፓርቲዎች ውግንና ሳያሳይ ነፃ ሆኖ የአገር ደህንነት የመጠበቅ ስራውን እንደሚሰራ ቢደነግግም፣ ሰራዊቱ ከተቋቋመለት አላማ ውጭ ታሪካዊ ስህተቶችን በህዝቦች ላይ እየፈጸመ ይገኛል ብሎአል።
በምስራቅ ሀረርጌ ዞን በሜታ ወረዳ በጨለንቆ ከተማ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ለተፈጸመው ዘግናኝ የጅምላ ፍጂት የመከላከያ ሰራዊቱን እና ዋናውን አዛዥ ጠ/ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን ተጠያቂ ያደረገው ጽሁፉ፣ ከዚህ ጅምላ ፍጂት በስተጀርባ ማነው ያለው ለሚለው ጥያቄ ለህዝቡ መልስ መስጠት ግዴታ ነው ሲል ያክላል። 

የኦሮምያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መከላከያ ሰራዊቱ ወደክልሉ እንዲገባ ጥሪ ባላደረገለት ሁኔታ የክልሉን ህዝብ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት መብቱን በመግፈፍ የፈፀመውና እየፈፀመ የሚገኘው ወንጀል የአገሪቱን ህገ-መንግስት በግልፅ የጣሰ ነው ሲል መግለጫው ያብራራል። 
የመከላከያ ሰራዊቱ አላማውን ረስቶ ያለሙያው በህዝቡ ውስጥ በመግባት እያወከ መገኘቱ የማንን አላማ ለማሳካት እንደሆነ መታወቅ አለበት የሚለው መግለጫው፣ ይህንን አሰቃቂ ወንጀል የፈፀሙትን የሰራዊቱ አባላት እና ከበስተጀርባ ሆነው ያቀዱትን ለህግ ለማቅረብ ከፌደራል መንግስት ጋር ሆኖ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል። 
የክልሉ የክልሉ የጸጥታ አካላትም የክልሉን ህዝብ ሰላም ለማስከበር ማንኛውንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ከማንኛውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆን አለባቸው ሲል ለክልሉ የጸጥታ አባላት ጥሪ አስተላልፏል። የክልሉ የጸጥታ አባላትም ህዝቡ አላስፈላጊ መስዋትነት እንዳይከፍል በመረጋጋት፣ በጥንቃቄ ፣ ከሁሉም በላይ መደማመጥና በአንድነት መንቀሳቀስ አለባቸው ብሎአል።
የኦሮሞ ህዝብ የመብት ጥያቄ ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑንና ድጋፉን እንደሚሰጥ የኮሚኒኬሽን ቢሮው ገልጿል። ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ስላቀረበና መብቱን በሰላማዊ ትግል ለማስከበር ስለተንቀሳቀሰ በየቀዬው በጅምላና በተናጠል ሊገደል፣ ከኖረበት አካባቢ ሊፈናቀልና ሽብር ሊፈጸምበት እንደማይገባ የገለጸው የክልሉ መንግስት፣ የኦሮሞ ህዝብ ለአገር አንድነት ፣ ሰላምና ብልጽግና መስዋትነት የከፈለው ለመገደል፣ ለመፈናቀልና ለመጨፍጨፍ አይደለም በማለት ድርጊቱን አውግዟል። 
መግለጫው የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በክልሉ መገናኛ ብዙሃን ቀርበው የሰጡትን መግለጫ የሚያጠናክር ነውለ። አቶ ለማ መከላከያ ሰራዊቱ በክልሉ ገብቶ ህዝብ እንዲገደል ፈቃድ አለመስጠታቸውን ገልጸው ነበር።
የክልሉ የኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ በአገሪቱ የሚፈጸሙ ግድያዎችን አድሎአዊ በሆነ መንገድ መዘገቡንም ኮንኗል። 
“የህዝብ ድምጽ ነኝ የሚለው EBC በተለያዩ ግዜዎች በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚፈጸሙ ችግሮችንና የሰዉ ህይወት መጥፋትን እንዳልሰማ ሆኖ “ ማለፉን የሚተቸው ቢሮው፣ በዚህም የተነሳ ሚዲያዉም በህዝብ ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታይና ተቀባይነት እንዳይኖርዉ አድርጎታል ብሎአል። በጨለንቆ በሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት 16 ንጹሃን ዜጎቻችን በጥይት ሲገደሉ፣ ኢቢሲ ጉዳዩን እንዳልሰማ አድርጎ ሲያልፈው፣ በአንጻሩ በወለጋ ዩኒቨርስቲ በ2 ተማሪዎች ላይ የተወሰደዉን ጥቃት በስፋት መዘገቡ የሚዲያውን ተአማኒነትና ገለልተኛነት ጥያቄ ውስጥ እንደጣለው ገልጿል። 
አንድ አገር አቀፍ ሚዲያ እዉነትን መደበቅ ሳይሆን ህዝብ የኔ ሚዲያ ነዉ ብሎ እንዲያምነዉ የሁሉንም አካባቢ ችግሮች እኩል መዘገብ ነበረበት ሲል ኮንኗል።
በሌላ በኩል ባለፈዉ ማክሰኞ የአገዛዙ ወታደሮች በጨለንቆ ከተማ ዉስጥ በሰለማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙትን ግድያ በመቃወም የሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ዛሬም ቀጥለው ውለዋል። በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች ትናንት የተጀመረው ተቃዉሞ ዛሬም ቀጥሎ ዉሏል።በወሊሶ ህዝቡ ወደ አደባባይ በመዉጣት አገዛዙን የሚያወግዙ መፈክሮችን አሰምቷል፣ “ ወያኔ ሌባ፣ህዝባችን ላይ የሚፍጸመዉ ግድያ ይቁም፣ወያኔ አይገዛንም” ይሚሉ መፈክሮች በብዛት ተሰምተዋል። በ ፉሪ፣ በአለም ገና ፣ በሰንዳፋ ፣ በጅማ ፣ አጋሮ እና ምስራቅ ሀረርጌ የተለያዩ አከባቢዎች ተቃዉሞ ሲደረግ ዉሏል።
ትላንት በአምቦ በአጋዚ ወታደሮችና በኦሮምያ ፖሊስ መካከል በተፈጠር ግጭት ከአጋዚወታደሮች የሞቱት ወታደሮች ቁጥር 4 መድረሱ ታውቋል።ወታደሮች ለህክምና ወደ ጉደር ሆስፒታል ከተላኩ በሁዋላ ህይወታቸዉ አልፏል።
በምስራቅ ሃረርጌ ባቢሌ ረረዳ የመከላከያ ሰራዊት እና በኦሮምያ ልዩ ፖሊሶች መካከል በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ከኦሮምያ ልዩ ፖሊሶች 1 ሰዉ ሲገደል ሌላ አንድ ሰው ደግሞ ቆስሏል።
የኦሮምያ ክልል አስተዳደር የክልሉ ፖሊስ ህዝቡን ከመከላከያ ሰራዊቱ ጥቃት እንዲካለከል ጥሪ ካደረጉ በሁዋላ በወታደሮችና በክልሉ ፖሊሶች መካከል አልፎ አልፎ ግጭት እየተከሰተ ነው።

No comments:

Post a Comment