Tuesday, December 5, 2017

እነ አዱኛ ቂጤሳ የክስ መዝገብ የተከሰሱ 10 ወጣቶች እያንዳንዳቸው አምስት አመት ተፈረደባቸው

አብዱ፣ ሽመልስ፣ ካሳሁን፣ ጳውሎስ፣ኬኖ፣ቶማስ፣ ኢሳያስ፣ ምትኩ እና ፈይሳ አንከላከልም ማለታቸውን ተከትሎ የተፈረደባቸው ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ እከላከላለሁ በማለቱ ቀጠሮ እንደተሰጠው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በፌስቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።
በግንቦት ሰባት ክስ የተመሰረተባቸው 7 የመከላከያ ሰራዊት አባላትም ተከላከሉ ተብለዋል። በእነ ምስጋናው ደምሴ የክስ መዝገብ የተከሰሱት መካከል ምስጋናው ደምሴ፣ አሸናፊ ሞገስ፣ ሙሉቀን ባዘዘው፣ ታዴ ብርሃኑ፣ ጌትነት አዛናው፣ ዳንኤል ዮሃንስና ሌሎች ሁለት ተከሳሾች ናቸው። ሁሉም ተከሳሾች በማንኛውም መንገድ በ"ሽብርተኛ" ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ፣ ከ1ኛ ተከሳሽ ውጭ ያሉት በኩብለላ እና 4ኛ ተከሳሽ ከመከላከያ ሰራዊት የተረከበውን እቃ አላስረከበም የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል። በሁሉም ክሶች እንዲከላከሉ ተበይኖባቸዋል። ተከሳሾቹ መዝገቡ በደንብ ሳይመረመር እንደተበደየነባቸው ለፍርድ ቤቱ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።
1ኛ ተከሳሽ ጌታሁን በየንን ጨምሮ አንከላከልም ያሉ ተከሳሾች የቅጣት አስተያየት ሲጠየቁ ፣ ጌታሁን በየነ " ለእኔ ይህ ችሎት መፍትሄ አይሰጠኝም። እኔ መፍትሄ የማገኘው ስር ነቀል ለውጥ ሲመጣ ነው፣ መፍትሄው የስርዓት ለውጥ ብቻ ነው። መፍትሄ የማገኘው ዴሞክራሲና ፍትህ ሲሰፍን ነው። ከእስር ቤት ስወጣም እታገላለሁ" በማለት በቃሉ ፍርድ ቤት ላይ ተናግሯል። ፍርድ ቤቱ 1ኛ ተከሳሽ አስተያየት በሚሰጥበት ወቅት "ይህን አንሰማህም! በስነ ስርዓት ሕጉ መሰረት አቅርብ!" እያለ በተደጋጋሚ አቋርጦታል። 

በእነ ጌታሁን በየነ የክስ መዝገብ አንከላከልም ያሉት ተከሳሾች የቅጣት ውሳኔውን ለመስማት ለታህሳስ 9/ 2010 ተቀጥረዋል።ተከሳሾቹ ቂሊንጦ እስር ቤት ውስጥ የሚገጥማቸውን ችግር በመግለፅ ቀጠሮ እንዲያጥርላቸው ጠይቀዋል። 13ኛ ተከሳሽ ባንተወሰን አበበ "የምንበላው የተፈጨ አሸዋ ነው" ሲል ለፍርድ ቤቱ በምሬት ተናግሯል።
በእነ አወል አባጊዳ የክስ መዝገብ ደግሞ 4ኛ ተከሳሽ ሰሚራ አማን 2 የመከላከያ ምስክሮችን አሰምቻለች። ከምስክሮቹ መካከል ንግስት ይርጋ ማዕከላዊ እስር ቤት በሰሚራ ላይ የተፈፀመውን በደል ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች። የማዕከላዊ መርማሪዎች የተፃፈና የሰሚራ ያልሆነን ቃል በግድ ፈርሚ በማለት ድብደባ እንደፈፀሙባት፣ በተደጋጋሚ በተፈፀመባት ድበደባ በግድ የእሷ ባልሆነ ቃል ላይ መፈረሟን፣ በግድ ለማስፈረም በተፈፀመባት ድብደባም እራሷ፣ እግሯ ላይ ጉዳት ደርሶባት ክሊኒክ ሄዳ እንደታከመች ንግስት ይርጋ የምስክርነት ቃሏን ሰጥታለች።
በሌላ በኩል ደግሞ ህዳር 9/2009 ዓም በእነ ሚፍታህ ሸህ ሱሩር መዝገብ የተከሰሰው 74ኛ ተከሳሽ ፈረደ ክንድሻቶ ይርጋ ፖሊሶች ባደረሱበት ምክንያት ሱሪ መልበስ እንደማይችል ተናግሯል።
“ከእርሻ ስመለስ ነው የያዙኝ” የሚለው ፈረደ፣ ዳንሻ ተወስዶ ተደብድቧል። ወደ ትግራይ ተወስዶ ግንድ ላይ በተጠለፈ ገመድ አስረው ጉድጓዱ ውስጥ እንዳስቀመጡትና ምግብና ውሃ ሳያገኝ መቆየቱን ገልጿል።
ወደ ሁመራ ሲመለስ ለረዥም ሰዓት እጆቹ ወደኋላ ታስረው ፀሀይ ላይ እንደቆዬ፣ ሁመራ ካለው የወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ገብቶ በዱላ ክፉኛ መደብደቡን የገለጸው ፈረደ፣ በዚህ ወቅት ብልቱን በመመታቱ ለከፍተኛ ስቃይ መዳረጉን ገልጿል።
ወደ ባህርዳር እስር ቤት ተዛውሮ ከመጣም በሁዋላ ይሁን ወደ ቂሊንጦ ከተዛወረ በሁዋላ ለሶስት ወራት ያህል ህክምና ማግኘት እንዳልቻለ፣ በመጨረሻ ግን በጥቁር አንበሳ ህክምና እንደተፈቀደለት ገልጿል። በድብደባው ምክንያት ከብልቱ በተጨማሪ ሆዱ ላይ ጉዳት ደርሶበት ቀዶጥገና ተደርጎለታል።

No comments:

Post a Comment