Wednesday, December 20, 2017

በምስራቅ ሃረርጌና በኢሉባቦር ዞኖች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄዱ

በምስራቅ ሃረርጌ በኮምቦልቻ ከተማ እንዲሁም በኢሉባቦር ዞን በመቱ ከተማ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።በኮምቦልቻ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍ መከላከያ ሰራዊቱ ከአካባቢያቸው እንዲወጣ ጠይቀዋል። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የሰጡትን መግለጫም ተማሪዎቹ አድሎአዊ የተሞላበት በማለት አውግዘውታል። የታሰሩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ሃሳባቸውን በነጻነት የገለጹ ወጣቶች እንዲፈቱም ተማሪዎች ጠይቀዋል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአካባቢው እንደሚገኙና በጨለንቆ አካባቢ ተጨማሪ 20 ቤቶችን ማቃጠላቸውን ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል ።
በመቱ ደግሞ ለ3ኛ ቀን በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ መከላከያ ሰራዊቱ ከክልሉ እንዲወጣ እንዲሁም በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እንዲቆምና በሶማሊና በኦሮምያ ክልሎች መካከል የሚካሄደው ድራማ ይቁም በማለት ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
“ የወያኔ አገዛዝ እየወደቀ በመሆኑ ህዝቡ አይኑን ስርዓቱ ላይ ማድረግ እንደሚገባውና ትግሉን ወደ ሁዋላ ከሚጎትቱ የብሄር ግጭቶች ራሱን እንዲያርቅ” ተሳታፊዎች ምክራቸውን ለግሰዋል። 

በሌላ በኩል በአገሪቱ የሚደረገውን ተቃውሞ ተከትሎ ከሩቅ አካባቢዎች የመጡና በተለያዩ ቤተሰቦች ውስጥ ተጠልለው የቆዩ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትምህርት ወደየ ቤተሰቦቻቸው በመሄዳቸው ትምህርት እንደማይጀመር ታውቋል።
በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደቱን አሁንም ተቋርጧል ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወጥተዋል
በአዳማ ዩንቨርሲቲም እንዲሁ ትምህርት አልተጀመረም። የዩንቨርሲቲው ተማሪዎች ጥያቄዎቻችን ካልተመለሱ አንማርም የሚል አቋም ይዘዋል። ከእለተ ዓርብ ታህሳስ 6 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል።
ተማሪዎቹ በኦሮሞና ሶማሌ ብሄር ተወላጆች መሃከል በወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች የተነሳ የሚፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋ ግጭቶችን በማውገዝ ትምህርታቸውን አቁመዋል። ብዛሃኛዎቹ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሄደዋል። በዩንቨርሲቲው ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ሰራዊት መስፈሩን ተቃውመዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ለሚ ጉታ የተማሪዎቹን ጥያቄዎች ሳያተባብሉ ትምህርት መቋረጡንና አብዛኛው ተማሪ በትምህርት ገበታው ላይ አለመገኘቱን አምነዋል። ነገር ግን ተማሪዎች ነገ ትምህርታቸውን እንደሚጀምሩና ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር ግቢው ውስጥ አለመኖሩን መግለጻቸው አሳማኝ አለመሆኑን ምንጮች አክለው ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment