Wednesday, December 27, 2017

በኦሮምያና ሶማሊ ድንበር አካባቢ ባለው ግጭት ብዙ ተዋንያን አሉ ሲሉ አቶ አብዲ ሙሃመድ ተናገሩ

ከ600 ሺ በላይ ዜጎችን ያፈናቀሉትን የሶማሊ ክልል መሪ አቶ አብዲ ሙሃመድን ገጽታ ለመገንባት በሚል የመንግስትና የአገዛዙ ደጋፊ ጋዜጠኞች ወደ ጅግጅጋ ተጉዘው ቃለምልልስ ያደረጉላቸው ሲሆን፣ አቶ አብዲም ከሁለቱ ክልሎች ግጭት ጀርባ ሌሎች በርካታ ተዋናዮች አሉ ብለዋል። ተዋናዮችን ግን በስም ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ግጭቱን ለማስቆም አለመቻሉንና አሁንም ድረስ የቀጠለ መሆኑን አቶ አብዲ ተናግረዋል። እኝሁ በከፍተኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል መጠየቅ እንዳለባቸው አስተያየቶች እየቀረቡባቸው የሚገኙት አቶ አብዲ፣ ከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊት አዛዦችና የህወሃት ባለስልጣናት ድጋፍ እንዳላቸው ይታወቃል። በእርሳቸው ቁጥጥር ስር የሚገኘውን 13 ሺ የሶማሊ ልዩ ሃይል ጦር በአካባቢው ሰላም ለማስፈን እንደሚጠቀሙበት የዛቱት አቶ አብዲ ፣ ማንኛውንም የጸጥታ ማስከበር ስራ ከ ጄኔራል ሳሞራ የኑስና ከጄል ገብሬ ዲላ ጋር በመመካከር የሚሰሩ መሆኑን ለመርማሪዎች ተናግረው ነበር።

አቶ አብዲ ከኦሮምያ ክልል የተፈናቀሉ የሶማሊ ተወላጆች 350 ብቻ እንደሆኑ ትልልቅ የመንግስት ባለስልጣናት ሳይቀር ይናገሩ ነበር በማለት የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩን ዶ/ር ነገሪ ሌንጮችን በሚነቅፍ መልኩ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ ሆኖም ከኦሮምያ ክልል የተፈናቀለው የሶማሊ ተወላጆች 50 ሺ ይጠጋል ብለዋል። እርሳቸው የሚመሩት ክልል ምን ያክል ሰዎችን እንዳፈናቀለ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ይሁን እንጅ የኦሮምያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊዎች 600 ሺ የኦሮሞ ተወላጆች እንደተፈናቀሉ ይናገራሉ።
ወደ ጅጅጋ የተላኩ ጋዜጠኞች የተለያዩ የኦሮሞ ተወላጆችን በማነጋገር በክልሉ ሰላም እንደሰፈነ ተደርጎ ለማቅረብ የተሰራው ድራም መክሸፉን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።
በሁለቱ ክልሎች መካከል በተነሳው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ተገድለዋል። በርካቶችም ሃብትና ንብራታቸውን ተቀምተው ተባረዋል።
ከሶማሊ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች ወደ ሶማሊ ክልል መመለስ ይፈልጉ እንደሆነ ተጠይቀው 99 በመቶ የሚሆኑት አቶ አብዲ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ለድህንነታችን ዋስትና አናገኝም በማለት መመለስ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል። ይህን ተከትሎ የለማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤቶችን ለተፈናቃዮች እየሰራ ነው።
በሁለቱ ክልሎች የድንበር ከተሞች ላይ የሚገኙ የሁለቱ ክልሎች ታጣቂዎች ከአካባቢው እንዲርቁ በፌደራል መንግስት በኩል ትዕዛዝ ቢተላለፍም ፣ በኦሮሞያ በኩል ውሳኔው የሶማሊ ልዩ ሃይል አባላትን ለመጥቀም ነው በሚል እየተቀበሉት አይደለም። የመከላከያ አዛዦች ከሶማሊ ልዩ ሃይል አባላት ጋር በመሆን የፈለጉትን እርምጃ እየወሰዱ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የኦሮምያ ሚሊሺያዎች ትጥቅ እንዲፈቱ ማድረግ ሀዝቡን ለበለጠ አደጋ እንዲጋለጥ ማድረግ ነው በማለት የድንበር አካባቢ ከተሞች ባለስልጣናት ይናገራሉ።

No comments:

Post a Comment